ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ወጣቶች በዓለም ውስጥ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ማድረግ የሚችሉ እርሾዎች ናቸው”

“ማርያምም እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ተለይቶ ሄደ። ማርያምም በዚያ ወራት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች” (ሉቃስ 1፡38-39)።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ እና እንደ አየሩ ሁኔታ በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ እርሳቸው የሚያደርጉትን ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አሰተምህሮ ለመከታተል ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት በዛሬው እለት ማለትም በጥር 22/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አሰተምህሮ በቅርቡ ከጥር 14-19/2011 ዓ.ም “እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ” (ሉቃ 1፡38) በሚል መሪ ቃል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተገኙበት በፓናማ ተካሄዶ በነበረው 34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ትኩረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “ወጣቶች በዓለም ውስጥ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ማድረግ የሚችሉ እርሾዎች ናቸው” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው እለት ማለትም በጥር 22/2011 ዓ.ም ያደርጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!
በቅርቡ በተጠናቀቀው እና በፓናማ አድርጌው ስለነበረው ሐዋሪያዊ ጉብኝት አጠቃላይ ይዘት በመጥቀስ ዛሬ ከእናተ ጋር ስለዚህ ጉዳይ ለመካፈል እፈልጋለሁ። በዚያ አገር የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን እና የእዚያ አገር ተወዳጅ ሕዝብ ስላደረገልን እንክብካቤ፣ ለእዚህ ለተቀበልነው ጸጋ ከእኔ ጋር በመሆን ለጌታ ምስጋና እንድታቀርቡ እጋብዛችኋለሁ። የፓናማ ፕሬዚዳንት እና ሌሎች ባለስልጣኖች፣ እንዲሁም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎችን በሙሉ ላደረጉልን ሞቅ ያለ እና ቤተሰባዊ የሆነ አቀባበል፣ በተጨማሪም በታላቅ ጉጉት እኛን ሰላም ለማለት ሲሯሯጡ የነበሩ ሕዝቦችን በሙሉ ለማመስገን እወዳለሁ። ሰዎች እጃቸው ላይ የሚገኙትን ሕጻናት ወደ ላይ ከፍ አድርገው በማንሳት “የሄውና የእኔ ኩራት፣ ይሄውና የእኔ የመጪው ጊዜ ተስፋ” በማለት ይናገሩ ነበር። የዚህ ዓይነት አካላዊ መግለጫ ምን ያህል ክብርን የሚያስገኝ መሆኑን የሚያሳይ እና በዚህ በጣም ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ በሚታይበት በአውሮፓ አህጉር እየኖረ ላለው ሕዝብ ምን ዓይነት ትርጉም ያሰማል!
የዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋናው ዓላማ የነበረው በዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ መሳተፍ የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን ከወጣቶች ጋር ያለው ግንኙነት ከአገሪቱ እውነታ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ የተነሳ በዚህ ምክንያት ከአገሪቷ ባለስልጣናት፣ ከብጹዕን ጳጳሳት፣ በማረሚያ ቤት ከሚገኙ ወጣቶች ጋር፣ ከቀሳውስት ጋር እና ደጉ ሳምራዊ በመባል በሚታወቀው የቤተሰብ አገልግሎት መስጫ ተቋም ጭምር አጋጣሚውን ተጠቅሜ ጎብኝቻለሁ ተገኛኝቻለሁም። ሁሉም ነገር በወጣቱ ላይ ደስታ በሚታይ መልኩ "የተጠላለፈ" እና "የተዋጣለት" ነበር፣ ለወጣቱ ከፍተኛ የሆነ ደስታ የፈጠረ በዓል ሲሆን እንዲሁም ለፓናማ የበዓል ቀን የነበረ፣ በአጠቃላይ ብዙ ድራማዊ የሚመስሉ ነገሮች በሚከናወኑበት እና ተስፋ እጅግ በሚያስፈልገው በመካከለኛው አሜርካ ትልቅ የበዓል ቀን ነበር።
በዚህ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ለየት ባለ ሁኔት የአገሩ ቀደምት ነዋሪዎች ዘር ተተኪ የሆኑ ወጣቶች እና የአፍሪካ ዘር ያላቸው ወጣቶችም ሳይቀር መገኘታቸው የሚታወስ ሲሆን ይህም በላቲን አሜሪካ ውስጥ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ያላትን የተለያዩ ገፅታዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳየ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ነበር። ከዚያም ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ የተለያዩ ቡድኖች መምጣት ሲጀምሩ፣ ከዚያም በመቀጠል የተለያዩ የፊት ገጽታዎች እና ቋንቋዎች መታየት ሲጀምሩ፣ የዚህ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ልማዳዊ የሆነ ክስተት መታየት ጀመረ። ከሁሉም አገራት የተውጣጡ ሰዎች ይዘዋቸው የመጡትን ባንዲራዎች በአንድ ላይ ሆኖ መመልከት፣ ደስተኛ በሆኑ ወጣቶች መካከል ተገኝቶ መጨዋወት ትንቢታዊ የሆነ ምልክት ነው፣ ይህ ዛሬ ብሔራዊነትን በከፍተኛ ሁኔታ በማንጸባረቅ እርስ በርስ በመጋጨት ላይ ከሚገኙው ኅብረተሰብ አንጻር ሲታይ ተቃራኒ የሆነ ምልክት ነው። ይህ ወጣት ክርስቲያኖች በዓለም ውስጥ ሰላም ማስፈን እንደ ሚችሉ የሚያሳይ ሁኔታ መኖሩን ያመለክታል።
ይህ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ጠንካራ የማሪያም ምልእክት ነበረው፣ ምክንያቱም የዚህ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን መሪ ቃል ወይም ጭብጥ ሐሳብ የነበረው ማሪያም መልኣኩ ላቀረበላት ጥያቄ “እነሆኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ፣ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” (ሉቃስ 1፡38) ብላ የተናገረችሁ የእሽታ ቃል በመሆኑ የተነሳ ነው። ከአምስቱ አህጉራት በተወጣቱ የወጣቶች ተወካዮች፣ እነዚህን የማሪያም ቃላት ሲያስተጋቡ መስማት፣ ከሁሉም በላይ ደግም ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ቃላት በወጣቶቹ ፊት ላይ ሲንጸባረቁ ማየት በጣም ብርቱ የሆነ ስሜት የሚፈጥር ክስተት ነበር። "እነሆኝ" ማለት የሚችል አዲስ ትውልድ እስካለ ድረስ መጪው ዓለም እንደ ሚኖር ያመላክታል።
የዓለም የወጣቶች ቀን በሚከበርበት ወቅት ሁሉ የመስቀል መንገድ ጸሎት ይካሄዳል። መስቀል ተሸክሞ ከሚሄደው ኢየሱስ ጀርባ ከማሪያም ጋር መጓዝ የክርስትና ህይወት ትምህርት ቤት ነው፣ እዚያ ትዕግስት፣ ዝምታ፣ ፍቅርን እና ተጨባጭ መሆንን እንማራለን። በፓናማ ወጣቶች በመካከለኛው አሜርካ እና በመላው አለም ውስጥ ከባድ የሆነ ሸክም የሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ወንድሞች እና እህቶች ሁኔታ ከማርያም እና ከኢየሱስ ጋር በመሆን ተሸክመው መጥተው ነበር። ከነዚህ ውስጥ ብዙ የተለያየ ዓይነት የባርነት እና ድህነት ሰለባዎች የሆኑ ወጣቶች ይገኙበታል። ይህንን በተመለከተ በጣም ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጣቸው ደጉ ሳምራዊ በመባል በሚታወቅ ተቋም ውስጥ በኤድስ በሽታ የተጠቁ ሰዎች የሚኖሩበት ቤት ውስጥ ተካሄዶ የነበረው የምስጢረ ንስሐ ስነ-ስረዓት ዋነኛው ነው።
የዓለም ወጣቶች ቀን እና ይህ ሐዋሪያዊ ጉዞ የተጠናቀቀው ወጣቶች በተገኙበት አመሻሹ ላይ በተደረገ የዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ ነበር። በዚያ የዋዜማ ምሽት ላይ ከወጣቶች ጋር ሕያው የሆነ ውይይት ተደርጎ ነበር፣ እነርሱም በንቃት እና በአድናቆት እንዲሁም በዝምታ ለማዳመጥ ችለው ነበር። በወቅቱ እነርሱ የማሪያምን አብነት በመከተል፣ እርሷ ምንም እንኳን በጣም ትንሽ የነበረች ሰው የነበረች ቢሆንም የእግዚኣብሔርን ቃል አምና በመቀበሏ በዓለም ውስጥ ተጽኖ በመፍጠር ትልቅ ስፋራ እንዳገኘች ሁሉ፣ ወጣቶችም ይህንን የማሪያም አብነት እንዲከተሉ ጥሪ አቅርቤላቸው ነበር። እነሱ "እነሆኝ" በማለታቸው በአንዳንዱ ወጣት ውስጥ ውብና ጠንካራ ምስክርነት ተረጋግጧል። እሁድ እለት ጠዋት ላይ የዚህ ዓለማቀፍ የወጣቶች ቀን ማብቂያን በማስመልከት በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከሞት መነሳቱን በመግለጽ በድጋሚ ለወጣቶቹ በአዲስ መልክ ቅዱስ ወንጌልን “ዛሬ” እንዲኖሩ ጥሪ አቅርቤላቸው ነበር፣ ምክንያቱም ወጣቶች የነገ ሰዎች ወይም የወደ ፊቱ ዘመን ሰዎች ሳይሆኑ የዛሬው ዘመን ሰዎች፣ የዛሬ ቤተ ክርስቲያን አባል እንደ ሆኑ፣ የዛሬው ዓለም አባል እንደ ሆኑ ጭምር ነግሬያቸዋለሁ። ጎልማሶቹን ደግሞ ለአዲሱ ትውልድ የሚሆኑ ተቋማትን፣ ሥራ፣ ማኅበርሰብ እና ቤተሰብ የማዘጋጀት ኃላፊነት እንዳለባቸው ነግሬያቸዋለሁ።
ከሁሉም የማዕከላዊ አሜሪካ ጳጳሳት ጋር አድርጌው የነበረው ስብሰባ ለእኔ ልዩ ማጽናኛ ነበር። በጋራ ሁላችንም ቅዱስ ሮሜሮ ኦስካር ትቶልን ያለፈውን አስተምህሮ ተምረናል፣ ቤተ ክርስቲያንን ሁል ጊዜ ማዳመጥ አስፈላጊ እንደ ሆነም ተምረናል፣ ይህም እርሳቸው መዐረገ ጵጵስናን ሲቀበሉ የመረጡት መሪ ቃል ወይም አርማ ነበር፣ ወጣቶችን በመቀረብ፣ ከድሆች ጋር መሆን፣ ለካህናት ቅርብ መሆን፣ ለቅዱሱ ለእግዚኣብሔር ሕዝብ ቅርብ በመሆን ቤተ ክርስቲያንን ማዳመጥ ይገባል ይሉ ነበር።
በፓናማ በአዲስ መልክ ታድሶ ለአገልግሎት የበቃውን በአንቲጓ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ስም የተሰየመውን ካቴድራል የመባረክ እድል አግኝቻለሁ። የእግዚአብሔር ክብር የተገለጸበት፣ የሕዝቡ እምነት የታየበት እና የሚያምር የሕዝብ በዓል በመሆን ታላቅ ምልክት ጥሎ አልፉዋል። መንበረ ታቦቱን ለመባረክ የተጠቀምንበት ቅባ ቅዱስ ምስጢረ ጥምቀት፣ ምስጢር ሜሮን፣ ምስጢረ ክህነት እና የጵጵስና ማዕረግ የሚቀበሉ ጳጳሳት ከሚቀቡት ቅባ ቅዱስ ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህ ቅባ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን ቤተሰቦችን፣ በፓናማ እና በመላው አለም የሚገኙ ሰዎችን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሚስዮናዊ ደቀ-መዛሙርት በመሆን በዓለም ውስጥ መንፈሳዊ ነጋዲያን በመሆን ጉዞዎቻቸውን በምድር ላይ ይቀጥሉ እና ያስፋፉ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት አዲስ ፍሬ የሚያፈሩበትን ጸጋን የሰጣቸዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
30 January 2019, 13:44