ር.ሊ.ጳ.ፍራንቸስኮስ በጥር 26/2011 ዓ.ም ከመልኣከ እግ/ሔር ጸሎት በኋላ ያስተላለፉት መልእክት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 26/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው አስተንትኖ ካደርጉ በኋላ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በመስጠት ከሚደገሙ ጸሎቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰውን “የእግዚኣብሔር መልኣክ ማርያምን አበሰራት” የሚለውን የብስራተ ገብሬል ጸሎት ከምዕመናን ጋር በመቀባበል ከደገሙ በኋላ እንደ ተለመደው ለዓለም ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት በአሁኑ ወቅት በየመን እየተከሰተ በሚገኘው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በየመን ውስጥ እየተከሰተ የሚገኘው ሰብአዊ ቀውስ እየጨመረ መምጣቱ በጣም እንዳሳሰባቸው ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

ይህ የእርስ በእርስ ግጭት ለረዢም ጊዜያት በመደረጉ የተነሳ ግጭቱ በረዘመ ቁጥር በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው መከራ እና ጫና እየበዛ መምጣቱን የገለጹት ቅዱስነታቸው በተለይም ደግሞ ለዚህ ግጭት መነሳት ምንም ዓይነት አስተዋጾ ያላዳደርጉ ሕጻናት በረሃብ እና በስቃይ ውስጥ እንደ ሚገኙ ቅዱስነታቸው አስታውሰው በአገሪቷ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የርዳታ መስጫ ተቋማት ለተጎጅዎች የሚሆን በቂ ምግብ ቢኖራቸውም ቅሉ ነገር ግን ርዳታ ፈላጊዎች የርዳታ መስጫ ጣቢያዎችን መድረስ አልቻሉም፣ ይህም በቀውሱ የተነሳ መንገዶች በመዘጋታቸው የተነሳ የተፈጠረ ክስተት መሆኑን ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ወድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ የእነዚህ ተጎጂ ሕጻናት እና የወላጆቻቸው ጩኸት ወደ እግዚኣብሔር ዘንድ ይደርሳል፣ በመሆኑም በዚህ ግጭት ውስጥ ለተካፈሉ አገራት እና ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሳይቀር ይህ ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም እና ከዚህ ቀደም የተደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነቶች እንዲከበሩ፣ በተጨማሪም የምግብ ማከፋፋያ ጣቢያዎች ለሕዝቡ ተደራሽ ይሆኑ ዘንድ፣ የሕዝቡ ስቃይ በአስቸኳይ ያበቃ ዘንድ ጥሪ አቀርባለሁ በማለት ቅድስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

“በየመን ለሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መጸለይ ይኖርብናል እባካችሁን በአንድነት ‘ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ’ የሚለውን ጸሎት በጋራ በመጸለይ በየመን የሚገኙ በረሃብ እየተሰቃዩ የሚገኙ ሕጻናትን፣ የተጠሙ ወላጆችን፣ ምንም ዓይነት የመድኃኒት አቅርቦት የሌላቸውን ሕዝቦች፣ በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙ የየመን ሕዝቦችን ለማርያም በአደራ በመስጠት እኛም ወደ እየቤቶቻችን በምንመለስበት ወቅት በልባችን ውስጥ የየመን ሕዝቦችን ስቃይ ይዘን መመለስ እንችል ዘንድ ጥሪዬን አቀረባለው”’ ካሉ በኋላ “ወደ ተባበሩት የአረብ ኤምሬትስ አገር ወደ ሆነችው ወደ አቡ ዳቢ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለመድረግ ወደ እዚያው ስለ ምጓዝ እባካችሁን ለእኔ ጸልዩልኝ” ካሉ በኋላ ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተው ቅዱስነታቸው መሰናበታቸውን ከደርሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

 

03 February 2019, 16:26