ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለየካቲት ወር ያስተላለፉት የጸሎት ሐሳብ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየወሩ ለወሩ የሚሆን የጸሎት ሐሳብ በቪዲዮ መልእክት ይፋ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው ለየካቲት ወር 2011 ዓ.ም  ያቀረቡት የጸሎት ሐሳብ “ሕገወጥ የሰው ልጆች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ተቀብለው በደስታ ለሚያስተናግዱ ሰዎች እንጸልይላቸው” የሚል መልእክት ያዘለ የጸሎት ሐሳብ እንደ ሆነ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ ለሆኑ፣ በአስገዳጅ ሁኔታ ሴተኛ አዳሪ እንዲሆኑ ለተገደዱ እና የጭካኔ ድርጊቶች ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ለማስተናገድ በደስታ ለሚቀበሉዋቸው ሰዎች እንጸልይ” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት የሚከተለውን ብለዋል. . .

ምንም እንኳን እኛ ዝም ለማለት ብንሞክርም፣ ነገር ግን ባርነት ልክ ከዚህ ቀደም እንደ ነበረው ጊዜ አይደለም።

ይህንን አሳዛኝ የተጋረጠብንን እውነታ በመመልከት የዚህ ወንጀል ተባባሪ ካልሆንን በስተቀር በሰብዓዊነት ላይ የሚቃጣውን ይህንን ወንጀል እየተመለከተ እጁን ታጥቦ ቁጭ የሚል ማንም ሰው ሊኖር አይችልም።

ከዚህ ቀደም እንደ ነበረው ሁሉ ምን አልባትም ከእዚያ በበለጠ መልኩ በዛሬውም ዓለም ቢሆን ባርነት በሰፊው ተንሰራፍቶ እንደ ሚገኝ መዘንጋት የለብንም።

“ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ፣ በአስገዳጅ ሁኔታ ሴተኛ አዳሪ እንዲሆኑ የተገደዱ እና የጭካኔ ድርጊቶች ሰለባ የሆኑ ሰዎችን በደስታ ተቀብለው ለሚያስተናግዱ ሰዎች እንጸልይላቸው”።

ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ማለትም በጥር 30/2011 ዓ.ም በቪዲዮ ባስተላለፉት የየካቲት ወር የጸሎት ሐሳብ እንደ ገለጹት እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን “የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ፣ በአስገዳጅ ሁኔታ ሴተኛ አዳሪ እንዲሆኑ የተገደዱ እና የጭካኔ ድርጊቶች ሰለባ ስለሆኑ ሰዎች በእየለቱ በዜናዎች እና በጋዜጦች ላይ የምንመለከተው እውነታ መሆኑን የገለጹ ሲሆን የኢኮኖሚ ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ ሕገወጥ ስደተኞች፣ ተፈናቃዮች፣ ብቻቸውን የተሰደዱ ሕጻናት፣ የበረሃ ውስጥ ተጓዦች የመሳሰሉ የተለያዩ ስያሜዎችን በመስጠት ብዙን ጊዜ የሰው ልጆች መሆናቸውን እንኳን እንዘነጋለን ብለዋል። በጦርነት፣ በረሃብ፣ ፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያት በሚከሰት ስደት፣ ሃይማኖታዊ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያት የሚሰደዱ ሰዎች ወይም ለአስከፊ ድህነት በመጋለጣቸው የተነሳ የሚሰደዱ ሰዎች በርካታ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መከራዎች ስለደርሰባቸው ቤት ንብረታቸውን ጥለው የሚሰደዱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መኖራቸውን ቅዱስነታቸው በቪዲዮ መልእክታቸው ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት እኛ በዓይናችን የማናያቸው ነገር ግን ይህንን አስገዳጅ የስደተኞች ፍልሰት አጋጣሚውን በመጠቀም ወንዶችን፣ ሴቶችን እና ሕጻናትን ሳይቀር ለአስገዳጅ የጉልበት ሥራ፣ አስገዳጅ የወሲብ ሥራ፣ የአካል ክፍሎችን በሕገወጥ መልክ ከሰዎች አካል ላይ በመንቀል በሕገወጥ መልክ ለንግድ በማቅረብ ሥራ፣ አስገዳጅ በሆነ መልኩ በልመና ሥራ ላይ እንዲሰማሩ የማደርግ ሥር ወይም አስገዳጅ በሆነ መልኩ በወንጅል ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ የማስገደድ ሥራ በመሥራት ከእነዚህ ዘርፎች ተጠቃሚ የሚሆኑ የተደራጁ ወንጀለኞች እንደ ሚገኙ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለየካቲት ወር ባቀረቡት የወሩ የጸሎት ሐሳብ እንደ ገለጹት ባርነትን "ከዚህ ቀደም እንደ ነበረው ጊዜ በሰብአዊነት ላይ ለተፈጸመው ወንጀል ተባባሪ ካልሆኑ በስተቀር ማንም ምንም እንደ ማይመለከተው ዓይነት እጁን ታጥቦ ዝም ብሎ ሊቀመጥ የማይችልበት ወቅት ላይ መሆናችንን ገልጸዋል።

 

 

07 February 2019, 14:19