ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ካቶሊካዊ ጋብቻን እና ዝግጅትን ከሚከታተል ከፍተኛ ሐዋርያዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ጋር ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ካቶሊካዊ ጋብቻን እና ዝግጅትን ከሚከታተል ከፍተኛ ሐዋርያዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ጋር  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጋብቻ ሕይወት አንድነትንና ታማኝነትን መግለጽ አስፈላጊ መሆኑን አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አንድነትና ታማኝነት በጋብቻ ሕይወት መካከል ብቻ ሳይሆን በማሕበራዊ ኑሮ መካከልም ለሰዎች ግንኙነቶች እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ተግባራዊ በማይሆኑበት ጊዜ የሚከሰቱትን ችግሮችና የሚያስከትለውን ቀውስ መመልከት ይቻላል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ትናንት ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2011 ዓ. ም. በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካቶሊካዊ ጋብቻን እና ዝግጅትን ለሚከታተል ከፍተኛ ሐዋርያዊ ፍርድ ቤት የሕግ ባለሞያዎች ባደረጉት ንግግራቸው፣ መልካም የጋብቻ ሕይወትን ለመኖር የሚያግዙ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች እንዳሉ እነርሱም አንድነትና ታማኝነት እንደሆኑ ገልጸዋል። “የዓለማዊውነት አስተሳሰብ በተስፋፋበት ዘመናችን፣ ካቶሊካዊ ቤተሰብ የጋብቻን ሕይወት እንደ ቅዱስ ወንጌል እና እንደ ቤተክርስቲያን ደንብ በመኖር ለምስክርነት እንዲበቁ የሚያስችል መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ድጋፍ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበዋል።

በጋብቻ ሕይወት አንድነትና ታማኝነት እንዲኖር ያስፈልጋል፣

በጋብቻ ሕይወት ውስጥ ታማኝነትን መግለጽ ይቻላል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ታማኝነት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ካቶሊካዊ ጋብቻን እና ዝግጅትን ለሚከታተል ከፍተኛ ሐዋርያዊ ፍርድ ቤት የሕግ ባለሞያዎች አስረድተዋል። በጋብቻ ሕይወት ውስጥ አንድነት እና ታማኝነት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሠረታት ቤተክርስቲያን መሠረት እንደሆኑ አስረድተው ነገር ግን የዘመናችን ማሕበረሰብ እነዚህን የጋብቻ ሕይወት መሠረት የሆኑትን ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያደርግ ድጋፍ አይሰጥም ብለዋል። አሁን የምንገኝበት ማሕበረሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ የዓለማዊነት መንፈስ እየተስፋፋ የሄደበት በመሆኑና እምነት እንዲያድግ የሚያበረታታ አስተዋጽዖ ስለሌለው፣ ካቶሊካዊ ቤተሰብ ቅዱስ ወንጌልን መሠረት ያደረገ የጋብቻ ሕይወት በተግባር በመኖር ምስክሮች እንዲሆኑ ያስፈልጋል ብለዋል። አንድነትና ታማኝነት በጋብቻ ሕይወት መካከል ብቻ ሳይሆን በማሕበራዊ ኑሮ መካከልም ለሰዎች ግንኙነቶች እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸው ተግባራዊ በማይሆኑበት ጊዜ የሚከሰቱትን ችግሮችና የሚያስከትለውን ቀውስ መመልከት ይቻላል ብለዋል።             

የቅድመ ጋብቻ ዝግጅት ሊኖር ይገባል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካቶሊካዊ ጋብቻ ፍሬያማ የሚሆንበትን መንገድ ሲያስረዱ፣ ካቶሊካዊ ጋብቻን ፍሬያማ ለማድረግ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ሁለት ወንድና ሴት ተጋቢዎች ለጋስ አንድነት እና ታማኝ ፍቅርን በሕይወታቸው ዘመን በሙሉ የሚጋሩበትን መንገድ በማሳየት እንዲያግዟቸው አሳስበዋል። የጋብቻ ቅድመ ዝግጅት በሦስት ደረጃዎች የተከፈለ ነው ብለው የመጀመሪያው ጋብቻ ከመፈጸሙ ከወራት በፊት የሚጀምር ዝግጅት፣ ሁለተኛው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በተቃረበበት ሳምንታት የሚደረግ ዝግጅት እና ሦስተኛው ጋብቻ ከፈጸሙ በኋላ ባለ ትዳሮች እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ የሚደረግ ዘላቂ ክትትል እንደሆነ አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ጋር አያይዘው የቤተክርስቲያን እረኞች የጋብቻ ዝግጅት ስልጠናን በተመለከተ የመጀመሪያውን ሃላፊነት የሚይዙ ቢሆንም በቁምስና ስር በሚገኙ የተለያዩ መንፈሳዊ ማሕበራት አባላት ሃሳባቸውን፣ ልምዳቸውን እና ምክራቸውን ለባለ ትዳሮች በማካፈል የበኩላቸውን እገዛ ማድረግ ይችላሉ ብለዋል።

የቅዱሳን አኲላ እና ፕሪሺላ ምሳሌን መከተል፣

ቅዱስ አኲላን እና ቅድስት ፕሪሺላን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፣ እነዚህ ሁለት ባልና ሚስት ሐዋርያው ጳውሎስን በወንጌል አገልግሎቱ ከጎኑ ሆነው እንዳገዙት አስታውሰው፣ ሐዋርያው ጳውሎስም እነዚህን ባል እና ሚስት ረዳት የወንጌል አገልጋዮች ብሎ ይጠራቸው እንደነበር ገልጸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለእነዚህ ባልና ሚስት ተከታዮቹ የወንጌል ተልዕኮ እውቅናን መስጠቱን ስንመለከት የቀድሞ ክርስቲያን ማሕበረሰብ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ተቀብለው ለአገልግሎት ራሳቸውን እንዳዘጋጁ እንመለከታለን ብለዋል።

የሐዋርያዊ እንክብካቤ አስፈላጊነት፣

በጋብቻ ሕይወት ጎዳና ለሚገኙት ቤተሰቦች ሊደረግ የሚገባውን እንክብካቤ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ባለትዳሮች አብረው በታማኝነት እንዲኖሩ ከሚያደርጋቸው መንገዶች ቀዳሚዎቹ፣ የእግዚአብሔርን ቃል መመሪያቸው ማድረግ፣ ትምህርተ ክርስቶስን መከታተል፣ ቅዱስት ምስጢራትን ሳያቋርጡ መቀበል፣ መንፈሳዊ አቅጣጫዎችን መከተል፣ የጋብቻን ሕይወት እየኖሩ ለሚገኙት እና አቅመ ደካማ ለሆኑት በሙሉ የቸርነት ሥራን ማበርከት እንደሆነ አስታውሰዋል። በጋብቻ ሕይወት ውስጥ የአንድነትንና የታማኝነትን ሕይወት የሚኖሩ ባለትዳሮች፣ በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ በመሰማራት የበኩላቸውን እገዛ ማበርከት የሚችሉ የቤተክርስቲያን ሃብት መሆናቸውን ቅዱስነታቸው ገልጸው እውነተኛ ፍቅርን እና ምስክርነትንም በመስጠት፣ ቤተክርስቲያን መልካም ፍሬን እንድታፈራ ለማድረግ ከሌሎች የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ጋር መተባበር ይችላሉ ብለው ይህን በመሰለ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ ባለ ትዳሮች የእግዚአብሔር አምሳያነት የሚገለጥባቸው ናቸው ብለዋል።     

የባለ ትዳሮችን መንፈሳዊ ጥንካሬ ማሳደግ ያስፈልጋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካቶሊካዊ ጋብቻን እና ዝግጅትን ለሚከታተል ከፍተኛ ሐዋርያዊ ፍርድ ቤት የሕግ ባለ ሞያዎች ባሰሙት ንግግር፣ የሕግ ባለ ሞያዎቹ የሚሰጧቸው ፍርዶች ፍትህን የተከተሉ እንዲሆን ያስፈልጋል ብለው ይህም ትክክለኛ የጋብቻ ሕግ በተግባር የሚገለጥበትና የባለትዳሮች ክርስቲያናዊ ሕይወት ጥንካሬን የሚያገኝበት መንገድ ይሆናል ብለዋል። 

30 January 2019, 16:38