ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ በዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ወጣቶችን ሰላም ባሉበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ በዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ወጣቶችን ሰላም ባሉበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ፦ “ወደ እውነተኛ የደስታ የሚመሩን መንገዶች”

መጋቢት 11/2011 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ የደስታ ቀን ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። እውነተኛ ደስታን በተመለከተ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በስድስት አመታት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳና ዘመናቸው ውስጥ በጻፏዋቸው በርካታ ሐዋርያዊ መልእክቶች እና ቃለ ምዕዳኖች ውስጥ እውነተኛ ደስታን በተመለከተ በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ደስታን በተመለከተ ከጻፉዋቸው ሐዋርያዊ መልእክቶች እና ቃለ ምዕዳናቾ ውስጥ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን እንመለከታለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በየተኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ “እውነተኛ ደስታን ፍለጋ” መኳተናቸው የተለመደ ነገር መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ምክንያቱንም አያይዘው ሲገልጹ “እግዚአብሔር ራሱ በእያንዳንዱ ወንድና ሴት ልብ ውስጥ" ደስታን እና ሙልአትን የመሻት ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት ስላሳደረባቸው መሆኑን መገለጻቸው ይታወሳል። “የእያንዳንዳችን ልብ ሳያርፍ ቀጣይነት ባለው መልኩ በመቃተት እና ያለማቋረጥ ልባችን ጥሙን ለማርካት የሚያስችለውን መልካም ነገር በመፈለግ ላይ ይገኛል” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን የእኛ ፈጣሪ፣ የእርሱን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ውበት፣ እውነት . . . ወዘተ በእኛ ሰብዓዊ ማንነታችን ውስጥ ያኖርልን ዘንድ፣ በዓይናችን የማይታይ ከፍተኛ የሆነ ጉጉት በሕይወታችን ውስጥ እንደ ሚገኝ በተለያየ ወቅት ባደርጉዋቸው ስብከቶች እና በጻፉዋቸው ሐዋርያዊ መልእክቶች እና ቃለ ምዕዳኖች መግለጻቸው ያታወሳል። ከእነዚህም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “የእውነተኛ ደስታ ምንጮች”  ካሉዋቸው ውስጥ ዐሥሩን እንደ ሚከተለው እንመለከታለን።

1.     እውነተኛ ደስታን የምናገኘው ከራሳችን ይልቅ በቅድሚያ ለሌሎች ሰዎች ትኩረት ስንሰጥ ነው!

ደስተኛ ለመሆን ከፈለግን ይህንን እውነተኛ የሆነ ደስታ ለማግኘት የምናደርገውን ጉዞ መጀመር የሚገባን ከራስ ወዳድነት በመላቀቅ ለሌሎች ማሰብ በመጀመር ሊሆን ይገባል። የቤተ ክርስቲያን አባቶች በተደጋጋሚ እንደ ሚሉት “ሐዘንተኛ የምንሆነው ለራሳችን ብቻ ማሰብ ስንጀምር ነው” ይሉ እንደ ነበረ ይታወሳል። ይህንን በተመለከተ ደግሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንዲህ ይሉ ነበር፦ “የግላችንን ጥቅማጥቅሞች ለማስከበር ብቻ በማሰብ ሕይወታችንን ለሌሎች ዝግ የምናደርግ ከሆነ በሕይወታችን ውስጥ ለሌሎች ሰዎች ቦታ የማንሰጥ ከሆንን፣ ሐዘንተኞች እንሆናለን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የደስታ እና የፍቅር መንፈስ ከእኛ ወዲያ ይርቃል” ማለታቸው ይታወሳል። በእርግጥ “በራሳችን ጥረት ብቻ ደስተኛ ለመሆን አንችልም!” በማለት አዘውትረው የሚናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ደስተኛ ለመሆን ከፈለግን ለጋሾች መሆን ይገባናል” ብለው ምክንያቱም "እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጡትን ይወዳል" (2ቆሮ 9፡7) በማለት ጨምረው መናገራቸውም ይታወሳል።

እውነተኛ ደስታን በሕይወታችን ለማጣጣም ከፈለግን፣ ራሳችንን በራሳችን ዘግተን፣ በራሳችን ዙሪያ ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ መቆጠብ እንደ ሚገባን ጨምረው መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ራሳችን በራሳችን ሙሉ እንደ ሆንን አድርገን በመቁጠር፣ በራሳችን ብቻ መተማመንን በማቆም ከሌሎች ወንድሞቻችን ጋር ያለንን የወንድማማችነት መንፈስ ማጠናከር ይኖርብናል ማለታቸውም ይታወሳል። ሕይወታችን ትርጉም ሊኖራት የሚችለው ለሌሎች ሰዎች ደስታን በመመኘት እና "ለሌሎች ሰዎች መልካም ነገርን በመመኘት” እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው “አንድ ሰው የተሻለ ሕይወት እንዲኖረው መርዳት ከቻልኩኝ በሕይወቴ ውስጥ የእግዚኣብሔር ስጦታ የሆነውን እውነተኛ ደስታ እውን ለማድረግ በቂ የሆነ ምክንያት ነው” ( Evageli Gaudium ቁ. 182) ማለታቸው ይታወሳል።

2.     የጭንቀት ስሜትን ማስወገድ

ብዙን ጊዜ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጽሐፈ ሲራክ ውስጥ “ልጄ ሆይ የሚቻልህን ያህል ሰውነትህን አዘጋጅ […] በደስታ ጊዜ አትታጣ” (መ. ሲራክ 14.11,14) የሚለውን የመጸሕፍ ቅዱስ ክፍል መጥቀስ ይቀናቸዋል። በተጨማሪም “እግዚአብሔር በምድር ላይ የልጆቹን ደኅንነት እና ደስታ ይሻል፣ ምንም እንኳን ወደ ሰማይ ለዘለአለማዊ እርካታ ቢጠራንም፣ እርሱ ሁሉን ነገር በዚህ ምድር ላይ አስተካክሎ የፈጠረበት ምክንያት የሰው ልጆች ሁሉ በደስታ እንዲኖሩ ነው” ማለታቸውም ይታወሳል።

3.     እውነተኛ ደስታን የሚሰጠን ስልጣን፣ ስኬት ወይም ገንዘብ ሳይሆን ፍቅር ነው!

“እውነተኛ ደስታን የሚሰጠን ስልጣን፣ ስኬት ወይም ገንዘብ ሳይሆን ነገር ግን ፍቅር ነው!” በማለት በተደጋጋሚ የሚናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “እውነተኛ ደስታን እንደ አንድ እቃ ከገበያ መዕከል የምንገዛው ነገር አይደለም” በማለት በአጽኖት መናገራቸው ይታወሳል። ስኬት እና ጊዜያዊ ደስታ ራስ ወዳድ በሆነ መንገድ የምንፈልግ ከሆነ እና እነዚህንም ነገሮች እንደ ጣዖት አድርገን በምናመልክበት ወቅት ከእውነተኛ ደስታ ይልቅ የመርከስ ስሜት ውስጥ እንገባለን፣ የተሳሳተ የማምለኪያ ስሜት ሊኖረን ይችላል፣ በመጨረሻም የእነዚህ ነገሮች ባሪያዎች እንሆናለን፣ ፈጽሞ እርካታ አይኖረንም የበለጠ እና ተጨማሪ ነገሮችን እንድንፈልግ ይገፋፋናል ይህም ደስታችንን እንድናጣ ያደርገናል” ማለታቸውም ይታወሳል።

“እውነተኛ ደስታ ለአፍታ ያህል ብቅ ብሎ ከዚያም በኋላ በኖ የሚጠፋ ነገር አይደለም: ነገር ግን ሌላ ነገር ነው! እውነተኛ ደስታ የሚገኘው እንዲሁ በከንቱ ከምናጋብሳቸው ቁሳቁሶች ምክንያት አይደለም፣ በፍጹም እንዲህ አይደለም! እውነተኛ ደስታ የሚገኘው በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ ከሌሎች ጋር ግንኙነት በመመስረት፣ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘት፣ ሌሎች ሰዎች ስለተቀበሉን በመደሰት፣ የተሰጠንን ፍቅር በመቀበል፣ እኛም የተሰጠንን ፍቅር ተቀብለን መልሰን ለሌሎች በመስጠት፣ ይህንንም የምናደርገው ጊዜያዊ የሆኑ ፍላጎቶቻችንን ለሟሟላት ብለን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሌላኛው ሰው ሰው በመሆኑ የተነሳ መሆኑን በማመን” ከሰዎች ጋር ግንኙነት በምንመሰርትበት ወቅት እውነተኛ ደስታን እናገኛለን” ማለታቸው ይታወሳል።

4.     ደስተኛ የሆነ መንፈስ እንዲኖረን በማድረግ

“እውነተኛ ደስታን መጎናጸፍ የምንችለው በሕይወት ሂደት ውስጥ ደስተኛ  የሆነ መንፈስ እንዲኖረን በማድረግ ሊሆን እንደ ሚገባ”  መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን የሚያስቁ እና የሚያስደስቱ ነገሮችን በማውራት እና በመሳቅ፣ በማሳቅ ከሌሎች እና ከራሳችን ጋር ያለን ግንኙነት እጅግ በጣም ሰብአዊ ስብዕናን በአማከለ መልኩ “ለጸጋ ቅርብ" የሆነ አመለካከት በማዳበር እውነተኛ ደስታን ማግኘት ይቻላል። በአጠቃላይ “እውነተኛ ደስታ የሚመነጨው እና የሚወለደው ከመንፈስ ቅዱስ ነው” ማለታቸውም ይታወሳል።

5.     አመስጋኝ መሆን!

እውነተኛ ደስታን በየቀኑ በምንቀበላቸው የጸጋ ስጦታዎች በመደሰት እና በማመስገን እውነተኛ ደስታን መጎናጸፍ እንደ ምንችል በተደጋጋሚ የገለጹት ቅዱስነታቸው በቀላሉ የሕይወታችንን ውበት በመመልከት እና በእለታዊ ኑሮዋችን ውስጥ በምናገኛው ትልቅም ይሁን ትንንሽ ነገሮች ተቀብለን በማመስገን ደስታን ማግኘት እንደ ሚቻል ቅዱስነታቸው መናገራቸው ይታወሳል። የአዚዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ “በእየለቱ በሚያገኘው ቁራሽ ዳቦ ወይም ደግሞ የራሱን ፊት በመመልከት ብቻ እግዚኣብሔር እንዲህ አድርጎ ስለፈጠረው ፈጣሪውን በደስታ ያመሰግን እንደ ነበረ” በማስታወስ እኛም ባለን እና በተሰጠን ነገር አመስጋኞች በምንሆንበት ጊዜ ሁሉ እውነተኛ ደስታን ለማግኘት እንችላለን ማለታቸው ይታወሳል።

6.     ይቅርታ ማደረግ እና ይቅርታን መጠየቅ እንዳለብን በማወቅ!

እውነተኛ ደስታን ማግኘት ከፈለግን ደግሞ ይቅርታ ማደረግ እና ይቅርታን መጠየቅ እንዳለብን ማወቅ ተገቢ መሆኑን በተደጋጋሚ የገለጹት ቅዱስነታቸው በታላቅ ቁጣ እና ቂም በተሞላ ልብ ውስጥ እውነተኛ ደስታ ምንም ዓይነት ስፍራ እንደ ሌለው ቅዱስነታቸው በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል። “ይቅርታ ማደረግ የማይችል ሰው ከሁሉም በላይ በቅድሚያ የሚጎዳው ራሱን ነው”። ጥላቻ ደግሞ ሐዘንን ያስከትላል። እኛ ይቅርታን እንድናደርግ የሚገፋፋን ነገር “የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፥ እልል በል፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ በፍጹም ልብሽ ሐሴት አድርጊ ደስም ይበልሽ ምክንያቱም እግዚአብሔር የተፈረደብሽን ፍርድ አስወግዱዋልና” (ት. ሰፎኒያስ 3፡14-15) ላይ እንደ ተጠቀሰው እኛ ራሳችን በእግዚኣብሔር ይቅር መባላችንን በመገንዘብ ሊሆን ይገባል ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን ይህም ማለት ደግሞ “እግዚኣብሔር እኛን ይቅር ብሎናል፣ ኃጢአቶቻችንን ረስቶልናል” ማለት በመሆኑ የተነሳ እኛም ለሌሎች ይቅርታን ማደርግ የገባናል ማለታቸውም ይታወሳል።

7.     ሥራዎቻችንን በአግባቡ ማከናወን እና የእረፍት ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም!

እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ከሚረዱን ነገሮች መካከል የተሰጡንን ኃላፊነቶች፣ ሥራዎች በአግባቡ ማከናወን እና የእረፍት ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም የሚሉት እንደ ሚገኙባቸው በተደጋጋሚ የገለጹት ቅዱስነታቸው በሥራ ቦታ ከሌሎች ጋር በሰላም የመሥራት ባህሪይ በማዳበር የሥራ ቦታችንን የወንድማማችነት እና የመተጋገዣ ቦታ በምናደርግበት ወቅት ደስታን ማግኘት እንችላለን ማለታቸው ይታወሳል። በተጨማሪም የእረፍት ጊዜያችንን በአግባቡ በመጠቀም ለታለመለት ዓላማ በማዋል እውነተኛ ደስታ እንድናገኝ የሚረዳን እንደ ሆነም ጨምረው መናገራቸው ይታወሳል።

8.     ጸሎት እና የወንድማማችነት መንፈስ!

እውነተኛ ደስታ እንድናገኝ ከሚያደርጉን ነገሮች መካከል በቀዳሚነት የሚገለጹት ጸሎት መጸለይ እና የወንድማማችነትን መንፈስ ማዳበር የሚሉት እንደ ሚገኙበት በተደጋጋሚ በተለያዩ አጋጣሚዎች የገለጹት ቅዱነታቸው ምክንያቱም እውነተኛ ደስታን ለማግኘት የምናደርገው ጉዞ በተለያዩ እንቅፋቶች፣ ተግዳሮቶች፣ ፈተናዎች . . . ወዘተ የተሞላ በመሆኑ የተነሳ እነዚህን መሰናክሎች ለማለፍ ደግሞ ጸሎት አስፈላጊ መሆኑን አጽኖት ሰጥተው መናገራቸው ይታወሳል። የወንድማማችነት መንፈስን ማዳበር፣ በእየለቱ ከሰዎች ጋር በሰላም ለመኖር መሞከር፣ ሰዎችን በጥሞና ማዳመጥ . . . ወዘተ በሕይወታችን ውስጥ እውነተኛ ደስታ እንዲሰፍን የሚረዱን ነገሮች እንደ ሆኑ ቅዱስነታቸው በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።

9.     ሕይወታችንን በእግዚኣብሔር እጅ ውስጥ በአደራ ማስቀመጥ!

እውነተኛ ደስታ እንድናገኝ ከሚያደርጉን ነገሮች መካከል እጅግ በጣም አስፈላጊው ነገር ሕይወታችንን በእግዚኣብሔር እጅ ውስጥ በአደራ ማስቀመጥ እንደ ሆነ በተለያዩ አገጣሚዎች የተናገሩት ቅዱስነታቸው ምክንያቱም በሕይወት ሂደት ውስጥ መስቀል ስለሚያጋጥመን፣ ጨለማ የሆኑ መንገዶችን አቋርጠን መሄድ ስለሚኖርብን፣ እንድንደክም የሚያደርጉን ብዙ ነገሮች ስለሚያጋጥሙን በእነዚህ እና እነዚህን በመሳሰሉ ምክንያቶች በመነሳት ሕይወታችንን በእግዚኣብሔር እቅፍ ውስጥ በአደራ በማስቀመጥ ከእነዚህ ጊዜያዊ ተግዳሮቶች ነጻ እንድንሆን በማድረግ እውነተኛ ደስታን እንድንጎናጸፍ ያደርገናል ማለታቸው ይታወሳል።

10.                       ሰዎች እንደ ሚወዱን እና እንደ ሚፈልጉን መገንዘብ!

እውነተኛ ደስታን እንድንጎናጸፍ ከሚያደርጉን ተግባራት መካከል ሰዎች እንደ ሚወዱን እና እንደ ሚፈልጉን መገንዘብ እና ማወቅ በጣም አስፈላጊ እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው በተደጋጋሚ በተለያዩ አጋጣሚዎች መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን በዚህ ረገድ ደግሞ እውነተኛ ደስታ የሚመነጨው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በምናደርገው እለታዊ ግንኙነት እና እርሱ ሕይወቱን ለእኔ ሲል አሳልፎ እስከ መስጠት ድረስ እንደ ወደደኝ መገንዘብ በራሱ ደስታን የሚፈጥር ጉዳይ ነው ማለታቸውም ያታወሳል።

21 March 2019, 10:21