ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ደካማ የዲፕሎማሲ ስርዓት ደሃ አገሮችን ሊጎዳ እንደሚችል አስጠነቀቁ

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አዲሱን የጎርጎሮሳውያን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለዲፕሎማቲክ አካላት ባስተላለፉት መልዕክታቸው አገሮች በመካከላቸው የሚያደርጉት ሁለገብ ግንኙነት መልካም ግንኙነት ደሃ አገሮችን ከጭቆና ለማላቀቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዲፕሎማቶች ባደረጉት ሰፊ ንግግራቸው በአገሮች መካከል የሚደረገውን ግንኙነት በማስመልከት ባለፉት ዓመታት ቅድስት መንበር ከተለያዩ አገሮች ጋር ያደረገችውን ስምምነትም አስታውሰው ከእነዚህም መካከል ስመተ ጵጵስናን በተመለከተ ከቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ ጋር የተደረገውን ጊዜያዊ ስምምነት ጠቅሰዋል።

በአገሪቱ የሚገኙ ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ካቶሊካዊ ምዕመናንን በበላይነት የሚመሩ ብጹዓን ጳጳሳት ስያሜ የሁለቱ ወገኖች ማለትም የቅድስት መንበርና የቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ይሁንታ ሊኖር እንደሚገባ ከዚህ በፊት ጊዜያዊ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል። ጊዜያዊ ስምምነቱ እስካሁን የቻይና ሕዝባዊ ርፓብሊክ መንግሥት ከቅድስት መንበር እውቅና ውጭ የራሱን ጳጳሳት መሾም እንዲያበቃ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል።

ከረጅም ዓመታት ወዲህ በቻይና የሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ከቅድስት መንበር ጋር ሙሉ ግንኙነት እንዳልነበራቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በአገሪቱ የሚገኙ ካቶሊካዊ ጳጳሳት በሙሉ፣ ከጊዜያዊ ስምምነቱ ወዲህ ከቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ከሆኑት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተሟላ ግንኙነትን ማድረግ በመቻላቸው ምስጋናቸውን አቅርበው ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ግንኙነቶችና ውይይቶች የተቀሩትንም ጥያቄዎች ለመመለስና ለሐይማኖት ነጻነት መንገድ እንደሚከፍቱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የመንግሥታቱ ሊግ የተመሰረተበት መቶኛ ዓመት ዘንድሮ መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ይህም ለመንግሥታቱ ሕብረት ዲፕሎማሲ መጎልበት ጥሩ እንደሆነ ገልጸው ነገር ግን መንግሥታት አንዱ ከሌላው የሚራራቅ ከሆነ የበላይነትን ስሜት በመፍጠር ወደ ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል አስረድተውል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስስኮስ ለአምባሳደሮቹ ባደረጉት ንግግራቸው መንግሥታት በመካከላቸው የተዋጣለት ዲፕሎማሲ ለማበጀት ከፈለጉ መልካሙ መንገድ ቅን ፍላጎትና መተማመን እንዲኖር ማድረግ፣ ችግራቸውን ለመፍታት የሚያስችል ፍትሃዊና ሐቀኛ ውይይት እንዲኖር ማድረግ፣ አለመግባባት ከተፈጠረ መፍትሄን ለማግኘት ስህተትን አሜን ብሎ መቀበል ያስፈልጋል ብለዋል። ይህ ሳይሆን ሲቀር ሃያላን መንግሥታት አቅመ ደካማ በሆኑት መንግሥታት ላይ የበላይነትን ለመጎናጸፍ ይቃጣቸዋል ብለዋል።

የፍትህና የሕግ የበላይነት እንዲኖር ያስፈልጋል፣

የብዙሃን መንግሥታት ግንኙነት አስፈላጊነቱ መንግሥታት በበርካታ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሃላፊነት በጋራ ለመወጣት የሚያደርጉትን ጥራአት የሚመለከት ቢሆንም መንፈሳዊ ግንኙነቶችንም  ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትና ከቅድስት መንበር ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል። ለመንግሥታት ግንኙነት ስኬታማነት አስፈላጊ የሆኑ ርዕሠ ጉዳዮችም ፍትህንና ሕግን ማክበር እንደሆነ ገልጸው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ መንግሥታት ዘንድ እየታየ የመጣው የራስን ፍላጎት ብቻ የማርካት ዓላማ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እንዲጣሱ ያደርጋል ብለዋል። ይህም የአገር መሪዎች ዜጎቻቸውን ለማረጋጋት የሚያደርጉት ጥረት ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሚመራበትን ሕግና ደንብ ወደ ጎን በማድረግ የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት በሚያስቀድሙበት ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ የተከበረውን የዓለም የሰላም ቀን ምክንያት በማድረግ፣ “መልካም ፖለቲካ ሰላምን ለመፍጠር” ያሉትን መልዕክታቸውን በማስታወስ እንደተናገሩት፣ በመልካም የፖለቲካ ሥርዓትና፣ በሕዝቦችና በአገሮች መካከል ባለው ሰላማዊ ግንኙነት መካከል የጠበቀ ግንኙነት መኖሩን አስረድተዋል። ሰላም ለተወሰነ ክፍል ብቻ መልካም መንገድን የሚያመቻች ሳይሆን ሁሉንም ሰብዓዊ ፍጥረት የሚያገለግል መሆን እንዳለበት ገልጸው እንደዚሁም የፖለቲካ ሥርዓትም ነገሮችን አርቆ በመመልከት ለችግሮች መፍትሄን የሚያፈላግ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ለአቅመ ደካሞች ከለላን መስጠት፣

አቅመ ደካማ የሆኑ መንግሥታትም ሆነ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቤተክርስቲያን የተጠራችበት ተልዕኮ አቅመ ደካሞችን መደገፍና ከለላን መስጠት እንደሆነ ገልጸው ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብና ተቋማት ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ሆነው እንዲያገለግሏቸው አደራ ብለዋል። በጦርነት ምክንያት ከፍተኛ የሰው ሕይወት መጥፋት የታየባትን ሶርያ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በሌሎች አገሮችም ለሚከሰቱ ጦርነቶችና አመጾች ፖለቲካዊ መፍትሄዎች እንዲያገኝ አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ አጋጣሚ በመካከለኛው የምስራቅ አገሮች የሚኖሩትን ክርስቲያኖች አስታውሰው በተጨማሪም በጦርነት በአመጽ ምክንያት አገራቸውን ለቀው የተሰደዱ በርካት ሰዎች መኖራቸውንም አስታውሰዋል። ለስደተኞች ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ በተለያዩ አጋጣሚዎች መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጦርነት፣ በአመጽ፣ በድህነትና በሌሎች ስቃዮች ምክንያት ከተወለዱበት አገር እንዲወጡ ለተገደዱት ስደተኞች መንግሥታት እገዛን እንዲያደርጉ፣ በማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ ገብተው ራሳቸውን የሚችሉበትን አጋጣሚዎች እንዲያመቻቹላቸው ጠይቀዋል።

በሕዝቦች መካከል ድልድይ መሆንና ሰላምን መገንባት ያስፈልጋል፣

ለዲፕሎማቶች ባደረጉት ንግግራቸው ስለ ሰላምና ስላምን ስለመገንባት የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ባለፈው ዓመት በአንዳንድ አገሮች ዘንድ የሰላም ምልክቶች መታየቱን አስታውሰው በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥታት እንዲሁም በደቡብ ሱዳን መሪዎች መካከል የተፈረሙትን የሰላም ስምምነቶችን እንደ ምሳሌ ጠቅሰው በሁለቱ ኮሪያዎች መካከልም መልካም የሰላም ምልክት መታየቱን ተናግረዋል። በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ያለውን የሕዝቦች አለመረጋጋት በቅርብ እንደሚከታተሉ የገለጹት ቅዱስነታቸው በሌሎች አገሮችም በተለይ በማሊ፣ በኒጀር፣ በናይጀሪና በካሜሩን የሚካሄዱት ጦርነቶችና አመጾች ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እንደሆኑ ገልጸው፣ ቨነዙአላን ያጋጠማት ማሕበራዊና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ መፍትሄን እንደሚያገኝ ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ተጀምሮ የቆመው ውይይት እንደሚጀምር ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ለጋራ ግባችን ትኩረትን መስጠት፣

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም በሃገራቱ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለጋራ ግብ መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበው የጋራ ግብም በአገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት መልሶ ማጤን እንዳለበት አሳስበውል።     

08 January 2019, 16:16