ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እኛ የተቀባነው ሌሎችን ለመቀባት ነው” አሉ

አሁን የምንግኝበት ወቅት የሕማማት ውቅት እንደ ሆነ ይታወቃል። በእዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስርዐተ አምልኮ ደንብ መሰረት እኛን ለማዳን እና ከእግዚኣብሔር ጋር እኛን ለማስታረቅ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ያቀረበው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ መሰጠቱን፣ መንገላታቱን፣ በመስቀል ላይ እንደ ሌባ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ መቀበሩን እና ከሙታን መነሳቱን እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተከናወኑባቸው ሦስት ዋና ዋና ቀኖች በተለየ ሁኔታ በታላቅ መንፍሳዊነት ይከበራሉ። ከእነዚህ ቅዱሳን ከሆኑ ቀናት መካከል በቀዳሚነት የሚገኘው የጸሎተ ሐሙስ ቀን ሲሆን በዚህ እለት ኢየሱስ መከራውን ከመቀበሉ በፊት ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን ራት ከመብላቱ በፊት የሐዋሪያቱን እግር ያጠበበት፣ እርሱ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የጀመረውን መንፈሳዊ ተልዕኮ እንድያስቀጥሉ በማሰብ ምስጢረ ክህነትን የመሰረተበት፣ የመጨረሻ ራት ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር ከተካፈለ በኃላ “ይህንን ለእኔ መታሰቢያ አድርጉ” በማለት ምስጢረ ቅዱስ ቁርባንን የመሰረተበት፣ ብጹዕን ጳጳሳት በእየአገረ ስብከታቸው ከካህናቶቻቸው ጋር መስዋዕተ ቅዳሴን በማሳረግ ምስጢረ ክህነት የተመሰረተበትን ቀን በማስታወስ በጋራ መስዋዕተ ቅዳሴን የሚያሳርጉበት፣ ለምስጢረ ቀንዲል (ሕሙማንን ለመፈወስ የሚያገልግል ቅባ ቅዱስ)፣ ለሚስጢረ ጥምቀት እና ለምስጢረ ክህነት አግልግሎት የሚውሉ ቅባ ቅዱሶች በብጽዕን ጳጳሳት የሚባረኩበት እለት ተከብሮ ማለፉ ታውቁዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ይህ በዓል በሚያዝያ 10/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉ የታወቀ ሲሆን በእለቱ ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መሳዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “እኛ የተቀባነው ሌሎችን ለመቀባት ነው” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 10/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

አሁን ከሉቃስ ወንጌል ተወስዶ በተነበበው ምንባብ እንደ ሰማነው ጌታ በኢሳይያስ ስለእርሱ የተነገሩትን ትንቢቶች በህዝቡ መካከል ሆኖ ሲያነብ የነበረውን የዚያን ጊዜ የነበረውን ደስታ ዳግም እንዳንቀበል ያደርገናል። በወቅቱ የናዝሬቱ ምኩራብ በዘመዶቹ፣ በጎረቤቶች፣ እርሱን በሚያውቁት ሰዎች፣ በወዳጆቹ ጭምር ተሞልቶ ነበር። ሁሉም ዓይኖቻቸውን በእርሱ ላይ አድርገው ነበር። ቤተ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ሕዝብ እንዲቀባው በላከው በኢየሱስ ላይ ሁል ጊዜም ቢሆን ዓይኖቿን ታደርጋለች።
ቅዱስ ወንጌላችን ብዙን ጊዜ ኢየሱስ በሕዝቡ መካከል ሆኖ የሚያሳዩ ምስሎችን የሚያቀርብልን ሲሆን በሕዝቡ ተከብቦ እና የታመሙትን ወገኖቻቸውን እንዲያድን፣ እርኩሳን መናፍስትን እንዲያስወጣ በሚጠይቁት ሰዎች፣ ትምሕርቱን ለማዳመጥ በሚሰበሰቡ ሰዎች፣ በመንገድ ላይ ከእርሱ ጋር አብረው በሚሄዱ ሰዎች፣ በአጠቃላይ ከብዙ ሕዝብ ጋር በመተባበር እና በመገፋፋት ይሄድ እንደ ነበር ቅዱስ ወንጌል በተደጋጋሚ ይገልጻል። “በጎቼ ድምጼን ይሰማሉ፣ እኔም አውቃቸዋለሁ፣ እነርሱም ይከተሉኛል” (ዮሐንስ 10፡27-28)።
ጌታ ከሕዝቡ ጋር የነበረውን ቀጥተኛ ግንኙነት በፍጹም አላቋረጠም። በእነዚያ ሰዎች መካከል፣ በጠቅላላ ከሕዝቡ ጋር እና ከእያንዳንዱ ግለሰብ ጋር የነበረውን የጠበቀ፣ በጸጋ የተሞላ ግንኙነት ማድረጉን ቀጥሎ ነበር። ይህንንም ደግሞ እርሱ ከሕዝቡ ጋር በነበረው ይፋዊ ህይወቱ ውስጥ ከመጀመሪያው ጀምሮ እናያለን፡ ሕጻን በነበረበት ወቅት ያበራው የእርሱ ብርሃን ቀስ በቀስ እረኞችን፣ ነገሥታትን እና እንደ ስምዖንና አና ያሉትን ሕልማቸው እውን እንዲሆን ይመኙ የነበሩትን ሳይቀር ስቦ ነበር። በመስቀል ላይ በነበረበት ወቅት ሳይቀር የእርሱ ልብ የቬሮኒካን፣ የቀሬና አገር ሰው የነበረውን የስምዖን፣ ከእርሱ ጋር ተሰቅሎ የነበረውን የሌባውን፣ የመቶ አለቃ የነበረውን ሰው . . .ወዘተ የእርሱ ልብ የእነዚህን ሰዎች ልብ ሁሉ ስቦ ነበር።
"ሕዝብ" የሚለው ቃል አንኳሳሽ የሆነ ቃል አይደለም። ምናልባት ለአንዳንድ ሰዎች ጆሮ የሚቀፍ እና ስም አልባ የሆነ ማኅበረሰብ የሚለውን ትርጉም ሊያስተጋባ ይችላል። ነገር ግን በወንጌል ውስጥ ሕዝቡ ከጌታ ጋር ሲገናኝ - በመንጋው መካከል የተገኘ እንደ አንድ እረኛ ሆኖ በመካከላቸው ውስጥ ሲቆም- የሆነ ነገር ይከሰታል። ሕዝቡ በውስጡ ያለውን ኢየሱስን ለመከተል ያላቸው ጥልቅ ፍላጎት፣ ለእርሱ ያላቸው አድናቆት በከፍተኛ ሁኔታ እንደ ሚጨምር፣ የማስተዋል ኃይላቸው በፍጥነት እንደ ሚያድግ ያሳያል።
በኢየሱስ እና በህዝቡ መካከል ያለውን ግንኙነት በሚያንጸባርቁት በእነዚህን ሦስት የጸጋ መገለጫዎች ላይ ከእናንተ ጋር በጋራ ለማሰላሰል እፈልጋለሁ።
እርሱን የመከተል ጸጋ፣
ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ውስጥ ሕዝቡ “እርሱን እንደ ሚፈልጉት” (ሉቃ. 4፡42) እና “ከእርሱ ጋር እንደ ሚጓዙ” (ሉቃ. 14፡25) ይነግረናል። እርሱን “ይገፋፉት ነበር”፣ “እርሱን ይከቡት ነበር” (ሉቃስ 8፡42-45)፣ “እርሱን ለማዳመጥ ይሰበሰቡ ነበር” (ሉቃ. 5፡15) ይለናል። እርሱን "የተከተሉት” ባልተጠበቀ ሁኔታ የተደረገ፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የተደረገ እና በፍቅር በተሞላ መልኩ ነበር። ከእዚህ ጋር ደግሞ በንጽጽር የሚታየው በጣም ጠባብ የሆነ አስተሳሰብ የነበራቸው የእርሱ ደቀ-መዛሙርት ሲሆኑ ኢየሱስ ሕዝቡ የሚባላ ነገር ለራሳቸው እንዲፈልጉ እንዲያሰናብታቸው ጭካኔ በተሞላው ባሕሪይ ሲናገሩ እንመለከታለን። እኔ እንደ ማምነው ቀሳውስታዊ መንፈስ የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው፡- ለህዝቡ ምንም ግድ ሳይላቸው በምግብ እና በግል ምቾት የተረጋገጠ መሻት አላቸው። ጌታ የኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት ፈተና ለማጨናገፍ አስቦ “የሚበሉትን እናንተው ስጡዋቸው” በማለት የኢየሱስን ምላሽ ይሰጣል። “ሕዝቡን እንዲከባከቡ ያሳስባል”።
የመገረም ጸጋ፣
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሕዝቡ ኢየሱስን በመከተል የሚያገኘው ነገር በደስታ መንፈስ የተሞላ አጋራሞት ነው። ሕዝቡ በኢየሱስ በጣም ይደነቁ ነበር (ሉቃ. 11፡14)፣ እርሱ በሚሰራቸው ተዐምራት ይደነቁ ነበር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በእርሱ ስብዕና በጣም ይደነቁ ነበር። ሕዝቡ እርሱን በመንገድ ላይ ሊያገኙት በጣም በሚፈልጉ ሕዝቡ መካከል የነበረች አንዲት ሴት የእርሱን እናት እንደ ባረከች ሁሉ ሕዝቡ እርሱ እንዲባርካቸው እና እነርሱም በተራቸው እርሱን ለመባረክ ይፈልጉ ነበር። ጌታ ራሱ በሰዎች እምነት ተደንቆ ነበር፣ ተደስቶም ነበር፣ ይህ እድል እናዳያመልጠው ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር።
የማስተዋል ጸጋ፣
በሦስተኛ ደረጃ ሕዝቡ ከኢየሱስ የተቀበለው ጸጋ የማስተዋል ጸጋ ነው። ሕዝቡም ኢየሱስን ፈልገው አገኙት፣ ከእዚያም ተከተሉት” (ሉቃ 9፡11)። “እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ስለነበር በትምህርቱ በጣም ተደነቁ” (ማቴ 7፡28-29)። ክርስቶስ የእግዚአብሔር ቃል የነበረው ሥጋን ለብሶ ተገለጸ፣ እርሱ አከራካሪ እና አወዛጋቢ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ መስጠት የሚያስችል ግንዛቤን ሊሰጥ ሳይሆን ነገር ግን የማስተዋል ጸጋን ለሕዝቡ ሊሰጥ መጣ። ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ከእርሱ ጋር ሲወያዩ ሰዎች ያስተውሉ የነበረው የኢየሱስ ሥልጣን፣ የእርሱ የማስተማር ብቃት ልባቸውን እንደ ነካ እና እርኩሳን መናፍስት እንኳን ሳይቀር ለእርሱ ይታዘዙት እንደ ነበረ ያስተውላሉ። (አከራካሪ የሆኑ ነገሮችን እና ጥያቄዎችን ጊዜያዊ በሆነ መልኩ በማንሳት ወጥመድ ውስጥ ለመክተት የሚፈልጉ ሰዎችን ትተው የእርሱን አሰትምህሮ ሲወዱት እናያለን)።
ቅዱስ ወንጌል ሕዝቡን የሚመለከትበትን መንገድ በቅርበት እንመልከት። ቅዱስ ሉቃስ በጌታ ቅባት ለመቀባት የተመረጡትን ድሆች፣ ዓይነ ስውሮች፣ የተጨቆኑ ሰዎችን እና ምርኮኞች የተባሉትን አራት ትላልቅ ቡድኖችን ያመለክታል። እርሱ ስለ እነርሱ ጠቅለል ባለ ሁኔታ የሚናገር ሲሆን ነገር ግን ቀስ በቀስ በጌታ የሕይወት ሂደት ውስጥ እነዚህ ቅቡዓን ቀስ በቀስ እውነተኛ ስሞችን እና ገጽታዎችን መውሰድ መጀመራቸው ደግሞ ያስደስታል። በአንዱ የሰውነት ክፍል ላይ ዘይት ሲቀባ ለመላው የሰውነት ክፍል ጠቃሚ ይሆናል። እንደዚሁም ጌታ የኢሳይያስን ትንቢት በማንሳት መንፈስ ቅዱስ ወደ እነርሱ የላከውን የተለያዩ "ስፍር ቁጥር የሌላቸው" ስሞች ያላቸውን እኛ "ሁሉን የሚያካትት" ብለን የምንጠራው: ለግለሰብ ወይም ለአንድ ለየት ላለ ቡድን የተሰጠው ጸጋና ቸርነት ከእዚያ በመቀጠል ደግሞ እንደ እያንዳንዱ የመንፈስ ቅዱስ እርምጃ ለሁሉም ሰዎች መልካም ነገር ያደርጋል።
ችግረኛ የተባሉ ሰዎች ደግሞ ድሆዎች የሆኑ እና በየመንገዱ ላይ ቁጭ ብለው ምጽዋዕት የሚለምኑ ሰዎች ናቸው። ነገር ግን እንደ ድሃዋ መበለት ያሉ በጣም የተጎሳቆሉ ሰዎች ያላትን ሁለት ሳንቲሞች ምንም ሳታስቀር ሰጠች። መበለቲቱ የሰጠችው ምጽዋዕት ብቸኝነቷን ከተመለከተው ከኢየሱስ በሰተቀር የማንም ሰው እይታ አልማረከም ነበር። በእርሷ በኩል ጌታ ወንጌልን ለድሆች የማወጅ ተልዕኮውን ሙሉ በሙሉ ሊያሟላ ይችላል። በሚያስገርም መልኩ ደግሞ የዝህችን መበለት ምጽዋዕት በተመለከተ ኢየሱስ የተናግረውን መልካም ዜና ቀድሞ የሰሙት ደግሞ ደቀ-መዛሙርቱ ናቸው። የዚህችን ለጋስ ሴት ታሪክ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ይጠቀሳል ብሎ የገመተ ማንም ሰው አልነበረም። እርሷ ያከናወነችው በጣም ቀለል ያለ መገለጫ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ይሰፍራል ብሎ ያሰበ ማንም የለም። ልክ እንደ “አጠገባችን እንዳሉት ቅዱሳን” የሆኑ ወንዶች እና ሴቶች ሁሉ የእርሷ ድርጊት ውስጣዊ የሆነ ደስታን የፈጠረባት በመንግሥተ ሰማይ መለኪያ ክብደት የተሰጠው በዓለም ውስጥ ከሚገኙ ሐብታሞች የበለጠ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው ድርጊት ነው።
ማየት የተሳናቸው ሰዎች በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ቦታ ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በርተሌሜዎስ (ማቴ 10: 46-52)፣ የእኔ ብጤ የነበረው መልሶ ለማየት የቻለው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዓይኖቹ ኢየሱስን ለመከተል የተጠቀመበት ሰው ይገኙበታል። የእይታ መቀባት! ዓይኖቻችን ኢየሱስ ብቻ ሊሰጠው የሚችለውን ብርህ የሆኑ ውበቶችን ሊያንጻባርቁ የሚችሉት፣ ብርህ የሆነ ተስፋ ሊፈነጥቅ የሚችለው፣ በዓለም ጫናዎች እና ተጽዕኖዎች በእኛ ላይ መፍጠር በሚችሉ ገጽታዎች የተነሳ በየቀኑ ደስታዎቻችንን የሚሰርቁ ነገሮችን ማሸነፍ የምንችለው በእርሱ እይታ ውስጥ ስንገባ ብቻ ነው።
የተጨቆኑትን ሰዎች ለማመልከት ወንጌላዊው ሉቃስ "ስቃይ" የሚለውን ሐሳብ የያዘ ቃል ይጠቀማል። ለወንጌላዊው ሉቃስ በጣም ተመራጭ የሆነውን በዘራፊዎች ተደብድቦ እና ቆስሎ በመንገድ ላይ ተጥሎ የነበረውን ሰው ቁስል በዘይት የቀባው እና በጨርቅ የጠቀለለውን ደጉ ሳምራዊ ምሳሌን መጠቀም በራሱ በቂ ነው። የክርስቶስ የቆሰለ ሥጋ ከመቀባት ጋር ይያያዛል። በዚህ በዘይት የመቀባት ታሪክ ጎን ለጎን በተለያዩ ስቃዮች ውስጥ የሚገኙትን ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች እና ችላ የተባሉት ሕዝቦች፣ የተገለሉ እና አታስፈልጉም የተባሉ ሰዎች ይገኙበታል።
ምርኮኞች በጦርነት ወቅት የተማረኩ ሰዎች ናቸው፣ የጦር መሳሪያ በግንባራቸው ላይ ተደቅኖ የተማረኩ ሰዎች ናቸው። ኢየሱስ የእርሱ ተወዳጅ ከተማ የነበረችው ስለ ኢየሩሳሌም መያዝ እና ስለ ሕዝቦቿ ስደት በተናገረበት ወቅት ተመሳሳይ ቃላትን ተጠቅሟል (ሉቃ 21፡24)። በዛሬው ዓለም ውስጥ የሚገኙ የእኛ ከተሞች የጦር መሳሪያ በግንባራቸው ላይ ተደቅኖባቸው ሳይሆን ነገር ግን ረቂቅ በሆኑ ርዕዮተ ዓለም አስተሳሰቦች የተነሳ የቅኝ ግዛት ሥር ውስጥ የገኛሉ።
በቅድመ አያቶቻችን ልፋት እና ወግ ዘይት ተቀብቶ የተገነባው ባህል ብቻ ከባርነት ነፃ ሊያወጣ ይችላል።
እኛ ግን ውድ ወንድሞቻችን ካህናት ቅዱስ ወንጌል በአብነት ያቀረበውን እነዚያን “ሕዝቦች” እና “የተሰበሰቡ ሰዎች” "እውነተኛ" የሆኑ የፊት ገጽታዎችን "በጌታ" ቅባት በመቃባታቸው የተነሳ እንደ ገና ሕያው የሆኑትን እና ቀና ማለት የጀመሩትን ሰዎች በፍጹም መዘንጋት የለብንም። በእኛ ውስጥ ያለው የመንፈስ ቅዱስ ቅባት ምልአት እንዲያገኝ እና እውነተኛ እንዲሆን የሚያደርጉት እነርሱ ናቸው፡ የተቀባነው እነርሱን በመቀባት እንችል ዘንድ ነው። እኛ የተገኘነው ከእነርሱ መካከል በመሆኑ የተነሳ በእነርሱ መካከል ሆነን ያለ ምንም ፍርሃት ማንነታችንን መግለጽ ይኖርብናል። እነርሱ የነፍሳችን አምሳያ እና የቤተክርስቲያን ምስል ናቸው። እያንዳነዱ የህዝቦቻችንን ልብ ይጋራሉ።
እኛ ካህናት ድሆች ነን፣ እናም ለድሆች ምጽዋዕት ስንሰጥ ድሃ የነበረችው መበለት የነበራትን ዓይነት ልብ ልኖረን ይገባል፣ ምጽዋዕት የሚጠይቀንን ሰው እጅ በመንካት እና የእርሱን ወይም የእርሷን ዓይን መመልከት ይኖርብናል። እኛ ካህናት እንደ በርጤሌሞስ ነን፣ በየጠዋቱ ተነስተን “ጌታ ሆይ እንዳይ ዘንድ እርዳኝ” በማለት እንጸልያለን። እኛ ካህናት ኃጢአት በምንሰራበት ወቅት በወንበዴዎች ተደብድቦ በመንገድ ላይ እንደ ወደቀ ሰው እንሆናለን። እናም እኛም ራሳችን ለሌሎች በርኅራኄ የተሞላ እጃችንን መዘረጋት ያስችለን ዘንድ በቅድሚያ እኛ እንደ ደጉ ሳምራዊ ዓይነት ሰዎች በርኅራኄ የተሞላ ልብ ውስጥ ለመግባት እንፈልጋለን።
ቅብዓ ቅዱስ እና ማዕረገ ክህነት በምሰጥበት ወቅት በእጄ ቅብዓ ቅዱስ በሚቀባው ሰው ግንባር ላይ ወይም ማዕረገ ክህነት በሚወስደው ካህን እጅ ላይ የምቀባውን ዘይት ይዤ ለመቆየት እንደሚመኝ ልናግራችሁ እወዳለሁ። በርኅራኄ መንፈስ የምንሰጠው ቅብዓ ቅዱስ እኛ ራሳችን ከዚህ ቀደም የተቀበለነው ቅብዓ ቅዱስ እንዲታደስ ያደርጋል። ይህንን የምላችሁ ደግሞ እኛ በጠርሙስ የታሸገ ዘይት አከፋፋዮች አይደለንም። እኛ ሌሎችን በቅብዓ ቅዱስ ስንቀባ እኛም ራሳችን በመንፈስ አማካይነት እና በሕዝባችን ፍቅር በአዲስ መልክ እንቀባለን። የሌሎችን ቁስሎች፣ ሐጢአቶች እና ጭንቀቶቻቸውን ሳይቀር በመንካት እጆቻችንን በማርጠብ እንቀባቸውለን። እምነቶቻቸውን፣ ተስፋቸውን፣ ታማኝነታቸውን እና ቅድመ ሁኔታ ያልተቀመጠበት የልግስና ተግባሮቻቸውን በምንቀባበት ወቅት እጆቻችን በመልካም ሽቱ መዐዛ ይረጥባሉ።
ከኢየሱስ ጋር በጋራ አብረን በሕዝቦች መካከል በመቆም እግዚኣብሔር በውስጣችን በጥልቀት የሚገኘውን የቅድስናን መንፈስ እንዲያድስልን እንጠይቅ፣ ለኛም በአደራ የተሰጡንን ሰዎች የእርሱን ምሕረት ማቅረብ እንችል ዘንድ እርሱ ይርዳን። በዚህ መንገድ በክርስቶስ የተሰበሰቡ ሰዎች ብቸኛው ታማኝ የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆናሉ፣ ይህም በመንግሥቱ ውስጥ ሙላቱ ይሆናል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 April 2019, 15:13