ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከኢጣሊያ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት ከክቡር አቶ ሴርጆ ማታረላ ጋር፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከኢጣሊያ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት ከክቡር አቶ ሴርጆ ማታረላ ጋር፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከኢጣሊያ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት የደስታ መግለጫ መልዕክት ደረሳቸው።

የኢጣሊያ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሴርጆ ማታረላ ቅዱስነታቸው በኢጣሊያ ውስጥ ወደ ፑሊያ፣ ቶስካና እና ሲሲሊ ክፍላተ ሀገራት ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ይበልጥ ድክመት የሚታይበትን የኢጣሊያ ሕዝብ በጠንካራ እና ዕለታዊ የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት በኩል ለማጽናናት ጥረት የተደረገበት እንደሆነ ገልጸው መልካም ውጤቶችም የታዩባቸው ናቸው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው የተመረጡበትን 6ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የኢጣሊያ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሴርጆ ማታረላ የእንኳን አደረሱ መልዕክታቸውን ልከዋል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን 266ኛው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው የተመረጡበትን 6ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በላኩት መልዕክታቸው በራሳቸው እና በመላው የኢጣሊያ ሕዝብ ስም ጤናን ተመኝተውላቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሰው ልጆች በሙሉ በማበርከት ላይ ለሚገኙት ሐዋርያዊ አገልግሎት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያሳለፏቸውን ከባድ የሐዋርያዊ የአገልግሎት ዓመታትን ያስታወሱት ፕሬዚደንት ሴርጆ ማታረላ፣ በዓለም ዙሪያ ካደረጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች መካከል የላቲን አሜርካ አገር በሆነችው በፓናማ ዘንድሮ በጥር ወር በተከናወነው 34ኛ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ መገኘታቸውን እና “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ፣ በአቡ ዳቢ ያደረጉትን ታሪካዊ ጉብኝት አስታውሰዋል። በእነዚህ ሁለቱ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ያስተላለፉትን የተስፋ፣ የሰላም እና የወንድማማችነት መልዕክታቸውን አስታውሰው በእነዚህ ሐዋርያዊ ጉኝቶች ወቅት ያስተላለፏቸው መልዕክቶች የሐይማኖት፣ የዘር እና የባሕል ልዩነት ሳይታይበት በሁሉ የማሕበረሰብ ዘንድ ሕሊናን በመቀስቀስ ውይይት እና መግባባት እንዲዳብር አድርገዋል ብለዋል።

የኢጣሊያ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሴርጆ ማታረላ በማከልም ቅዱስነታቸው በኢጣሊያ ውስጥ ወደ ፑሊያ፣ ቶስካና እና ሲሲሊ ክፍላተ ሀገራት ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ይበልጥ ድክመት የሚታይበትን የኢጣሊያ ሕዝብ በጠንካራ እና ዕለታዊ የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት በኩል ለማጽናናት ጥረት የተደረገበት እንደሆነ ገልጸው መልካም ውጤቶችም የታዩባቸው ናቸው ብለዋል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ የቅድስና እወጃ ክብረ በዓል ላይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር መገናኘታቸውን ያስታወሱት ክቡር ፕሬዚደንት ሴርጆ ማታረላ መላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን በበላይነት ሆነው የሚያበረክቱት ሐዋርያዊ አገልግሎት ቀጣይነት እንዲኖረው በማለት መልካም ልባዊ ምኞታቸውን በመልዕክታቸው ገልጸውላቸዋል።

19 March 2019, 18:27