ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ “ክርስቶስ ሕያው ነው” (Christus vivit ) በሚል አርእስት ያፋ ያደርጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ “ክርስቶስ ሕያው ነው” (Christus vivit ) በሚል አርእስት ያፋ ያደርጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን 

“ክርስቶስ ሕያው ነው” (Christus vivit )

ክፍል ሁለት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በስድስት አመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ውስጥ ከዚህ ቀደም ሦስት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖችን ለንባብ ማብቃታቸው የሚታወቅ ሲሆን እነዚህም በላቲን ቋንቋ Evangelii Gaudium”  በአማሪኛ ሲተረጎም “በወንጌል የሚገኝ ደስታ”  በሚል አርእስት እ.አ.አ በኅዳር 24/2013 ዓ.ም ለንባብ ያበቁት ቃለ ምዕዳን በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አሁንም በላቲን ቋንቋ Amoris Laetitia”  በአማሪኛው በግርድፉ ሲተረጎም “የፍቅር ሐሴት” በሚል አርእስት እ.አ.አ. በመጋቢት 19/2016 ዓ.ም ለንባብ ያበቁት ቃለ ምዕዳን ሲሆን ይህ ቃለ ምዕዳን በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር፣ በቤተሰብ ውስጥ ስለሚታዩ ተግዳሮቶች፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለቤተሰብ ማድረግ ሰለሚጠበቅባቸው ሐዋርያዊ እንክብካቤ የሚያወሳ ድህረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ለንባብ ማብቃታቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእነዚህ ስድስት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ውስጥ በሦስተኛ ደረጃ ለንባብ ያበቁት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እ.አ.አ በመጋቢት 19/2018 ዓ.ም በላቲን ቋንቋ “Gaudete et Esultate” በአማርኛው “ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ” በሚል አርእስት ለንባብ ያበቁት ቃለ ምዕዳን ሲሆን ይህ ቃለ ምዕዳን “በአሁኑ ዓለማችን ውስት የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ወደ ቅድስና መንገድ እንዲመለሱ የሚጋብዝ ጥሪ” የተካተተበት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ሲሆን በአሁኑ ዘመን በሚገኘው ዓለማችን ውስጥ በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን፣ የተለያዩ የሕይወት ተግዳሮቶች እየገጠሙዋችሁ የምትገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ እንዲሁም አሁን ባለው ዓለማችን ውስጥ ያለውን መልካም እድል መጠቀም ያልቻላችሁ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ልጆቻችሁን በታላቅ ፍቅር ተንከባክባችሁ እያስደጋችሁ የምትገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ለቤተሰባችሁ የሚሆን እንጀራ በእየለቱ ለማግኘት የምትኳትኑ፣ የምትለፉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁ የምትሰሩ የማኅበረስብ ክፍሎች፣ በእድሜያችሁ ዘመኑ ሁሉ ለራሳችሁ፣ ለቤተሰባችሁ ለአገራችሁ፣ በአጠቃላይ ለማኅበረሰቡ መልካም የሆነ ተግባር ያከናወናችሁ አረጋዊያን ሁላችሁ “ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራነስኮስ በአራተኛ ደረጃ ለንባብ ያበቁት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ደግሞ ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 17/2011 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን ሲካሄድ የነበረው 15ኛ የብጹዕን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባሄ ተካሂዶ ማለፉ የሚታወቅ ሲሆን የዚህ ጉባሄ ማጠቃለያ ሐሳብ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርእስት የተዘጋጀ እና በመጋቢት 16/2011 ዓ. ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ተፈርሞ እንዲታተም ፈቃድ የተሰጠው እና በዚህም መሰረት በመጋቢት 24/2011 ዓ. ም. ለንባብ ያበቁት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ቅዱስነታቸው በርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ለንባብ ያበቁት አራተኛው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ነው። የዚህን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን የምዕራፍ ሁለት አጠቃላይ ይዘት በአጭሩ እንደ ሚከተለው እናቀርብላችኋለን፣ ተከታተሉን።

ምዕራፍ ሁለት

ኢየሱስ ሁሌም ወጣት ነው

ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ “ኢየሱስ ሁሌም ቢሆን ወጣት ነው” በሚል አርእስት የቀረበ ሲሆን በውስጡም ከአንቀጽ 22-63 አቅፎ የያዘ ነው። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንደ ገለጹት ኢየሱስ በቅዱስ ወንጌል ታሪክ ውስጥ “ታዳጊ ወጣት እንደ ነበረ፣ ከቤተሰቦች ጋር ወደ ናዝሬት በሄደበት ወቅት ጥፍቶ እንደ ነበረ እና ከዚያም በኋላ በቤተ መቅደስ ውስጥ እንደ ተገኘ” ያስረዳል። እርሱ እንደ ማነኛውም ታዳጊ ወጣት የኖረ እና በዚያም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ከቤተሰቡ እና ከሕዝቡ ጋር እንደ ማነኛውም ሰው ግንኙነት እንደ ነበረው ከቅዱስ ወንጌል ለመረዳት እንችላለን። ይህ ግንዛቤ በወጣቶች ሕይወት ውስጥ ሊኖር ይገባል። ወጣቶችን ከቤተሰቦቻቸው እና ከማህበረሰቡ የሚለይ ወይም ወጣቶችን ያላሳተፈ ሕቅዶች ማውጣት እንደ ማይገባ ይገልጻል። በአንጻሩ ደግሞ ማነኛውም ዓይነት እቅድ ወጣቶችን ያሳተፈ፣ ወጣቶችን የሚረዳ፣ እነርሱን በተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት እና ተልዕኮዎች ውስጥ ማሳተፍ ተገቢ ነው የሚሉ አንቀጾች ይገኙበታል። 

ቤተ ክርስቲያን የወጣቶች መሆኑዋን ለመግለጽ በማሰብ “ቤተ ክርስቲያን እያረጀች እንድትሄድ ከሚያደርጉዋት ሁኔታዎች እግዚኣብሔር ቤተ ክርስቲያንን ነጻ ያወጣ ዘንድ እንጸልይ” በማለት የሚገልጹ  አንቀጾች የተካተቱበት ምዕራፍ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ወጣት እንደሆነች አድርጎ በማሰብ ዓለም የሚያቀርብላትን ነገሮችን ሁሉ እሺ ብላ ትቀበላለች ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ እንደ ሆነ የሚተነትኑ አንቀጾች የሚገኙበት ምዕራፍ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን በእግዚኣብሔር ቃል እና በቅዱስ ቁርባን፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እየተመራች እና ወጣት እየሆነች መሄድ ይኖርባታል የሚል ሐሳብ የሚንጸባረቅበት ምዕራፍ ነው።

ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስን ምስል “ውብ እና ብቃት ባለው መልኩ” ማንጸባረቅ እንደ ሚገባት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዚህ በቅርቡ ይፋ ባደረጉት “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርእስት ይፋ ባደረጉት ቃለ ምዕዳን ውስጥ የገለጹ ሲሆን ከሁሉም በላይ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን የራሱዋን ገጽታ ሳይሆን ነገር ግን ኢየሱስን ማንጸባረቅ ይኖርባታል በማለት የገለጹባቸው በርካታ አንቀጾች ይገኙበታል። ይህ ማለት ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ተጨባጭ በሆነ መልኩ ለውጥ ያስፈልጋታል የሚለውን ሐሳብ በትህትና መቀበል ማለት ነው በማለት ማብራሪያ የሚሰጡ ሐሳቦች ተካተውበታል።

“ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርእስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅርቡ ያፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በአሁኑ ወቅት ወጣቶች ከቤተ ክርስቲያን እየራቁ እንደ ሚገኙ የሚገልጹ አንቀጾች የተካተቱበት ሲሆን ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት “በከባድ እና በቀላሉ ልንገነዘበው በምንችለው ምክንያቶች እንደ ሆነ ገልጸው እነዚህም በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች እና የቤተ ክርስቲያን ኢኮኖሚ ከማስተዳደር ጋር በተያያዘ መልኩ በሚታዩ ጉድለቶች የተነሳ መሆኑን የሚገልጹ አንቀጾች የሚገኙበት ምዕራፍ ሲሆን እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ ለወጣቶች ከፍተኛ እንቅፋት በመሆናቸው የተነሳ ወጣቶች ከቤተ ክርስቲያን እንዲርቁ እንዳደረጋቸው ይገልጻል ምዕራፍ ሁለት።

በዚህ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ በምዕራፍ ሁለት ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንደ ገለጹት “ማርያም ከናዝሬት ከተማ የተገኘች ወጣት ሴት እንደ ሆነች” አድርገው ያቀረቡ ሲሆን እርሷ “እንዳልከኝ ይሁንልኝ” በማለቱዋ የተነሳ ሕይወቱዋ አደጋ ላይ እንደ ሚወድቅ ብታውቅም ቅሉ፣ ነገር ግን ሁሉንም ነገር በጸጋ በመቀበል ለግል ሕይወቷ ሳትጨነቅ የእግዚኣብሔርን ቃል ኪዳን ጠባቂ መሆኑዋን እንዳስመሰከረች ይገልጻል። በዚህም የተነሳ “እያንዳንዳችሁ የዚያ ቃል ኪዳን ተሸካሚዎች እንድትሆኑ እጠይቃችኋለሁ” የሚል አንቀጽ የተካተተበት ምዕራፍ ሲሆን በምንም ዓይነት ሁኔታ እግዚኣብሔር ለሚያቀርብልን ጥሪ “አንብየው” ማለት አይገባንም ብለዋል። በቤተ ክርስቲያን ልብ ውስጥ በጣም ብዙ የሚባሉ ቅዱሳን እንደ ሚገኙ የሚገልጹ አንቀጾች የተካተቱበት ምዕራፍ ሲሆን ለምሳሌም ቅዱስ ሰባስቲያን፣ የአዚዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስን የመሳሰሉ በርካታ ወጣት ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን ልብ ውስጥ እንደ ሚገኙ የሚገልጹ አንቀጾችም የተካተቱበት ምዕራፍ ነው። በአጠቅላይ ምዕራፍ ሁለት ኢየሱስ ራሱ ወጣት እንደ ነበረ፣ ከእርሱ የወጣትነት ሕይወት የምንማራቸው ነገሮች እንዳሉ፣ ቤተ ክርስቲያን ወጣት መሆን እንደ ሚኖርባት፣ ቤተ ክርስቲያን ለለውጥ ዝግጁ መሆን እንደ ሚገባት፣ በዘመናችን እየታዩ ለሚገኙ ምልክቶች ቤተ ክርስቲያን ትኩረት መስጠት እንደ ሚገባት፣ ማርያም እራሷ ከናዝሬት ከተማ የተገኘች ወጣት መሆኑዋን የሚያወሳ እና እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ልብ ውስጥ በጣም በርካታ ወጣት ቅዱሳን እንደ ሚገኙ የሚያወሱ አርእስቶች የተካተቱበት ምዕራፍ ነው።

 

10 April 2019, 16:01