ፈልግ

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በገና በዓል ዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ ባደርጉበት ወቅት

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ “በገና በዓል እግዚኣብሔር ለእኛ አዲስ ሕይወት የሰጠናል” ማለታቸው ተገለጸ።
የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስትያን ማኅበርሰቦች ዘንድ በታኅሳስ 16/2011 ዓ.ም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት የገና በዓል ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህ ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን የሚከበርበት የገና በዓል በታኅሳስ 15/2011 ዓ.ም ምሽት ላይ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መሪነት በተደርገው የዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ በርካታ ምዕመና በተገኙበት መከበሩን ከደረሰን መረጃ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “የገናን በዓል በእውነተኛ መንፈስ ማክበር የምንችለው የኢየሱስን ፍቅር ስንከተል ብቻ ነው” ማለታቸውን ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “በገና በዓል እግዚኣብሔር ለእኛ አዲስ ሕይወት የሰጠናል” ብለዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስትያን ማኅበርሰቦች ዘንድ በታኅሳስ 16/2011 ዓ.ም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት የገና በዓል በተከበረበት ወቅት በዚህ በዓል ዋዜማ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያሰሙትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

ዮሴፍም ከእጮኛው ከማርያም ጋር “ቤተልሔም ወደ ምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ሄዱ” (ሉቃስ 2፡4)። ዛሬ ምሽት የገናን በዓል ምስጢር በሚገባ ለማወቅ ወደ ቤተልሔም እንሂድ።
ቤተልሔም፡ የሚለው መጠርያ ትርጉሙ የዳቦ ቤት ማለት ነው። በዚህ ቤት ውስጥ ጌታ ዛሬ ሁሉንም የሰው ልጆች ልያገኛቸው ይፈልጋል። ለመኖር ምግብ እንደ ምያስፈልገን እርሱ በሚገባ ያውቃል። የዚህ ዓለም ምግብ በራሱ ብቻ ልባችንን እንደ ማያጥግብም ያውቃል። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እንደ ተጠቀሰው የሰው ልጅ ቀደምት ኀጢአት ምግብን ከመውሰድ ጋር ተያያዥነት እንዳለው ይገልጻል፡ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን "ፍሬውን ከወሰዱ በኋላ በሉ” በማለት የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ (ኦ.ዘፍ. 3፡6) ይገልጻል። ፍሬውን ከወሰዱ በኋላ በሉ። የሰው ልጅ ስግብግብና ክፉ ሆነ። በዘመናችን ለብዙዎች የሕይወት ፍቺ ቁሳዊ የሆኑ ንብረቶችን ከመጠን በላይ በሆነ መልኩ ማጋበስ ማለት ነው የሚለውን ትርጓሜ እያሰማ መጥቱዋል። ዛሬም ቢሆን ያለ ርኅራኄ የሚታየው ስግብግብነት በሁሉም የሰው ዘር ታሪክ ውስጥ እስካሁን ጊዜ ድረስ የሚታይ ሲሆን እርስ በእርሱ በሚጋጭ በሚመስል መልኩ ደግሞ በጣም ጥቂት የሚባሉ ሰዎች ከመጠን በላይ ምቹ በሆነ መልኩ የሚመገቡ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ በጣም ብዙ የሚባሉ የዓለማችን ሕዝቦች ደግሞ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን እለታዊ የሆነ እንጀራ ማግኘት ተስኖዋቸው በስቃይ ውስጥ ሆነው በመኖር ላይ ይገኛሉ።
ቤተልሔም የታሪክን አቅጣጫ የሚቀይር የመለወጥ ነጥብ ነው። በዚያ የዳቦ ቤት እግዚኣብሔር በበረት ውስጥ ይወለዳል። እርሱ "እኔ የእናንተ ምግብ የሆንኩኝ እዚህ እገኛለሁ" ለማለት የፈለገ ይመስላል። እርሱ ከእኛ አይወስድም ነገር ግን እንድንበላው ይሰጠናል፣ እሱ ተራ የሆኑ ነገሮችን ብቻ አይሰጠንም፣ ነገር ግን ሁለንተናውን ይሰጠናል። በቤተልሔም እግዚአብሔር ሕይወታችንን አልወሰደም ነገር ግን ሕይወቱን እንደሰጠ ይነግረናል። ከውልደታችን ቀን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ወስደን መብላት ለለመድን ለእኛ ኢየሱስ “ውሰዱና ብሉ” ይለናል። “ይህ ሥጋዬ ነው” (ማቴ፡ 26፡26)። በቤተልሔም የተወለደው ሕጻኑ ልጅ ሕይወታችንን በአዲስ መልክ እንኖር ዘንድ ይነግረናል፣ በስግብግበነት መንፈስ እንድንበላ እና ንብረት እንድናከማች ሳይሆን ነገር ግን ካለን በማካፈል እና በመስጠት እንድንኖር ይመክረናል። አምላክ የእኛ ምግብ ለመሆን እራሱን ትንሽ አድርጎ ያቀረባል። የህይወት እንጀራ የሆነውን እርሱን በመመገብ ነገሮችን የማከማቸት እና በስግብግብነት የመሰብሰብን መንፈስ አስወግደን በፍቅር እንደገና በአዲስ መልክ እንድንወለድ ያደርገናል። ኢየሱስ "ከዳቦ ቤት" (ቤተልኤም) ሆኖ ወደ ቤታችን እኛን በመመለስ የእግዚአብሔር ቤተሰብ እንድንሆን፣ ለባልነጀራዎቻችን ወንድሞች እና እህቶች መሆን እንችል ዘንድ ወደ ቤቱ የመልሰናል። እርሱ በተወለደበት በከብቶች በረት ፊት ቆመን ስንመለከት የሕይወት ምግብ የሚሆነን ቁሳዊ ሃብት ሳይሆን ፍቅር እንደ ሆነ፣ ሆዳምነት ሳይሆን ልግስና እንደሆነ፣ ጩኸት ሳይሆን ሰላማዊ እና የዋህ መሆኑን እንረዳለን።
ጌታ በእየቀኑ መመገብ እንደሚያስፈልገን ያውቃል። ለዛ ነው ከቤተልኤም ከከብቶች በረት ውስጥ አንስቶ የፋሲካ እራት እስከ በላበት የላይኛው ክፍል አንስቶ ሕይወቱን በየቀኑ ለእኛ የሚያቀርበው በዚህ ምክንያት ነው። ዛሬም በመሰውያው በመበረ ታቦት ላይ የሚቆረስ ዳቦ ለእኛ ራሱን ሰጥቱዋል፣ እርሱ ወደ ቤታችን ገብቶ ከእኛ ጋር ለመመግብ ፈልጎ በራችንን በማንኳኳካት ላይ ይገኛል። በገና በዓል ወቅት እኛ በምድር ላይ ሆነን ከሰማይ የወረደውን ኢየሱስን የሕይወት እነጀራችን አድርገን እንቀበለዋለን። ይህ በፍጹም የማይለወጥ ምግብ ነው፣ አሁንም ቢሆን በምድር ላይ ሆነን የዘላለም ህይወት ቅምሻ እንዲኖረን ያስችለናል።
በቤተልሔም ውስጥ የእግዚአብሔር ሕይወት ወደ ልባችን ገብቶ በዚያ መኖር እንደ ጀመረ መገንዘብ እንችላለን። ይህን ስጦታ ከተቀበልን ከእያንዳንዳችን ሕይወት ጀምሮ ታሪክ ይቀየራል። ኢየሱስ በልባችን ውስጥ መኖር ከጀመረ የህይወቴ ማዕከል የሚሆነው የራስ ወዳድነት መንፈስ ሳይሆን ነገር ግን የተወለደው እና ለእኔ ሲል ለፍቅር የሚኖረው እርሱ ይሆናል ማለት ነው። ዛሬ ምሽት ወደ ቤተልሔም እንድንሄድ መልእክት ያስተላለፉትን የመላእክት ድምጽ ስንሰማ . . . የሕይወት እንጀራ ምንድነው፣ ያለእርሱ ልኖር የማልችለው ያ የሕይወት እንጀራ ምንድነው? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። ጌታ ነው ወይስ ሌላ ነገር ነው ለሕይወቴ የምያስፈልገኝ? በዚህም ሁኔታ ለእኛ ሲል በድህነት የተወለደውን አዲስ ሕጻን ስሜት መረዳት እንጀምራለን፣ አዲስ የሕይወት መስመር ማየት እንጀምራለን፣ በትህትና ለመኖር እንመኛለን። በእርግጥ እነዚህ ሁሉ ቁሳዊ የሆኑ ነገሮች እና ሕይወቴን የሚያወሳስቡ ነገሮች ለኑሮዬ ያስፈልጋሉ ወይ? ብለን እስቲ ራሳችንን እንጠይቅ። እነዚህ ሁሉ አስፈላጊ ያልሆኑ ተጨማሪ ነገሮች ሳይኖሩኝ እና የበለጠ በጣም ትሁት በሆነ መልኩ እና ቀለል ባለ ሁኔታ ህይወቴን ለመኖር እችላለው ወይ? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። ኢየሱስ በተኛበት ቤተልሔም ድረስ የተጓዙት ሰዎች ሁሉ ማርያምን፣ ዮሴፍን እና እረኞችን ጨምሮ በጉዞዋቸው ወቅት እንጀራ የሆናቸው ኢየሱስ ራሱ ነበር። በዚህ በገና ወቅት “እንጀራችንን ከሌሎች ምንም የሚበላ ነገር ከሌላቸው ሰዎች ጋር እንካፈላለን ወይ? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ።

ቤተልሔምን እንደ ዳቦ ቤት አድረገን ወስደናት ነበር በመቀጠል ደግሞ ቤተልሔም የዳዊት ከተማ እንደ ነበረች የሚገልጸውን ምሳሌ እንውሰድ። በዚያ ቦታ ወጣቱ ዳዊት እረኛ ነበር፣ እንደዚሁም እግዚአብሔር የሕዝቡ እረኛና መሪ እንዲሆን መርጦታል። በገና በዓለ ወቅት በዳዊት ከተማ የተወልደውን ሕጻን ቀድመው ያዩት እረኞች ነበሩ። ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚንግረን “በዚያን ወቅት እረኞቹ በፍርሃት ተሞልተው ነበር” (ሉቃ 2፡9) ይለናል። ነገር ግን መልኣክት ወደ እነርሱ ቀርበው “አትፍሩ” እንዳሉዋቸው ይገልጻል። ይህንን “አትፍሩ” የሚለውን ሐረግ በወንጌል ውስጥ ስንት ጊዜ እናነባለን? እግዚአብሔር እኛን በሚፈልግበት ወቅት ያለማቋረጥ ይህንን ቃል የሚደጋግም ይመስላል። ምክንያቱም ከመጀመርያው ጊዜ አንስቶ እኛ በኃጢኣታችን የተነሳ እግዚኣብሔርን በጣም ስለምንፈራው ነው፣ አዳም ኃጢኣት ከሠራ በኋላ “አንተን ስለፈራሁ ተደበኩኝ” (ዘፍ. 3፡10) በማለት የተናገረው በዚሁ ምክንያት ነው። በቤተልሄም የታየው ፍርሃት የእዚህ አንዱ አካል ነው፣ ምክንያቱም የሰው ልጅ ለእግዚኣብሔር “እንቢየው አልታዘዝም ሲል” እግዚኣብሔር ደግሞ በቀጣይነት የሰውን ልጅ በመፈለግ “አይዞህ ይችላል” በማለት የሚፈልገው በዚሁ ምክንያት ነው። ከእኛ ጋር በማነኛው ሁኔታ የሚኖረው እርሱ እግዚኣብሔር ነው። እናም የእርሱ በመካከላችን መገኘት ፍርሀት የሚፈጥርብን ቢሆንም እርሱ ግን ትልቅ ሆኖ ሳለ እንዳንፈራው ርኅራኄ በተሞላው በሕጻን ልጅ ተመስሎ መጣ። ይህ “አትፍሩ” የሚለው ቃል ለቅዱሳን ያልተነገረ፣ ነገር ግን በእዚያን ወቅት በንጹህ ልቦና እግዚአብሔርን በማምለክ የሚታወቁት በጣም ትሁት ለነበሩ እረኛ ተብለው ይጠሩ ለነበሩ ሰዎች የቀረበ ጥሪ ነው። የዳዊት ልጅ በእረኞች መካከል የተወለደው ማንም ሰው መቼም ቢሆን ብቻውን እንደ ማይሆን እና እንደ ማይገለል ያሳያል፣ ምክንያቱም የእኛ ፍራቻዎቻችንን በሙሉ እንድናሸንፍ የሚረዱን እረኞች አሉ፣ የሚወዱን ያለምንም ልዩነት የሚቀርቡን እረኞች ስላሉን ነው።
የቤተልሔም እረኞች ጌታን እንዴት መገናኘት እንደ ምንችል ያስተምሩናል። በሌሊት ነቅተው ይጠብቁ ነበር፣ እነርሱ አይተኙም፣ እነርሱ ብዙን ጊዜ ኢየሱስ እኛም እንድንፈጽመው የሚጠይቀንን “ነቅታችሁ ጠብቁ” የሚለውን ቃል በተግባር ላይ አውለውታል (ማቴ. 25፡12, ማር. 13፡35, ሉቃ. 21፡36) እንደ ተጠቀሰው። በጨለማ ውስጥ ንቁ ሆነው ይጠባበቃሉ፣ በዚያም ወቅት “የእግዚኣብሔር ብርሃን በእነርሱ ላይ ይሆናል” (ሉቃ 2፡9)። ለእኛም እንዲሁ ይሆናል። በህይወታችን ውስጥ ያጋጠሙትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በጨለማ ውስጥ ለመጋፈጥ ስንሞክር ጌታ ወደ እኛ በመምጣት በሕይወታችን መታየት ይጀምራል፣ ከእዚያም ሕይወታችንን ይቀይራል። ወይም ደግሞ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የእራሳችን ጥንካሬዎችና ችሎታዎች በሚሆኑበት ጊዜ ህይወታችንን በምንፈልግበት ወቅት እርሱ የብርሃን ምልክት ሊሆነን ይችላል፡ ልባችን ከእግዚአብሔር ብርሃን ጋር ተጣብቆ ይቆያል። ጌታ እንድንጠብቀው ይፈልጋል፣ እኛ በአልጋችን ላይ ተንጋለን ተኝተን እርሱን መጠበቅ አንችልም። እረኞቹ በፍጥነት ተነስተው ሄዱ ይለናል፣ እኛም ብንሆን “በፍጥነት ተነስተን እንድንሄድ ይመክረናል” (ቁ. 16)። እነሱ በስፍራው እንደ ደረሱ እንዲያው ዝም ብለው ቆመው በማሰብ እና ምንም ተጨማሪ ነገር ሳያደርጉ በዚያው ዝም ብለው ተገትረው የቆሙ ሰዎች አልንበሩም። ነገር ግን መንጋቸውን ባለበት ቦት ትተው ተነስተው በፍጥነት ሄዱ፣ ለእግዚኣብሔር ሲሉ መንጋቸውን ጥለው በዚህም ምክንያት የራሳቸውንን እና የመንጋዎቻቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለው ሄዱ። ሁሉንም ነገር ለእግዚኣብሔር ብለው ቀሪውን ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጣሉ። በቤተልሄም በከብቶች በረት ውስጥ የተኛውን ሕጻኑን ኢየሱስን ካዩትም በኋላ እዚያው አርፈው አልተቀመጡም፣ በሄዱበት ፍጥነት ተነስትው ወደ እየመጡበት በመመለስ ለሰዎች ሁሉ ስለሕጻኑ ማንነት መሰከሩ “በምስክርነታቸውን የሰሙ ሰዎች ሁሉ ይህንን ከእረኞች በመስማታቸው ተደንቁ” (ሉቃስ 2፡18)።
ተግቶ መጠበቅ፣ ወደ ፊት በፍጥነት መሄድ፣ ለአደጋ ማጋለጥ፣ ተመልሶ ውበትን ለሌሎች መተረክ እነዚህ ነገሮች ሁሉ የፍቅር ተግባሮች ናቸው። መልካም የሆነው እረኛ፣ ለበጎቹ ሕይወቱን ለመስጠት በገና እለት ወደ እኛ የመጣው፣ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በፋሲካ ሰሞን ጴጥሮስን ጥያቄ ይጠይቀዋል፣ ይህም ጥያቄ እኛን ሁላችንን ይወክለናል እንዲህም ይላል “ትወደኛለህን?” (ዮሐ. 21፡15)። የመንጋው የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው ይህን ጥያቄ በምንመልስበት አግባብ ነው። ዛሬ ማታ እኛም በተመሳሳይ ቃል “እወድሃለሁ” ብለን እንድንመልስለት ኢየሱስ ይጠይቀናል። እያንዳንዳችን የምንሰጠው ምላሽ ለአጠቃላይ መንጋው በጣም ጠቃሚ የሆነ ምላሽ ነው።
እረኞቹ “ወደ ቤተልሔም እንሂድ” ብለው ወደ እዚያው እንዳቀኑ ሁሉ እኛም ወደ እዚያው እናቅና። የራስ ወዳድነት መንፈስን ሁሉ አስወግደን ወደ ቤተልሔም እንሂድ፣ ራሳችንን በዓለማዊ መንፈስ ከመሸበብ ይልቅ፣ ቁሳቁሶችን የማጋበስ ፍላጎቶቻችንን አሸንፈን ወደ ቤተልሔም እንሂድ።
ጌታ ሆይ አንተ በዚያው በቤተልሔም ሆነ ስለምትጠብቀኝ ወደ እዚያው ለመሄድ እፈልጋለሁ ማለት ይኖርብናል። አንተ በግርግም ውስጥ የተኛህ ሕጻን የህይወቴ እንጀራ እንደሆንክ እገነዘባለሁ። እኔም ደግሞ በምላሹ ለዓለም የምሰጥ እንጀራ መሆን እችል ዘንድ በቅድሚያ ያንተ የፍቅርህ መዓዛ ያስፈልገኛል። አንተ መላክም እረኛ የሆንክ እኔን በትክሻህ ላይ አድርገ ውሰደኝ፣ በአንተ መወደዴ ሌሎችን እንድወድ ያደርገኛል። በዚህም መልኩ እኔ “ጌታ ሆይ እንተ ሁሉንም ነገር ታውቃለህ፣ እንደ ምወድህም ታውቃለህ” (ዮሐ. 21፡17) ብዬ በመናገር ይህንን የገና በዓል በመልካም ሁኔታ ማክበር እችል ዘንድ እርዳን።
 

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
25 December 2018, 18:25