ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢጣሊያ የሕጻናት ሕክምና አገልግሎት ፌዴሬሽን አባላትን ተቀብለው  ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢጣሊያ የሕጻናት ሕክምና አገልግሎት ፌዴሬሽን አባላትን ተቀብለው  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የጤና እንክብካቤ አገልግሎት ለሁሉም እኩል ይዳረስ”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ በኢጣሊያ የሕጻናት ሕክምና አገልግሎት ፌዴሬሽን አባላትን ተቀብለው ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። ከተቋቋመ 40 አመታትን ላስቆጠረው ፌዴሬሽኑ አባላትን ባደረጉት ንግግር የማሕበሩ አገልግሎት ልዩነትን ሳያድረግ ለሁሉም የማሕበረሰብ ክፍሎች እንዲዳረስ ሰብዓዊ መብትንም ያከበረ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ 

እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ልባዊ ሰላምታዬን አቀርባለሁ።  ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ላደረጉት ንግግር ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ማህበራችሁ ላለፉት አርባ አመታት ያህል በሕጻናት ሕክምና አገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩት፣ ከ 5.500 በላይ ለሚሆኑ ባለሞያዎች በሕጋዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ ድጋፍን በማድረግ በተጨማሪም የሞራል እና የሞያ ድጋፍ እየሰጠ መቆየቱ ይታወቃል። በሕጻናት ሕክምና አገልግሎት ላይ ለተሰማሩት ባለሞያዎች የምታደርጉት እገዛ ሃላፊነቸውን በሚገባ አውቀውት፣ ሊሰጥ የሚገባውን ሞያዊ አገልግሎት በጥንቃቄ እንዲያበረክቱ የሚያግዝ ነው።

ፌዴሬሽኑ በብሔራዊ ደረጃ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ለዜጎች በሙሉ ጤና ነክ የሆኑ አገልግሎቶችን እያበረከተ፣ የአገልግሎቱንም ጥራት ከጊዜ ወደ እያሳደገ፣ ከፖለቲካ ተቋማት እና ሕዝባዊ ድርጅቶች ጋር የተለያዩ ውሎችን በመግባት የታዳጊ ሕጻናትን ጤና ሲከታተል ቆይቷል።

አገልግሎታችሁን የምታበረክቱባቸው የዕድሜ ገደብ የሰው ልጅ በአካልም ሆነ በአእምሮ ፈጣን እድገት የሚያሳይበት የዕድሜ ገደብ ነው። አዲስ የተወለደን ሕጻን የሚደርስ የጤና ችግር ወይም የአሥር ዓመት ዕድሜ ታዳጊ ሕጻንን ለማከም የሚያስፈልገውን የሕክምና መሣሪያ አጠቃቀም ማወቅ፣ እንደዚሁም ከአካላዊ እና ከስነ ልቦና ጋር የተገናኘ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ አስቀድሞ ማወቅ ይቻላል።

ይህን የመሰለ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሠረታዊ የሞያ ብቃት እንዲኖር እና ዘላቂ የሞያ ማሻሻያ ስልጠናዎች ሊኖሩ ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ ለሕጻናት የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያግዙ ውይይቶች፣ ዓውደ ጥናቶች እና ጉባኤዎች ሊኖሩ ይገባል። በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ወደ ተመቻቸ የኑሮ ደረጃ እና ማሕበራዊ እድገት በደረስንበት ዘመን፣ ተፈጥሮአዊ የጤና አጠባባቅም ፈተና ላይ በወደቀበት ዘመናችን የተለያዩ እቅዶችን በመወጠን ማሕበረሰቡን ስለ ጤና አጠባበቅ ማስተማር አንገብጋቢ እና አስፈላጊ ጉዳይ ሆኗል።

ፌዴሬሽናችሁ ለሕጻናት የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎትን በተመለከተ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያደርገው የሞያ ማሻሻያ ስልጠና፣ የመከላከያ ዘዴ እና ሳይንሳዊ የምርምር ሂደት እውቅናን አግኝቷል። በዚህ ያላሰለሰ ጥረት በመታገዝ አገልግሎታችሁን ዘላቂ እና ለሁሉ የሚዳረስ ማድረግ ትችላላችሁ። በሽታን መከላከል እና ከበሽታም መፈወስ የሚችሉት በመልካም የኑሮ ደርጃ ላይ የሚገኙት ናቸው። የሰዎች የኑሮ አለመመጣጠን በድሃ የማሕበረሰብ ክፍል ላይ ተጽዕኖን በማሳደሩ፣ በዚህም የተነሳ በርካታ ሰዎች በቂ የሕክምና አገልግሎትን የማያገኙ መሆኑን በመገንዘብ፣ የሕክምና አገልግሎት ሥርዓት ሰብዓዊ መብትን ያከበረ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። ለሰው ልጆች የሚሰጥ ትኩረት ከሳይንሳዊ የሞያ ብቃት ጋር ተዳምሮ፣ አገልግሎት ተጠቃሚውን በማዳመጥ እና በመረዳት፣ ታማኝነትንም እንዲያገኝ ማድረግ የአገልግሎታችሁ ልዩ መገለጫ ነው።

ከእምነት ባገኛችሁት ሃይል እና ጥበብ በመታገዝ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎችን ለማዳን የተጓዘበትን የርሕራሄ እና የማዳን መንገድን ለመከተል ተጠርታችኋል። በቅዱስ ወንጌል ላይ የተገለጸውን እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከብዙ ስዎች ጋር መገናኘቱን የሚያስታ፣ ከበሽታቸው መፈወሱን የሚገልጽ የቅዱስ ወንጌል ክፍል በየጊዜው በማንበብ፣ የእናንተን ማንነት እና አገልግሎታችሁን ሁልጊዜ ማሳደግ እና ማደስ ያስፈልጋል።

የሕክምና አገልግሎትን ከምታበረክቱላቸው ሕጻናት ጋር ካላችሁ ግንኙነት በፊት ትላቅ የሃላፊነት ድርሻ ካለባቸው ከወላጆች ጋር ዘላቂ ግንኙነት ሊኖራችሁ ይገባል። እነዚህ ወላጆች ውድ ልጆቻቸውን ለእናንተ አሳልፈው ሲሰጡ እርግጠኞች መሆን የሚፈልጉት በሕክምና ሞያ ብቃታችሁ ብቻ ሳይሆን በሰብዓዊ ዋስትናችሁም ጭምር ነው።

የታመሙ ሕጻናትን በምትጎበኙበት ጊዜ ሕጻናቱ ከእናንተ ከፍተኛ ትኩረትን፣ ሰብዓዊ ፍቅርን እና ርህራሄን ይጠብቃሉ። ይህን አስቀድሞ ካልተገነዘቡ ነገር ግን በግል እና በማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ በመጨነቅ ከመጣደፍ ይልቅ በስቃይ ላይ የሚገኙትን ሕጻናት ማበረታታት፣ ማጽናናት እና ስቃያቸውን ለማስወገድ ፈውስ የሚገኝበትን መድሐኒት ማቅረብ ቀዳሚ ተግባር መሆን ያስፈልጋል።

ለሕጻናት በሚሰጥ የጤና እንክብካቤ መካከል ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥተ ሰማይ ለማን እንደሚሆን በማስረዳት የተናገረውን ማስተዋል ያስፈልጋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሕጻናትን ወደ ራሱ የጠራቸው፣ ሕጻናትም ወደ እርሱ በደስታ የቀረቡት የሚያማምሩ ስጦታዎችን ተመልከተው በመማረክ ሳይሆን በእውነተኛ ማንነቱ በመሳባቸው ነው።

የሥራ ባልደረባችሁ የሆኑት ዶክተር ፍራንኮ ፓኒዞኒ በንግግራቸው እንደገለጹት “አንድ የሕክምና ባለሞያ ከሁሉ አስቀድሞ ለሕጻናት ሊሰጥ የሚገባውን የሕክምና አገልግሎት ሳይፈጽም ማረፍ የለበትም” ብለዋል። ዶክተር ፍራንኮ ንግግራቸውን በመቀጠል የሕጻናት ሐኪሞች ትንሽም በአገልግሎታቸው ወቅት ማሳደግ ያለባቸውን ባሕል እና እጅግ ጠቃሚ ልምድ ሲናገሩ “መመልከት ያለብን ሕጻናት ስለሚሰቃዩበት የበሽታ ዓይነት እና አመጣጡን ወይም የምንገኝበትን የሥራ ውጥረት ወይም ስለ ራሳችን ሕይወት ወይም ስለ ድካማችን ሳይሆን አሻግረን መመልከት ይገባል። የሕሙማኑን የዛሬ ስቃይ ብቻ ሳይሆን የነገውንም ስቃይ ማሰብ ያስፈልጋል፤ አንድ ታማሚን ብቻ ሳይሆን ሌሎች በርካታ ሕሙማን መኖራቸውን ማሰብ ያስፈልጋል፤ በአካባቢያችን የሚገኙ ሕሙማንን ብቻ ሳይሆን በሩቅ አገር የሚገኙትንም ማሰብ ያስፈልጋል” ብለዋል።

በሕክምና አገልግሎታችሁ እነዚህን መርሆች የምትከተሉ ከሆነ እውነተኛ ተልዕኮ ያለበትን፣ አእምሮን እና ልብን የሚያሳትፍ፣ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳትሉ የዘወትር ሃላፊነታችሁን በሚገባ ማከናወን ትችላላችሁ። በመሆኑም ለሕጻናት የምታበረክቱት የሕክምና አገልግሎታችሁ በምትሄዱበት ሁሉ እናንተን ተከትሎ ይበልጥ ደግሞ በሥራ ገበታ በምትሆኑባቸው ጊዜያት አብሮአችሁ ይሆናል።

ይህን አገልግሎት በማበርከታችሁ እና የወንጌል እሴት የሚገኝበት ክርስቲያናዊ ተግባር በማከናወናችሁ ምስክርነታችሁን ትሰጣላችሁ። የቤተክርስቲያን አባል በመሆናችሁ፣ የአመለካከት አድማሳችሁን በማስፋት፣ ያካበታችሁትን እውቀት እና ችሎታን በመጠቀም፣ ማሕበራዊ የኑሮ ደረጃዎችን በማገናዘብ፣ ወደ ፊት ሊቀርብ የሚገባውን ትክክለኛ እና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ሥርዓት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ በማሕበረሰቡ መካከል ለድሆች እና አቅመ ደካማ ለሆኑት ሁሉ ርህራሔ እና ጥበብ የታከለበት አገልግሎት ማበርከት ያስፈልጋል። በምታከናውኑት የሕክምና አገልግሎታችሁ የእግዚአብሔር ቡራኬ ለእያንዳንዳችሁ ይድረሳችሁ በማለት እናንተም በጸሎታችሁ እንድታስታውሱኝ አደራ እላለሁ፤ አመሰግናለሁ”።

 

 

     

21 March 2019, 17:32