ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ከፓናማ መልስ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ

ከጥር 14-19/2011 ዓ.ም “እነሆኝ  የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ” (ሉቃ 1፡38) በሚል መሪ ቃል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተገኙበት በፓናማ ሲካሄድ የቆየው 34ኛው ዓለማቀፍ የወጣቶች ቀን በጥር 19/2011 ዓ.ም በሰላም መጠናቀቁ ይታወቃል። በዚህ በ34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ከአምስት አህጉራት የተውጣጡ ከ167,000 በላይ ወጣቶች ተሳታፊ እንደ ነበሩም ቀደም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን በዚህ 34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ማገባደጃ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባደረጉት ንግግር መጪው 35ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በፖርቹጋል ዋና ከተማ በሌዝቮን እንደ ሚደረግ ቅዱስነታቸው ገለጸዋል፣ ከዚያም በኋላ 34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን መጠናቀቁ ይታወሳል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ይህ 34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ከተጠናቀቀ በኋላ ቅዱስነታቸው በጥር 19/2011 ዓ.ም ወደ ሮም  በአውሮፕላን እየተመለሱ በነበሩበት ወቅት እንደ ተለመደው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ቅዱስነታቸው ምላሽ መስጠታቸው የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ ታዳጊዎችን ከጥቃት መከላከል፣ ጽንስ ማስወረድን፣ ስደተኞችን እና በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አስቸጋሪ በሚባሉ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ አገራትን  በተመለከተ ጋዜጠኞ ለቅዱስነታቸው ጥያቄዎችን ማንሳታቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸውም ለቀረበላቸው ጣያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠታቸውን ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በሚቀጥለው የካቲት ወር ውስጥ ታዳጊዎች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ እና አካላዊ ጥቃቶችን በተመለከተ የሚካሄደውን ስብሰባ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ቅዱስነታቸው በሚቀጥለው የካቲት ወር ውስጥ ታዳጊዎችን ከጥቃት እንከላከል በሚል ዓላማ የሚካሄደው ስብሰባ በታዳጊዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ሙሉ በሙሉ ያስቆማል የሚል እምነት እንደ ሌላቸው ገልጸው፣ ምክንያቱም ይህ በታዳጊዎች ላይ የሚቃጣው ጾታዊ እና አካላዊ ጥቃት ሰብዐዊ ችግር በመሆኑ የተነሳ ይቀንስ ይሆናል እንጂ ሙሉ በሙሉ ማስቆም ግን እጅግ ከባድ መሆኑን ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

በማህጸን ውስጥ ላለው ሕጻን መራራት ያስፈልጋል

“በጣም ብዙ የሚባሉ ሴቶች በአጋጣሚ ወይም ደግሞ ሆን ብሎ በሚከሰት እርግዝና የተነሳ በጣም ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደ ሚገኙ፣ በአንጻሩ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ጽንስ ማስወረድ በፍጹም እንደ ማትፈቅድ፣ እርሳቸው (ማለትም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ) ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የምሕረት መልእክት ያስተላልፋሉ፣ ነገር ግን ብዙ ሴቶች በስቃይ ውስጥ ይገኛሉ፣ ይህንን እንዴት የመለከቱታል?” ብሎ አንድ ጋዜጠኛ ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ቅዱስነታቸው “በዚህ ዓይነት ስቃይ ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን ስቃያቸውን እንደ ሚጋሩ እና እነርሱንም እንደ ሚያከብሩ” ገልጸው “ነገር ግን የምሕረት መልእክት ለሁሉም ሰዎች የተላለፈ መልእክት ነው፣ ሌላው ቀርቶ ይህ የምሕረት መልእክት ገና ያልተወለዱ በማህጸን ውስጥ ያሉ ሕጻናትንም ሳይቀር እንደ ሚመለከት” ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል። “ጽንስ የሚያስወርዱ ሴቶች ይህንን ተግባር ከመፈጸማቸው በፊት በምንም ዓይነት ሁኔታ የተፈጠረ ሕጻን ቢሆንም በማህጸን ውስጥ ላለው ሕጻን ግን መራራት ያስፈልጋል” ያሉት ቅዱስነታቸው ጽንስ ላስወረዱ ሴቶች የሚደረገው ምሕረት “አስቸጋሪ ምሕረት” መሆኑን ገልጸው አስቸጋሪ የሚሆነው ግን “ጽንስ ላስወረደች ሴት ምሕረት ማድረጉ ላይ አይደለም፣ ምክንያቱም እግዚኣብሔር ሁሌም ቢሆን መሃሪ ነው፣ ነገር ግን አስቸጋሪ የሚሆነው ሁኔታ ሴቲቱ ጽንስ ካስወረደች በኋላ የሚደርስባት የአዕምሮ ስቃይ ከፍተኛ መሆኑ” ደግሞ ሁኔታውን እንደ ሚያወሳስበው ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል። በመሆኑም ጽንስ በማስወረዳቸው የተነሳ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን ማጽናናት፣ ማገዝ እና አብሮዋቸው መሆን እንደ ሚገባ የገለጹት ቅዱስነታቸው በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ጽንስ ማስወረድ ማለት በእውነት ምን ማለት እንደ ሆነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማገዝ እንደ ሚገባ ጨምረው ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ ጽንስ ያስወረዱ ሴቶች ወደ ንስሐ እንዲመጡ በማድረግ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በቅድሚያ ሳይወለድ በአጭሩ እንዲቀጭ ከተደረገው ልጃቸው ጋር በመንፈስ እርቅ እንዲፈጥሩ ማድረግ፣ ይህንን ስህተት የፈጸሙ ሴቶች የሰሩት ስህተት ከፍተኛ መሆኑን እና የሰው ነፍስ ማጥፋታቸው ከፍተኛ ኃጢኣት መሆኑ እንዲሰማቸው ማድረግ፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በዚህ ምክንያት የደርሰባቸውን ስቃይ እና እንግልት የሚገልጽ ታሪካቸውን በጥሞና ማዳመጥ፣ ከዚያም በኋላ እነዚህን ሁሉ አሳዛኝ ተግባሮች እና ስቃዮች ለእግዚኣብሔር እንዲያቀርቡ በመርዳት ወደ እምነት መንገድ እንዲመለሱ ማገዝ ያስፈልጋል።

ብዙ ወጣቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት እያቆሙ ነው

“ብዙ ወጣቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት እያቆሙ ነው፣ ለምንድነው እንዲህ እየሆነው?” በማለት አንድ ጋዜጠኛ ለቅዱስነታቸው ላቀረበው ጥያቄ ቅዱስነታቸው ሲመልሱ “ይህም የሆነበት ምክንያት በዋነኝነት ክርስቲያኖች ለወጣቱ ተገቢ የሆነ ምስክርነት ባለመስጠታቸው”  እንደ ሆነ ገልጸው “በተለይም ደግሞ ቀሳውስት እና ጳጳሳት፣ እንዲሁም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሳይቀር ተገቢውን ምስክርነት ባለመስጠታችን የተነሳ የተከሰተ ችግር ነው” ብለዋል።

“ከቤተ ክርስቲያን እረኞች ባሻገር ግብዝ የሆኑ ክርስቲያኖች ሕዝቡን ከቤተ ክርስቲያን እንዲነጠል በማድረግ ላይ እንደ ሚገኙ” የገለጹት ቅዱስነታቸው “የዚህ ዓይነት ግብዝ የሆኑ ክርስቲያኖች ለሕዝቡ ምስክርነት መስጠት ካልቻሉ፣ ራሳቸውን ካቶሊክ ነን ብለው መጥራት እንደ ማይኖርባቸው” ገልጸው በዚህ ረገድ እነደ እነዚህ ያሉ ግብዝ ክርስቲያኖች ምን አልባት ራሳቸውን “በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስርዓት ያደጉ እንደ ሆኑ፣ ነገር ግን አሁን ሙቅ ወይም ቀዝቃዛ ያልሆነ፣ ነገር ግን ለብ ያለ ወይም ዓለማዊ አድርገው ራሳቸውን መቁጠር ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

ለካህናት ጋብቻ መፍቀድን በተመለከተ

ካህናት ሚስት እንዲኖራቸው ፍቃድ መስጠትን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቅዱስነታቸው የሰጡት ምላሽ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደ ነበረ አስታውሰው እርሳቸውም በወቅቱ የላቲን ስርዓት የሚከተሉ ካህናት “በድንግልና የመኖር ሕግን በመቀየር ካህናት ሚስት እንዲያገቡ ከመፍቀድ ይልቅ ሕይወቴን አሳልፌ ለመስጠት እመርጣለሁ” ብለው እንደ ነበር  ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። “እኔም በበኩሌ” አሉ ቅዱስነታቸው ለጥያቄው የራሳቸውን ምላሽ ለመስጠት በመዘጋጀት “እኔም በበኩሌ በግሌ በድንግልና መኖር ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ጸጋ በመሆኑ፣ ይህንን የድንግልና ሕይወት ከካህናት ሕይወት በመነጠል ሌላ አማራጭ ማቅረብ አልፈልግም” በማለት ምላሽ መስጠታቸው የገለጸ ሲሆን “ነገር ግን ይህንን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ዝግ ከማድረግ ይልቅ በዚህ ዙሪያ ሰፊ ጥናቶች እንዲካሄዱ በማደርግ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ቦታ እና ጊዜ የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት ግን እንደ ሚያስፈልግ” ቅዱስነታቸው አጽኖት ሰጥተው ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቶች ውስጥ የስነ-ፆታ ትምህርት መስጠት አስፈላጊነት በተመለከተ

“በትምህርት ቤቶች ውስጥ የስነ-ፆታ ትምህርት መስጠት አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ ወይ?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቅዱስነታቸው ሲመልሱ “በትምህርት ቤቶች ውስጥ የስነ-ፆታ ትምህርት መስጠት አስፈላጊ እንደ ሆነ” ገልጸው ነገር ግን ይህንን አጋጣሚ በመጠቀመ “በእውቀት ሃሳብ ቅኝ ግዛት ውስጥ ወጣቶችን በማስገባት” ወጣቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እንዳያስከትል ጥንቃቄ ማድረግ እንደ ሚገባ ገልጸው የስነ-ፆታ ትምህርት በዋነኝነት ሊሰጥ የሚገባው ግን በቤት ውስጥ በቤተሰብ አማካይነት ቢሆን እንደ ሚመርጡ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ወቅታዊውን የቬንዙዌላ ጉዳይ በተመለከተ

ወቅታዊውን የቬንዙዌላን ጉዳይ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቅዱስነታቸው በሰጡት ምላሽ እንደ ገለጹት  “ሁሉም የቬነዝዌላ ሕዝቦች በስቃይ ውስጥ በመሆናቸው የተነሳ” እርሳቸው የሚደግፉት ሁሉንም ቬንዙዌላዊያንን እንደ ሆነ ገልጸው እኔን እያስፈራኝ የሚገኘው አሳሳቢው ጉዳይ በዚያች አገር የሚከሰተው የደም መፋሰስ እጅግ በጣም እንደ ሚያሳስብቸው ገልጸው፣ ማነኛውም ዓይነት ግጭት እና ብጥብጥ እኔን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስጨንቀኝ ተግባር ነው” ብለዋል።

ስደተኞችን በተመለከተ

ስደተኞችን በተመለከተ ደግሞ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቅዱስነታቸው በሰጡት ምላሽ እንደ ገለጹት “በሁኑ ወቅት የሚታየው የስደተኞች ችግር የተወሳሰበ ችግር እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ነገር ግን ዋናው አስፈላጊ ነገር ሊሆን የሚገባው “ስደተኞችን ለመቀበል” የተዘጋጀ የተከፈተ ልብ አስፈላጊ እንደ ሆነ ገልጸው በዚህ ረገድ ስደተኞችን የሚቀበሉ መንግሥታት ስደተኞች ከማኅበርሰቡ ጋር ተግባብተው እና ተዋህደው ይኖሩ ዘንድ መትጋት ይኖርባቸዋል ብለዋል። ስደተኞችን በተመለከተ ከአውሮፓ አህጉር ግሪክ እና ጣሊያንን፣ ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ደግሞ ሊባኖስን እና ዮርዳኖስን በብነት በማንሳት ማመስገናቸውን ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “የስደተኞች ጉዳይ ውስብስብ በመሆኑ የተነሳ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ያለ አንዳች ጭፍን ጥላቻ" መናገር እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

ፓናማ ድንቅ የሆነች አገር ናት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በፓናማ ተካሄዶ የነበረውን 34ኛውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ከተሳተፉ በኋላ ወደ ሮም በመመለስ ላይ በነበሩበት ወቅት ከላይ የተጠቀሱትን ከጋዜጤኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡ በኋላ ጋዜጠኞች ላቀረቡላቸው ጥያቄ እና እያበረከቱት ለሚገኙት አስተዋጾ ከፍተኛ የሆነ አድናቆት እንዳላቸው ገልጸው እና አመስግነው “ይህንን ቃለ ምልልስ ከማጠናቀቄ በፊት ስለ ፓናማ አንድ ነገር ለማለት ወዳለሁ” ብለው “ፓናማ በጣም ድንቅ የሆነች አገር ናት፣ በቆይታዬ ይህንን ተረድቻለሁ” በመጨረሻም በአውሮፓ አህጉር ብዙን ጊዜ የማናያቸውን ነገር ግን በፓናማ በሰፊው ከሚንጸባረቁ ነገሮች መካከል አንድ ነገር ለመጥቀስ እፈልጋለሁ፣ በፓናማ የሚኖሩ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን በሚያሳድጉበት ወቅት ‘የእኔ ድል፣ የእኔ ኩራት፣ የእኔ የመጪው ጊዜ ተስፋ” በማለት ልጆቻቸውን እንደ ሚያሳድጉ ገልጸው “እኛ በምንኖርበት በአውሮፓ አህጉር እና በጣሊያን የምንገኝ ቤተሰቦች የእኛስ ኩራት የሚመነጨው ከየት ነው? ከአገር ጎብኚዎች ብዛት የተነሳ ነው? ካለን ሕንጻዎች የተነሳ ነው? ከውሾቻችን ጋር በመሆናችን ነው? ወይስ ከልጆቻችን ጋር? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ የገባል ካሉ በኋላ ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

29 January 2019, 13:32