ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓናማ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት ጋር ተገናኙ።

34ኛውን አለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በፓናማ በማድረግ ላይ የሚገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጉብኝታቸው ከአገሪቱ ፕሬዚደንት፣ ከሲቪል ማሕበረሰብ ተወካዮችና ከተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች ጋር ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን ቅዱስነታቸው ለእነዚህ ከፍተኛ ባለ ስልጣናት ንግግር ማድረጋቸውም ታውቋል።    

“ክቡር ፕሬዚደንት፣

የተከበራቸሁ ባለስልጣናት፣

ክቡራትና ክቡራን፣

ክቡር ፕሬዚደንት ለተደረገልኝ መልካም አቀባበል፣ ስላደረጉልኝ ንግግር እና ፓናማን እንድጎብኝ መልካም ፈቃድዎ ሆኖ ስለጋበዙኝ አመሰግናለሁ። በዚህ አጋጣሚ ለመላው የፓናማ ሕዝብ፣ ከዳሪዬን እስከ ቺሪኪ እንዲሁም ለቦካስ ደል ቶሮ ሕዝብ ሰላምታዬን እያቀረብኩ፣ 34ኛውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ለማዘጋጀት የበኩላቸውን ከፍተኛ እገዛ ላበረከቱት በሙሉ፣ በሮቻችሁን ከፍታችሁ ለተቀበላችሁን በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ይህን መንፈሳዊ ጉዞዬን የምጀምረው፣ ፓናማ የዓለም ዋና ከተማ ብትሆን በማለት ሲሞን ቦሊቫር ያቀረበው ሃሳብ በወቅቱ መሪዎች ዘንድ የአንድ አገር ሕዝቦች የመሆን ሕልም በታለመበት ታሪካዊ አገር ነው። ከዚህ መልዕክት የምንወስደው ጠቃሚ ሃሳብ፣ የበርካታ ባሕል ባለቤት የሆነው ሕዝባችን በጋራ ሆነው፣ ተከባበረው ለመኖር የሚያስችላቸውን ሕብረት ለመፍጠር ብቃት እንዳላቸው ማወቅ ነው። ይህን የአባት በጎ ሃሳብ በሠረት በማድረግ በእርግጥም ፓናማ መልካም ሃሳብ ሕልም የሚመነጭባት አገር አድረገን መውሰድ እንችላለን።

ፓናማ መልካም ጥሪ የሚነገርባት መሬት ናት፣   

ሕዝቦች ተከባብረውና ተፋቅረው በሕብረት የመኖር ፍላጎት ስንመለከት የፓናማ መንግሥት ምክር ቤት አወቃቀርንና፣  ዓለም አቀፍ በዓላቸውን ለማክበር በመቶዎች ከሚቆጠሩ አገሮች ተነስተው እርስ በርስ ለመገናኘት፣ በዓላቸውን በጋራ ለማክበር ባደረባቸው ፍላጎት፣ ረጅም መንገድ ተጉዘው ወደ ፓናማ የመጡበትን ዓላማ ስንመለከት የሕብረት አስፈላጊነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን። ፓናማ ለአካባቢው አገሮች ለምታበረክተው አገልግሎት ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ወጣቶችን ለማስተናገድ ምቹ ቦታ ሆና በማግኘታችን ምስጋናን እናቀርባለን። ውቅንያኖስንና የብስን በማገናኘት እንደ ድልድይ የምታገለግል፣ በላቲን አሜርካ አገሮች መካከል እንደ ቀጭን አገር የምትታይ ፓናማ፣ ለላቲን አሜርካ አገሮች ዘላቂ ግንኙነት እንደ ዋና ምሳሌ የምትጠቀስ አገር ናት። ይህም በፓናማ ሕዝብ ልብ ውስጥ ልዩ ስሜትን ፈጥሮ ይገኛል። እያንዳንዳችሁ ለአገራችሁ ዕድገት የምትሰጡት ቦታ፣ አገራችሁ የተጠራችበትን ሕልምን፣ ለሌሎችም የምታሰማውን ጥሪ ተግባራዊ የማድረግ  ልዩ ተልዕኮ አለባችሁ። ይህ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት እንዲሳተፍ፣ ለራስ፣ ለቤተሰብና ለአገር እድገት  መሳካት ዕለታዊ ጥረትን ማድረግ ይጠይቃል። በፓናማ መልካም ለውጦችን ለማምጣት ከተፈለገ፣ ጥራት ያለውን ትምህርት ለማዳረስ፣ ለኑሮአቸው በቂ ገቢን የሚያስገኝ ጥሩ ሥራ የማግኘት ዕድል ማመቻቸት የመላው ሕዝቦቿ ተሳትፎ ይተይቃል። እነዚህ ሁለቱ ማሕበራዊ አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ የሚቀርቡ ከሆነ፣ ሕዝቦች ጥያቄዎቻቸውና ምኞቶቻቸው ተሟልቶላቸው፣ የደስታ እና የሰላም ሕይወት መኖር ይችላሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህ ሁለቱ ማሕበራዊ አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ ያልተመቻቹ ከሆነ በተለይም በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙት ዜጎች ነጻነታቸው እንዲነፈግ፣ ሰብዓዊ ክብራቸው እንዲቀንስ ያደርጋል።

የፓናማ ሃብታምነት የሚገለጸው በቀደምት የአገሬው ተወላጅ በሆኑ የብሪብሪ፣ ቡግሌ፣ ኤምበራ፣ ኩና፣ ናዞቴሪቤ፣ ንጋቤና ዋውናና ጎሳዎች ነው። እነዚህ ጎሳዎች ስለ ባሕላቸውና ስለ ዓለም ያላቸውን እይታ የሚያስታውሱባቸው በርካታ መንገዶች አሏቸው። ለእነዚህ ጎሳዎች በሙሉ ምስጋናዬንና ልባዊ ሰላምታዬን አቀርብላቸዋልሁ። ፓናማ መልካም ጥሪ የምነገርባት አገር ናት በማለት እውቅናን የምንሰጠው፣ ሕዝቦቿ ለፓናማ እድገት ተስፋን በመሰነቅ በጋራ መስራታቸውን በመስማታችንና በማየታችን ነው። የጥቂት ሰዎች ፍላጎትን በማስቀረት የጋራ ጥቅምን ማስከበር የሚቻለው የአገርን የተፈጥሮ ሃብት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል በጋራ የመወሰን መብት ሲረጋገጥ ነው።             

ወጣቶች በደስታና በፍላጎት ተነሳስተው፣ አስተያየታቸውን በነጻነት የመግለጽ ችሎታቸውንም በመጠቀም፣ በመሪነት ደረጃ ላይ ለሚገኙት የሚያሰሙት ጥያቄ፣ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በተገቢና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም ተግባር ላይ እንዲያውሉት ነው። ጥያቄያቸውና ፍላጎታቸው መሪዎቻቸው ሌሎችንና ዓለማችንንም ለማገልገል የተሰጣቸውን ሃላፊነ ግልጽ በሆነ መንገድ በተግባር እንዲያከናውኑ ነው።    

ፓናማ የተስፋ ምድር ናት፣

በእነዚህ ቀናት ውስጥ ፓናማ የምትጠቀሰው ለአካባቢው አገሮች እንደ ምቹ የኤኮኖሚ ማዕከልና ሕዝቦች ከቦታ ወደ ቦታ የሚሸጋገሩባት አገር መሆኗ ብቻ ሳይሆን የተስፋም አገር መሆኗ ነው። ከአምስቱ አሕጉራት ለመጡት ወጣቶች የመገናኛና የመተዋወቂያ አገር፣ ምኞታቸውንና ሕልማቸውን ይዘው የመጡባት አገር ሆናለች። በዓላቸውን እያከበሩ በሕብረት የሚጸልዩባት፣ በጥልቅ ፍላጎት በመነሳሳት የሚኖሩባትን ዓለም የተሻለች ለማድረግ ያላቸውን ምኞትና ሃሳብ የሚጋሩባት አገር ሆናለች። የዓለም ወጣቶች በፓናማ ተገናኝተው ይህን በማድረጋቸው፣ ህብረት፣ የፈጠራ ችሎታን ማሳደግና መተጋገዝ፣ ብቸኝነትን አስወግዶ ዓለምን መልካም የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ይገነዘቡታል። ለዚህ አብረው ማቀዳቸውና መስራታቸው ሰብዓዊ መብታቸው ነው።

በመጨረሻም ይህን 34ኛውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ለማዘጋጀት የበኩላችሁን አስተዋጽዖን ላበረከታችሁ በሙሉ ምስጋናዬን እያቀርብኩ፣ ክቡር ፕሬዚደንትንና በዚህ ስፍራ የተገኛችሁትን በሙሉ፣ በብዙሃን መገናኛዎችም በኩል ከእኛ ጋር መሆንን ለመረጣችሁ በሙሉ ምስጋናዬን በማቅረብ፣ ለጋራ ጥቅም በምታደርጓቸው ጥረቶች በሙሉ መልካም ተስፋንና ደስታ እንዲበዛላችሁ እመኛለሁ”። 

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
25 January 2019, 15:40