የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚያዝያ ወር የጸሎት ሃሳብ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየወሩ በሚያቀርቡት የጸሎት ሃሳባቸው ለሚያዝያ ወር እንዲሆን ያሉትን የጸሎት ሃሳባቸውን ለመላው ዓለም ካቶሊካዊ ምእመናን በቪዲዮ መልዕክት በኩል አስተላልፈዋል። በዚህ የጸሎት ሃሳባቸው ጦርነቶች እና አመጾች  በሚካሄዱባቸው የዓለማችን ክፍሎች የሕክምና አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙት የጤና ባለሞያዎች ዶችተሮች፣ ነርሶች፣ የጤና ረዳቶች እና በዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙት በሙሉ የተስፋ ምልክት መሆናቸውን አስረድተዋል። እነዚህ ሰዎች ጥበበኞች፣ ደፋሮች እና ደጎች፣ ለተጠሩበት የአገልግሎት ዘርፍ ታማኞች በመሆን በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ቢገኙም የሕክምና አገልግሎታቸውን ያበረክታሉ ብለዋል። በመሆኑም ምዕመናን በሙሉ በያለንበት በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ በጎርጎሮርሳዊው 1978 ዓ. ም. በተከበረው 11ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን ባስተላለፉት መልዕክት የጤና ባለሞያዎች ዶችተሮች ጥበበኞች፣ ደፋሮች እና ደጎች፣ ለተጠሩበት የአገልግሎት ዘርፍ ታማኞች፣ ሳይንስን እና የሕክምና ስነ ጥበብን ጥሪያቸው እና ሙያቸው አድርገዋል ማለታቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል። በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ. ም. ለስፔን እና ለላቲን አሜርካ የሐኪሞች ማሕበር አባላት ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የአንድ የሕክምና ዶክተር ማንነት እና ታታሪነት የሚለካው ባካበተው ዕውቀት እና ችሎታ ብቻ ሳይሆን ከሁሉ አስቀድሞ በአካልና በመንፈስ ለሚሠቃዩ ሰዎች በሚያሳዩት የርህራሄ እና የምሕረት ልብ እንደሆነ አስረድተው በስቃይ ላይ ለሚገኝ ታማሚ መራራት በራሱ ፈዋሽ መድሐኒት እንደሚሆን አስረድተው መራራት ማለት አዘኔታ መግለጽ ሳይሆን ሕመምን መጋራት እንደሆነ ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች መርጃ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ ኮሚሽን ገለጻ መሠረት በዓለማችን ውስጥ ባሁኑ ጊዜ ከሃያ በላይ አመጾች በመካሄድ ላይ መገኘታቸውን ገልጾ ከእነዚህም መካከል በየመን፣ ኢራቅ፣ ሶርያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ አፍጋኒስታን እና በዩክሬን እንደሆነ ጠቅሷል በዴሞክራቲክ ኮንጎ እና በመካከለኛው የአፍሪቃ ሪፓብሊክ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ዘላቂ አመጾች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልጿል። በርካታ የሰብዓዊ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች እንዳስታወቁት ሆስፒታሎች እና የጤና አገልግሎት መስጫ ማዕከላትም ቢሆኑ የጦርነት ጥቃት ስለሚሰነዘርባቸው አስተማማኝ ጸጥታ ያለባቸው ሥፍራዎች አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ሕብረት መሪ እና የቅዱስ ቁርባን የወጣቶች እንቅስቃሴ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፌድሪክ ፎርኖስ እንዳስገነዘቡት በአመጾች መካከል ጥቃት የሚደርስባቸው ንጹሃን ዜጎች መሆናቸውን ገልጸው በዚህ ወቅት የተጎጂዎችን ሕመም እና ስቃይ ለመቀንስ የጤና አገልግሎት ባለሞያዎች እርዳታ ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታን የሚመለከቱ  ሕጎች በሚጣሱበት ጊዜ የሕክምና ማለሞያዎችም የጦርነቱ ሰለባ ስለሚሆኑ በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል። “ደስ ይበላችሁ፣ ሐሴትንም አድርጉ” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት “ለሌሎች ደህንነት ሲሉ የራስን ሕይወት ለሞት አሳልፎ መስጠት ወደ ቅድስና የሚወስድ መንገድ ነው” ማለታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ንግግራቸውን በጥር 19 ቀን 2010 ዓ. ም. ለኢጣሊያ የቀይ መስቀል ማሕበር አባላት ባሰሙት ንግግር “መልካም ሳምራዊ ለቆሰለ ሰው የሚያደርግለትን የመጀመሪያ የሕክምና እርዳታን ሳይሰጥ ሊያልፍ አይችልም፣ አይፈርድበትምም፣ የሚያደርገውን የሕክምና እገዛን በማንኛውም ሥነ ምግባራዊ ሆነ በመንፈሳዊ አስተሳሰብ እንዲደናቅፍ አያደርግም” ማለታቸው ይታወሳል።

05 April 2019, 19:44