በአቡ ዳቢ ከተማ ውስጥ በሚገኘው በዛይድ ስታዲዬም ያሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ በአቡ ዳቢ ከተማ ውስጥ በሚገኘው በዛይድ ስታዲዬም ያሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የክርስቲያን መሣሪያ እምነት እና ፍቅር ብቻ ናቸው”።

ቅዱሳን ተብለው የተጠሩበት ምክንያት በሕዝቦች መካከል እውቅናን ስላተረፉ ወይም ሃብትን ስለ ሰበሰቡ ወይም በሥራቸው ዕውቅናን ስላገኙ ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን ለኢየሱስ ክርስቶስ የተቀደሱት የሚላቸው ደሆችን፣ የተረገጡትን፣ የተሰቃዩትን እና የተጨቆኑትን ነው

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካለፈው እሑድ ጥር 26 እስከ ጥር 28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በተባበሩት አርብ ኤምሬቶች ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ባጠቃለሉበት በዛሬው ዕለት በአገሩ ከሚኖሩት ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት ላይ እንደ ገለጹት የክርስቲያን መሣሪያ እምነት እና ፍቅር ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በአቡ ዳቢ ከተማ ውስጥ በሚገኘው በዛይድ ስተዲዬም ያሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ታሪካዊ ነው ተብሏል። አንድ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ አረብ አገሮች ባሕረ ሰላጤ ሲጓዙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመጀመሪያው እንደሆኑ መግለጻችን ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉ ምመናን በሙሉ ባሰሙት ስብከታቸው ለብጹዓን ምስጋና ይግባቸውና እናንተ የሰላም ምሳሌ ናችሁ በማለት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውስጥ በተለያዩ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ምዕመናንን አመስግነዋቸዋል። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን ቀላል የሕይወት ምስክርነቶችን እየሰጡ፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ለመንፈሳዊ ወንድሞቹ ይናገር እንደነበረ ኢየሱስ ክርስቶስን እየተከተሉ የፍቅር ሥራዎችን ለወንድሞች እና እህቶች ማበርከት ኣነድሚያስፈልግ አሳስበዋል።   

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አረብ ባሕረ ሰላጤ አገሮች ባደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝታቸው፣ እንደዚሁም የመጀመሪያቸው በሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት ላይ ለምዕመና በሙሉ ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል። መስዋዕተ ቅድሴውን ለተካፈሉት 180,000 ምዕመናን ዕለቱ የጋራ ጸሎት የቀረበበት የደስታ ዕለት ሆኖ መዋሉ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከማቴዎስ ወንጌል ተወስዶ በተነበበው መልዕክት ላይ በመመርኮዝ ባቀረቡት አስተንትኖ ከኢየሱስ ጋር ከሆናችሁ፣ እንደ ደቀ መዛሙርቱ ቃሉንም የምታደምጡ ከሆነ፣ በቃሉም የምትመሩ ከሆነ ብጹዓን ናችሁ ብለዋል። ይህም በክርስትና ሕይወት ውስጥ ማወቅ የቻልነው የመጀመሪያው እውነት ነው ብለዋል። የክርስትና ሕይወት ከሁሉም በላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች መሆናችንን ማወቅ ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ ማንም በዚህ ዓለም ላይ ከሕይወታችን ሊነጥቅብን ያማይችለው የደስታችን ምክንያት ነው። ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እናንተና ሳገኛችሁ ልነግራችሁ ያፈለኩት ቃል ይህ ነው፣ የተባረካችሁ የሚል ነው ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን የተባረካችሁ ናችሁ ሲላቸው፣ እያንዳንዱ ቅዱሳን፣ ቅዱሳን ተብለው የተጠሩበት ምክንያት ለምንድነው ብለን ራሳችንን እንጠይቃለን። ቅዱሳን ተብለው የተጠሩበት ምክንያት በሕዝቦች መካከል እውቅናን ስላተረፉ ወይም ሃብትን ስለ ሰበሰቡ ወይም በሥራቸው ዕውቅናን ስላገኙ ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን ለኢየሱስ ክርስቶስ የተቀደሱት ደሆች፣ የተረገጡት፣ የተሰቃዩት እና  የተጨቆኑት ናቸው። ይህን በሚገባ ለመረዳት ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደኖረ መመልከት ያስፈልጋል። ለአንዳንድ ነገሮች ክብርን ለመስጠት ደሃ ነበር፣ ነገር ግን ፍቅርን በማሳየት ሐፍታም ነበር። ብዙ የታመሙ ሰዎችን በማዳን ኣና በመፈወስ ይታወቅ ነበር ነገር ግን የራሱን ሕይወት ከሞት ሊያተርፍ አልቻለም። ሊያገለግል እንጂ ሊገለገል አልመጣም። ትልቅነት የሚገኘው ከመስጠት እንጂ ከመቀበል አይደለም። ፍጹም ትክክል እና ትሑት ሆኖ ሳለ ራሱን ለሕገ ወጥ ፍርድ አቀረበ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ፍቅር ወደ ዓለም አምጥቷል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ክርስቶስን በሙሉ ልብ እንድንከተል የሚያደርገንን የመንፈስ ቅዱስ እገዛን በጸሎት እንጠይቅ በማለት ምዕመናኑን አሳስበዋል።           

05 February 2019, 16:47