ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የሞሮኮ ቤተክህነት የወንድማማችነት ፍቅርን የሚያስድግ ይሁን”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከመጋቢት 21 እስከ መጋቢት 22 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በሰሜን አፍሪቃ አገር በሆነችው በሞሮኮ 28ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሞሮኮ በሚገኙት የቤተክህነት አባላት ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት ቤተክህነቱ በሞሮኮ ሕዝብ መካከል የወንድማማችነት ፍቅርን የሚያስድግ እንዲሆን አሳስበዋል። ከብጹዓን ጳጳሳት ከካህናት፣ ከገዳማዊያት እና ገዳማዊያን፣ ከአብያተክርስቲያናት ሕብረት ተወካዮች ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት እንዳስገነዘቡት ትክክለኛ ፍሬያማ የወንጌል ተልዕኮ የሚከናወነው ሰዎችን ከአንድ እምነት ወደ ሌላ እምነት እንዲሄዱ በመስበክ ሳይሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከሌሎች ጋር ለመኖር በምናደርገው ጥረት እንደሆነ አስረድተዋል።

ወደ ሞሮኮ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከማገባደዳቸው በፊት በራባት ከቴድራል ውስጥ ላገኟቸው የአብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ተወካዮች ባሳአሙት ንግግር እንዳስረዱት ትክክለኛው የወንጌል ተልዕኮ ትርጉም የሚገለጠው ከወንጌል ከሚመነቸው ብርሃን ነው ብለዋል። ከአንድ ካህን እና ከአንዲት እህት የቀረበላቸውን ምስክርነት ካዳመጡ በኋላ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ቅዱስነታቸው በሞሮኮ የሚገኝ የክርስቲያን ማሕበረሰብ በቁጥር ዝቅተኛ ቢሆንም በቁጥር እና በያዘው የቆዳ ስፋት ማነስ የተገደበ አይደለም ብለዋል።

የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር ማመሳሰል ይቻላል በማለት ከኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የቀረበውን ጥያቄ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በሞሮኮ ምድር የሚገኙትን ክርስቲያኖች ከምን ጋር ማመሳሰል ይቻላል ብለው፣ ሊመሰል የሚችለው ብዙ ሊጥን እንደሚያቦካ እርሾ ሊመሰል ይችላል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጠን እና የላከን በቁጥር እንድንበረክት ሳይሆን በሕዝቦች መካከል ተገኝተን እንደ ጥቂት እርሾ በመሆን ሌላውን በርካታውን ሕዝብ በጽድቅ፣ በወንድማማችነት ፍቅር እንድናገለግል እና በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ በሕብረት እንድንኖር ነው ብለዋል።

የወንጌል መዓዛ፣

ስለዚህ ፍሬያማ የሆነ እውነተኛ የወንጌል ተልዕኮ የቁጥር ብዛት ወይም የምንይዘው የመሬት የቆዳ ስፋት ሳይሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለን ግንኙነት የሚገለጽ ነው ብለዋል። እውነተኛ የወንጌል ተልዕኮ ፍሬ የሚገለጠው ሰዎችን ከአንድ እምነት ወደ ሌላ እምነት እንዲኮበልሉ በማድረግ ሳይሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከሌሎች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በሚኖረን የግንኙነት እና የአካሄድ ዓይነት ነው ብለው ዋናው የቁጥር ማነስ ሳይሆን ለሌሎች ምን ትርጉም በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ማወቅ ነው ብለው (በማቴ. ምዕ. 5፤13 – 15) ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፣ ነገር ግን ጨው ጣዕሙን ካጣ እንዴት ጣዕሙን መልሶ ሊያገኝ ይችላል፣ ወደ ውጭ ከመጣል እና በሰው እግር ከመረገጥ በቀር ከእንግዲህ ወዲያ ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፣ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ለትሰወረይቻላትም። መብራት አብርቶ እንቅብ የሚደፋበት ማንም የለም፣ ይልቅስ በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲበራ በሚታይበት በከፍተኛ ቦታ ላይ ያደርገዋል። የሚለውን አስታውሰዋል።

ክርስቲያን መሆን ማለት ሌላውን ማቅረብ ማለት ነው፣

በሞሮኮ ከሚገኙት የቤተክህነት ወገኖች ጋር ቆይታን ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቤተክህነቱ በምዕመናኖች ቁጥር ማነስ እና በስልጣን ውስንነት መጨነቅ እንድማያስፈልግ አሳስበው አገልግሎት የሚለካው በየትም ሥፍራ ቢገኙ በቦታው ለሚገኙት ሕዝቦች በሚያበረክቱት አገልግሎት እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ያስፈልጋል፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ “Ecclesiam Suam” ሲተረጎም “የእናንተ ቤተ ክርስቲያን”     ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው “ቤተክርስቲያ ከዓለም ጋር ውይይት ስታደርግ የምትገኝበትንም ዘመን ያገናዘበች መሆን ያስፈልጋል” ማለታቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰው ይህ ማለት ደግሞ የተከታዮችን ቁጥር ለማሳደግ ብቻ የሚደረገውን የዘመናችንን ሩጫ መምሰል የለበትም ብለው ቤተክርስቲያን መከተል ያለባት ጌታዋ እና መምህሯ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር በምታድረገው ውይይት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። አንድ ክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ ከእያንዳንዱ ሰው ጋር እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ውይይትን የሚያደርግ ሕያው ቅዱሳት ምስጢራት መሆንን መማር እንደሚስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበዋል። ይህ ውይይትም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በየዋህነት እና በልበ ትሑትነት መከናወን ያስፈልጋል ብለዋል። በሰዎች መካከል የሚደረግ ውይይት ነጻነታቸውን የሚያከብር እና ገደብ የሌለውን ፍቅር በማሳየት የሚከናወን መሆን እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
01 April 2019, 17:32