ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እንደ ማርያም እነሆኝ በማለት ራሳችንን ለእግዚአብሔር መስጠት ይኖርብናል”

የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ባለፈው ቅዳሜ ኅዳር 29/2011 ዓ.ም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለዓዳም ኃጢያት መጸነሱን የሚዘክረው የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ በዓል በታላቅ መንፈሳዊነት በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህ በዓል በቫቲካን በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ማለፉን ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች በእለቱ በተነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ላይ መሰረቱን ባደርገው ስብከት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “እንደ ማርያም እንሆኝ እንዳልከው ይሁንልኝ” በማለት ራሳችንን በዕየለቱ ለእግዚኣብሔር መስጠት ይኖርብናል” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባልፈው ቅዳሜ ኅዳር 29/2011 ዓ.ም የጽነሰተ ማርያም አመታዊ በዓል በተከበረበት ወቅት ያሰሙትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አስናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! መልካም በዓል ይሁንላችሁ!

የዛሬው የእግዚኣብሔር ቃል የተለየ አማራጭ ይሰጠናል። በመጀመርያው ምንባብ (ዘ.ፍጥ. 3፡9-15,20) ውስጥ በመጀመርያ ላይ የሰው ልጅ ለእግዚኣብሔርን ያሳየውን እንቢተኛነት የሚገልጽ ሲሆን በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ ደግሞ (ሉቃስ (1፡26-38) ማርያም መልኣኩ ገብርኤል ባበሰራት ወቅት ለእግዚኣብሔር “እነሆኝ” በማለት እሽታዋን ስትገልጽ እናያለን። በሁለቱም ምንባባት ውስጥ ሰውን የሚፈልገው እግዚአብሔር መሆኑን እንመለከታለን። በመጀመሪ ደረጃ ግን አዳም ኃጢአት ከሰራ በኃላ በተደበቀበት ወቅት “የት ነህ ያለኸው?”(ዘፍ 3,9) በማለት ጠይቆት እንደ ነበረ የሚገልጸውን ክፍል የምናገኝ ሲሆን እርሱም “እኔ ራሴን ደብቅያለሁ” (ዘፍ. 3፡10) በማለት እንደ መለሰ የሚገልጸውን ምንባብ እናገኛለን። በሁለተኛው ምንባባ ውስጥ ደግሞ እግዚኣብሔር ኃጢኣት ወደ ሌለባት ወደ ማርያም በሄደበት ወቅት ደግም እርሷ “እነሆኝ የእግዚኣብሔር አገልጋይ” (ሉቃ. 1፡38) ብላ እንደ መለሰች የሚገልጸውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል እናገኛለን። “እነሆኝ” የሚለው ቃል እኔ ተደብቅያለሁ ከሚለው ቃል ጋር በጣም ይለያያል ተቃራኒ የሆኑ ቃላት ናቸው። እነሆኝ የሚለው ቃል ለእግዚኣብሔር ተግባር ዝግጁ መሆናችንን የሚገልጽ ቃል ሲሆን ኃጢኣት ደግሞ እንድንደበቅ፣ እንድንገለል፣ ብቻችንን እንድንሆን ያደርገናል።

“እነሆኝ” የሚለው ቃል በሕይወት ሂደት ውስጥ ቁልፍ የሆነ ቃል ነው። ይህ እነሆኝ የሚለው ቃል ከራስ ወዳድነት እና ከራሳችን ፍላጎቶች ነጻ በመሆን በእግዚአብሔር ላይ የተመሰረተ ወደ ቀጥተኛ ህይወት የሚሸጋግረውን የሕይወት ሽግግር ያመለክታል። እነሆኝ የሚለው ቃል ለጌታ ዝግጁ መሆናችንን የሚያመልክት ቃል ነው፣ የራስ ወዳድነት በሽታን የሚፈውስ ነው፣ ለወደፊቱ ሕይወት መድሃኒት ነው፣ የጎደለብንን ነገር የመሙላት አቅም አለው። እነሆኝ የሚለው ቃል ኃጢአት ከጫነብን እርጅና የምንላቀቅበት መንገድ ነው፣ በውስጣችን የወጣትነት መንፈስ እንዲኖር የሚደረግ ሕክምና ነው። እነሆኝ የሚለው ቃል ከእኔ ይልቅ እግዚኣብሔር አስፈላጊ መሆንን እንድረዳ የሚረዳኝ ቃል ነው። ከጌታ ጋር ለመጫወት መፍቀድ ማለት ነው፣ ለእርሱ አስገራሚ እና ድንገተኛ ለሆኑ ስጦታዎች ራሳችንን በትህትና መክፈት ማለት ነው። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ እነሆኝ ማለት ለእግዚኣብሔር ከምንሰጠው ውዳሴ ሁሉ የላቀ ውዳሴ ነው። ታዲያ ለምንድነው እያንዳንዱን ቀናችንን “ እነሆኝ ጌታ ሆይ” ብለን የማንጀምረው ለምንድነው? በእየለቱ ጥዋት ጥዋት “እነሆኝ ጌታ ሆይ እንዳልከኝ ይሁንልኝ” ማለት መልካም የሆነ ነገር ይመስለኛል።

ማርያም “እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” በማለት አክላ ተናገረች። “እንደ እኔ ቃል ሳይሆን” እንዳንተ ቃል ይሁንልኝ ነው ያላችሁ” ለእግዚኣብሔር ቃል ገደብ አላበጀችም። እኔ ለእሱ ጥቂት ነገሮችን እሰጣለው፣ እኔ ፈጥኜ ለእርሱ ይህንን አደርጋለሁ ከዚያም በኃላ ግን እኔ የምፈልገውን አድርጋለሁ” በማለት አላሰበችም። አይደለም እንዲህ አላሰበችም፣ ማርያም እርሷን ሲመቻት ብቻ አለነበረም ጌታን የወደደችው ወይም እርሷ በፈለገችው መንገድ ብቻ አይደለም ጌታን የወደደችሁ። እርሷ በሁሉም ነገሮች ውስጥ በእግዚኣብሔር ታምና ኖረች። ይህ የሕይወት ምስጢር ነው። በሁሉም ነገር ውስጥ በእግዚኣብሔር ታምኖ መኖር ያስፈልጋል። ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ነገር ግን ልክ እንደ አዳም “እኔ ስለፈራው ተደበኩኝ” ብለን መልስ ስንሰጥ ጌታ ይሠቃያል። እግዚአብሔር አባት ነው፣ ከአባቶች ሁሉ የሚበልጥ አባት ስለሆነ የልጆቹን እምነትን ይፈልጋል። በሕይወታችን ውስጥ ስንት ጊዜ ነው እግዚኣብሔርን የተጠራጠርነው! እርሱ እኛን ለመፈተን፣ ነጻነታችንን ሊገፈን፣ ብቻችንን ሊተወን ይችላል በማለት እንጠራጠር ወይም እናስብ ይሆናል። ነገር ግን ይህ ትልቅ ማታለያ ነው፣ ከመጀመርያው ከጥንት ጊዜ ጀመሮ የነበረ ፈተና ነው፣ የዲያቢሎስ ፈታኝ የሆነ ከባድ ፈተና ነው፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለንን መተማመን እንድናጣ የሚያደርገን ፈተና ነው። ማርያም ይህንን ታላቅ የሆነ ፈተና “እነሆኝ” የሚለውን ቃል ተጠቅማ አሸነፈች። እናም ዛሬ የእኛ የማርያምን ውበት እንመለከታለን፣ በንጽህና እና ያለ ኃጢአት መኖሩዋን፣ ለእግዚኣብሔር ሁልጊዜም ገራገር እና ግልጽ ሆና መኖሩዋን የሚያሳይ ውበት በማርያም ውስጥ እንመለከታለን።

ይህ ማለት ደግሞ ማርያም በኑሮዋ ሂደት ውስጥ ሕይወት አልጋ በአልጋ ነበር ማለት ግን አይደለም። ከእግዚኣብሔር ጋር መኖር ማለት ደግሞ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ሁሉ ቅጽበታዊ በሆነ መልኩ ያስወግዳል ማለት ግን አይደለም። ዛሬ በተነበበል ቅዱስ ወንጌል ማብቂያ ላይ “መልኣኩም ከእርሷ ተልይቶ ሄደ” (ሉቃስ 1`38) የሚለውን ማስታወስ ተገቢ ነው። “ከእርሷ ተልይቶ ሄደ” የሚለው ቃል በጣም ጠጣር የሆነ ቃል ነው። መልኣኩ ማርያምን ብቻዋን ጥልዋት መሄዱ አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታን ይፈጥራል። እርሷ በምን ዓይነት መንገድ የእግዚአብሔር እናት እንደምትሆን ታውቅ ነበር-ይህንን በተመለከተ መልኣኩ እንዴት እንደ ሚከሰት ነግሮዋት ነበር- ነገር ግን መልአኩ ለእሷ ብቻ እንጂ ለሌሎች ሰዎች ሰለጉዳዩ አላብራራም ነበር። ችግሩ የጀመረው በፍጥነት ነበረ፣ ከሕግ ውጪ የሆነ ያልተለመደ ሁኔታ ነበር፣ ቅዱስ የዮሴፍን  ለስቃይ የዳረገ፣ የተወጠኑ የሕይወት ዕቅዶችን ያበላሸ፣ የሰዎች መነጋገሪያ የመሆን. . .ወዘተ የመሳሰሉ ችግሮችን ፈጥሩዋል። ነገር ግን ማርያም እነዚህ ችግሮች ቢጋረጡባትም በእግዚኣብሔር መተማመኗን ግን ቀጥላ ነበር። ምንም እንኳን መልኣኩ ትቷት ብሄድም ነገር ግን ከእርሷ ጋር የሚሆን፣ በእርሷ ውስጥ የሚሆን፣ ከእርሷ ጋር አብሮ የሚኖር እግዚኣብሔር እንዳለ ግን በሚገባ አምናለች። በእግዚኣብሔር ተማመነች። እግዚኣብሔርን አመነች። ምንም እንኳን በከፍተኛ ችግር ውስጥ የገባች ቢሆንም ነገር ግን እግዚኣብሔር ከእርሷ ጋር በመሆኑ የተነሳ ሁሉም ነገር መልካም ሆኖ እንደ ሚቀጥል ግን በሚገባ ተማምና ነበር። በዚህ ረገድ ጥበባዊ አመለካከት እንዳለ እንመለከታለን- በችግሮች ላይ ተመርኩዞ መኖር አያስፈልግም- አንዱ ችግር ሲጠንቃቀቅ ሌላ ችግር ይቀጥላል! ነገር ግን በእግዚኣብሔር ላይ መተማመን እና በእየለቱ በእርሱ ላይ በመተማመን በመኖር “እነሆኝ” ማለት ያስፈልጋል። “እነሆኝ” ለእግዚኣብሔር የምንሰጠው ትክክለኛ መልስ ነው። “እነሆኝ” ማለት በራሱ በጣም ትልቅ የሆነ ጸሎት ነው። ያለ አዳም ኃጢኣት የተጸነሰች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እነሆኝ በማለት መኖር የምንችልበትን ጸጋ እንድታሰጠን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

08 December 2018, 16:17