ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የተጋነነ የእጅ ስልክ አጠቃቀም ጎጂ ሱስ እንዳሆን አሳሰቡ።

በሮም ከተማ የሚገኝ የቪስኮንቲ ሁለተኛ ደርጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በጳውሎስ ስድስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተቀብለው ንግግር ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለተማሪዎቹ እንደገለጹት፣ እውቀትን መቅሰም የሚቻለው ነጻነት ሲኖር ነው ብለው ያለ ነጻነት መልካም ሕይወትንም መኖር እንደማይችል አስታወቁ። ተማሪዎቹ የእጅ ስልኮቻቸውን ያለ ገደብ ከመጠቀም የተነሳ ከሰዎች ጋር ሊኖር የሚገባው የዓይን ለዓይን ግንኙነት እንዳይቀንስ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እና በምጣኔ ሐብት የኖቬል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ፍራንኮ ሞዲሊያኒ ያስተማሩበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ እውቀትን እና መልካም ባሕልን ለማሳደግ ያላቸውን ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለተቀበሏቸው ተማርዎች እንዳስረዱት ተማሪዎቹ የአንደነትን፣ የመከባበርን፣ ከልዩ ልዩ ባሕሎች ጋር ውይይቶችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ነጻነት እና የወደ ፊት ብሩሕ ተስፋ ሊኖር ይገባል፣

የወንድማማችነት ፍቅር ሊኖር ይገባል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህ የወንድማማችነት ፍቅር በነጻነት፣ በእውነት፣ በፍትህ እና በተለይም በሕብረት ሆነው ድሆችን እና ደካሞችን በመርዳት ላይ የተመሠረተ ይሁን ብለው በማሕበራዊ ሕይወት መካከል ፍትህ የሚጎድል ከሆነ ጥላቻ ሊስፋፋ ይችላል ብለዋል።

"ሰዎች ነጻነትን የሚነፈጉ ከሆነ እውቀትን መቅሰም አይችሉም፣ መልካም የወደ ፊት ሕይወትም ሊኖራቸው አይችልም። እውነትን ለማግኘት ተገድደን ሳይሆነ ከልብ የሚመነጭ እውነተኛ ፍላጎት ሊኖር ይገባል። በግድ የሚደረግ የእውነት ፍለጋ እውነትን የማግኘት ችሎታችንን በማስወገድ የወደ ፊት ተስፋ እንዲጨልም ያደርጋል። ፍትህን ለማሳደግ የማንጥር ከሆነ የጥቂት ሰዎች ጥቅም ብቻ የሚያስከብር አገርን እንገንባለን"።     

በዝምታ እና እርስ በእርስ በመገናኘት፣

ተማሪዎቹ ሂሊናቸው ምን እንደሚል ማዳመጥ ያስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በነፋስ እንደሚነጠቅ ወረቀት መሆን እንደሌለባቸው አሳስበዋል። ተማሪዎቹ ዝምታን መፍራት እንደሌለባቸው ያስረዱት ቅዱስነታቸው በውስጣዊ ዝምታ በመታገዝ ሕሊናችን የሚናገረውን በትክክል ማዳመጥ ይቻላል ብለው ከራስ ወዳድነት የጸዳ ድምጽን ለይቶ ማወቅ የሚቻለው እውነተኛ ሕሊና ሲኖር ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ተማሪዎቹ ከእጅ ስልኮቻቸው እና ከሌሎች ጎጂ ሱሶች መራቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል። የእጅ ስልክ የተፈጠረው ሰዎች እርስ በእርስ መገናኘት እንዲችሉ ለማድረግ እንጂ እንደ አደንዛዥ ዕፅ ሱስ መሆን የለበትም ብለዋል። ሱስ የሚሆን ከሆነ በሰዎች መካከል የሚደረገው ግንኙነት ፍሬያማ ሊሆን እንደማይችል ገልጸው ሕይወት የተሰጠን በውስጣችን ብቻ እንድንነጋገር ሳይሆን ከሌሎች ሰዎች ጋርም እንድንነጋገር ነው ብለዋል።     

"የተቀሳቃሽ ስልክ ጥቅም ከፍተኛ ነው። የዘመናችን መልካም የቴክኖሎጂ ውጤት ነው። ሁላችንም በአግባቡ መጠቀም ከቻልንበት መልካም ይሆናል። ነገር ግን ለዚህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ የምንገዛ ከሆነ ነጻነትን እናጣለን። ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች እርስ በእርስ እንድንገናኝ የሚያስችሉን ጠቃሚ የመግልገያ መሣሪያዎች ናቸው። ነገር ግን በእነዚህ የመገናኛ መሣሪያዎች አጠቃቀም ከገደብ አልፈው ሱስ የሚሆኑብን ከሆነ ከሰዎች ጋር የምናደረገው ግንኙነት ትርጉም ሊያጣ ይችላል። ሕይወት የተሰጠን ከሌሎች ጋር ፍሬያማ የሆኑ ግንኙነቶችን ማድረግ እንድንችል ነው"።           

ሌሎችን ማፍቀር መቻል ያስፈልጋል፣

ትክክለኛነት እና ታማኝነት ሁለት የአኗኗር ዜይቤዎች እንደሆኑ ለተማሪዎቹ ያስረዱት ቅዱስነታቸው ፍቅርን ለሰዎች ስንገልጽ ከአንገት በላይ ሳይሆን ከሙሉ ልብ መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል። ፍቅር በታማኝነት ላይ የተመሠረተ ዘላቂነት ያለው ሊሆን እንደሚገባ አሳስበው ፍቅር የዋዛ መሆን የለበትም ብለዋል። ፍቅር ከእግዚአብሔር ስጦታዎች መካከል የላቀ እንደሆነ አስረድተው ማፍቀር ማለት ልብን ሰፊ ማድረግ ነው ብለዋል። ፍቅር በባል እና በሚስት ወይም በሁለቱ የትዳር ጓደኛሞች መካከል የሚፈጠር ጠንካራ የወዳጅነት ስሜት ብቻ እንዳልሆነ ገልጸው ተጨባጭ ፍቅር የሚገለጠው ሌሎችንም ለመርዳት በተለይም የተቸገሩትን እና አቅመ ደካማ የሆኑትን ለመርዳት ካለን ፍላጎት የሚመነጭ ነው ብለዋል። በፍቅር ተነሳስተን ለሌሎች የምናደርገው እገዛ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያድግ ያስፈልጋል ብለው በዚህ መልክ ፍቅርን ማሳደግ መፍራት እንደሌለባቸው ተማሪዎችን አሳስበዋል።  

ቸርነትን በማሳየት ማሸነፍ ያስፈልጋል፣

በወጣቶች መካከል እየተንጸባረቀ ያለውን የጉልበተኝነት ስሜት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በኢጣሊያ ውስጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በስፋት እንደሚከናወን ገልጸው ተማሪዎች በእነዚህ አገልግሎቶች ውስጥ እንዲሳተፉ ጥሪያቸውን አቅርበውላቸዋል። ለተማሪዎቹ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳናቸው እንዳስገነዘቡት ተማሪዎች ሕልማቸው እንዳይቋረጥ፣ ለሁሉም ሰው የተሻለ ዓለምን እንዲመኙ አሳስበዋል። በተጨማሪም  በመካከላቸው የሚያደርጉት ግንኙነቶች ሚዛናዊ እንዲሆን፣ ለሂሊናቸው እና ለውስጣዊ አስተሳሰባቸው ጥንቃቄን እንዲያደርጉ፣ የወደፊት ሕይወታቸውን ለማስተካከል፣ ፍትሃዊ እና ያማረ ዓለምን ለመገንባት በርትተው መሥራት እንዳለባቸው አደራ ብለዋል።            

15 April 2019, 15:00