ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ጋር  

የደቡብ ሱዳን የሐይማኖት አባቶች እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት ሱባኤ መግባታቸው ተገለጸ።

ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 2 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ከተማ በሚገኝ በቅድስት ማርታ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የግል ጸሎት ቤት ውስጥ የተጀመረው የሱባኤ ዝግጅት ነገ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ የሚጠናቀቅ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በማጠቃለያው ስነ ስርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ እና ሱባኤውን ለተካፈሉት በሙሉ ቅዱስነታቸው እርሳቸው የፈረሙበት የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታን የሚያበረክቱ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የደቡብ ሱዳን የሐይማኖት አባቶች እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት በሕብረት ሆነው በቫቲካን ከተማ ከዛሬ ረቡዕ ሚያዚያ 2 ቀን እስከ ነገ ሚያዝያ 3 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ የሚቆይ የሁለት ቀን ሱባኤን መግባታቸው ታውቋል።  ሱባኤያቸውን የገቡት በቫቲካን ከተማ ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የግል ጸሎት ቤት ውስጥ መሆኑ ታውቋል።

የደቡብ ሱዳን የሐይማኖት አባቶች እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በቫቲካን ውስጥ ሱባኤን ለመግባት ያላቸውን ምኞት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡት የአለም አንግሊካን ቤተክርስቲያን ሕብረት መሪ እና የካንተርበሪ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ጃስቲን ዌልቢይ መሆናቸው ሲታወቅ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በሃሳባቸው የተደሰቱ መሆናቸው ታውቋል።   

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ጊዜያዊ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ ባለፈው ሳምንት ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ጊዜ እንዳስረዱት የደቡብ ሱዳን መሪዎች በቫቲካን ከተማ ተገናኝተው ሱባኤን ለመግባት እቅድ እንዳላቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

ሱባኤውን የቤተክርስቲያን አባቶች እና የመንግሥት ባለስልጣናት ይካፈሉታል፣

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል እንደገለጸው የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በሃገሪቱ ከሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ሆነው በሚቀጥለው ግንቦት 4 ቀን 2011 ዓ. ም. የጋራ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ታውቋል። የስብሰባቸው ዋና ዓላማም ተሻሽሎ በቀረበው እና የደቡብ ሱዳንን ግጭት ለማስወገድ በተደረሰበት የጋራ ስምምነት ተግባራዊነት ላይ ለመወያየት እንደሆነ ታውቋል። በጋራ ውይይቱ ላይ የሚገኙት የአገሪቱ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ከአራቱ ምክትል ፕሬዚደንት ጋር እነርሱም ሪካ ማቻር ቴኒ ዱርጎን፣ ጄምስ ኢጋ፣ ታባን ደንግ ጋይ እና ርብቃ ኛንደንግ ደ ማቢዮር መሆናቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል። በቫቲካን ከተማ የተጀመረውን የሱባኤ ዝግጅት በመካፈል ላይ የሚገኙት፣ ከደቡብ ሱዳን አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤትን የሚወክሉ ስምንት አባላት መሆናቸው ታውቋል። በሱባኤው መንፈሳዊ አስተምህሮአቸውን የሚያቀርቡት በኡጋንዳ የጉሉ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ጆን ባፕቲስት ኦዳማ እና የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ክቡር አባ አግቦንክሂያንመጌ መሆናቸው ታውቋል።

ጸሎት፣ አስተንትኖ እና ዕርቅ፣

የሱባኤውን ዝግጅት በጋራ ያስተባበሩት የቫቲካን መንግሥት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እና የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳሳት ጽሕፈት ቤት መሆኑ የታወቀ ሲሆን ዓላማውም ከቤተክርስቲያን በኩል በቀረበው ሃሳብ መሠረት የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት ከቤተክርስቲያን መሪዎች ጋር ሆነው በጸሎት እና በአስተንትኖ የሚተባበሩበትን አጋጣሚ ለመፍጠር፣ በመካከላቸው የመከባበርን እና የመተማመንን መንፈስ ለማሳደግ፣ ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ሰላምን እና ብልጽግና የተጣለባቸውን ሃላፊነት በጋራ በመሥራት እንዲወጡ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ መሆኑ ታውቋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግር፣

ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 2 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ከተማ በሚገኝ በቅድስት ማርታ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የግል ጸሎት ቤት ውስጥ የተጀመረው የሱባኤ ዝግጅት ነገ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ የሚጠናቀቅ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በማጠቃለያው ስነ ስርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ እና ሱባኤውን ለተካፈሉት በሙሉ ቅዱስነታቸው እርሳቸው የፈረሙበት የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታን የሚያበረክቱ መሆናቸው ታውቋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚገኙት የአለም አንግሊካን ቤተክርስቲያን ሕብረት መሪ እና የካንተርበሪው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ጃስቲን ዌልቢ እና የስኮትላንድ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን መሪ ክቡር አባ ጆን ቻልመርስ በጋራ ሆነው በሚያቀርቡት እና “የሚከፋፍል ሃሳብን በማስወገድ አንድ የሚያደርግ መንገድ መፈለግ ያስፈልጋል” በማለት መልዕክታቸውን የሚያቀርቡ መሆናቸው ታውቋል። በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሱባኤው ተካፋዮች ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን የሚሰጡ መሆኑ ታውቋል።    

10 Apr 2019, 14:49