ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ኢየሱስ ጸሎት መጸለይ እንዲይስተምረን መጠየቅ ይኖርብናል” ማለታቸው ተገለጸ።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት በዛሬው እለት ማለትም በኅዳር 26/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደርጉት የጠቅላላ የተምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 11፡1 ተወስዶ በተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ በተጠቀሰው “ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፡ ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን” ብሎ በተናገረው ቃል ላይ መሰረቱን ባደረገው የጠቅላላ የተምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ጸሎት “የመጸለይ መንፈስ እንዲኖረን ከኢየሱስ ልንማር ይገባል” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 26/2021 ዓ.ም በቫቲካን በሚገው በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
“አባታችን ሆይ” በተሰኘው ጸሎት ዙሪያ የምናደርገውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዛሬ እንጀምራለን። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ የጸሎት ሰው እንደ ሆነ የሚያሳዩ ግልጽ የሆኑ መገለጫዎች በብዙ ስፍራዎች ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን፣ ኢየሱስ ይጸልይ ነበር። ምንም እንኳን ከእርሱ ተልዕኮ አስቸኳይነት እና ብዙ ሰዎች ለአጣዳፊ እና አስቸኳይ ጉዳዮቻቸው የሚፈልጉት ቢሆንም ቅሉ ኢየሱስ ብቻውን መሆን እንዳለበት፣ እራሱን በማግለል መጸለይ እንደሚያስፈልገው ተሰምቶት ነበር። የማርቆስ ወንጌል ይህንን የኢየሱስ ተግባር በተመለከተ ኢየሱስ የመጀመሪያውን ይፋ አገልግሎት ከጀመረበተ ጊዜ አንስቶ ስለዚህ ጉዳይ በዝርዝር ይተርካል (ሉቃ. 1፡35)። ኢየሱስ በቅፍርናሆም የነበረው ቆይታ የተጠናቀቀው በክብር እና በድል አድራጊነት ነው። ፀሐይ ከጠለቀች በኃላ ብዙ ቁጥር ያላቸው የታመሙ ሰዎች ኢየሱስ ወደአለበት ሥፍራ ያመጡ ነበር; መሲሑም ይሰብካል ይፈውሳልም። በብዙ ሥቃይ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን እንደ ሚፈውስ የተነገሩት ጥንታዊ ትንቢቶች እና ይህንን አዳኝ የሚጠባበቁ ብዙ ለተሰቃዩ ሰዎች - ኢየሱስ ቅርባቸው ነው፣ ኢየሱስ እኛን የሚያድን እና ነጻ የሚያወጣ አምላካችን ነው። ይሁን እንጂ ያ ሕዝብ ከዚህ ቀደም ናዝራዊ በሆነው ነቢይ ዙሪያ ከሚሰበሰቡ ብዙ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር; አንዳንድ ጊዜ ውቅያኖስ የሚመስሉ ትላልቅ ስብሰባዎች የሚካሄዱ ቢሆንም፣ ኢየሱስ በሰዎች ሁሉ የሚጠበቅ፣ ከእስራኤል ተስፋ የተገኘው ውጤት ነው።
ኢየሱስ ከዚህ ሁሉ ነገር የሚሸሽ አምላክ አይደለም፣ እርሱን እንደ መሪያቸው አድርገው በመረጡት ሰዎች ታግቶ ለመቅረት አልፈለገም። ይህም አንድ መሪን የሚያጋጥመው ፈተና ነው፡ ከሕዝቡ ጋር ባላቸው የጠበቀ ግንኙነት የተነሳ ከሕዝቡ መለየት በጣም ይከብዳቸዋል። ከቅፍርናሆም የመጀመሪያ ምሽት ጀምሮ እርሱ የመጀመሪያው መሲሕ ነው። በሌሊቱ መገባደጃ ላይ ጎህ ሲቀድ ደቀመዛሙርቱ አሁንም እርሱን ፈልገው ሊያገኙት አልቻሉም። ታዲያ የት ነበር? በመጨረሻም ጴጥሮስ ኢየሱስን እራሱን ገለልተኛ በሆነ ቦታ ላይ ብቻውን እስካገኘበት ጊዜ ድረስ ሙሉ በሙሉ በጸሎት ውስጥ ነበር። ከዚያም በኃላ እንዲ አለው “ሁሉም አንተን እየፈልጉ እኮ ናቸው?” አለው። ይህም የአዲስ ስብከተ ወንጌል ስኬት ማረጋገጫ ነው።
ኢየሱስ ግን ሌላ ቦታ መሄድ እንዳለበት ለራሱ ሰዎች ይናገራል፣ እሱን መፈለግ የሚገባቸው ሰዎች ሳይሆኑ ነገር ግን አስቀድሞ ሰዎችን የሚፈልገው እርሱ ራሱ እንደ ሆነ ይናገራል። ለዚህም ነው እርሱ ቀጣይነት ባለው መልኩ በገሊላ ጎዳናዎች ላይ ሲመላለስ የነበረው በዚሁ ምክንያት ነው። በጸሎት ከአባቱ ጋር ይገናኝ ነበረ። የጸሎት መንገድ ላይ ይጓዝ ነበር። ኢየሱስ ይጸልያል።
ምሽቱንም በሙሉ በጸሎት አሳለፈ።
በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ኢየሱስ የጸሎት ሰው መሆኑን፣ ከአብ ጋር ያለውን ቁርኝት፣ በመገልጽ ሁሉንም ነገር በዚሁ መልኩ ማስተዳደር የሚችል ይመስለኛል። ከሁሉም በላይ ይህንን ተግባሩን በጌተሰማኒ በነበረበት ወቅት ገልጾታል። የኢየሱስ ጉዞ የመጨረሻ ክፍል (እስከዚያ ጊዜ ድረስ ካደረጋቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ አስቸጋሪ በሆነው ወቅት) ኢየሱስ በተከታታይ በመጸለይ የመስዋዕትነቱን ትርጉም ፍቺውን ለማግኘት ከአባቱ ጋር በተከታታይ በጸሎት ይገናኝ ነበር። በእርግጥ ይህ ጸሎት ቀላል የሆነ ነገር የነበረ ሳይሆን በእውነትም "የምያስጨንቅ"፣ አትሌቶች እንደ ሚሰማቸው ዓይነት የጭንቀት ስሜት እና የመስቀል መንገዱን ለመደገፍ የሚችል ጸሎት ነበር።
እዚህ ጋር በጣም አስፈላጊው ነጥብ “ኢየሱስ ጸለየ” የሚለው ነው።
ኢየሱስ በጣም ብዙ ሕዝቦች በተሰበሰቡበት ስፍራ በመገኘት ከሕዝቡ ጋር የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች አብሮ በመካፈል ይጸልይ ነበር፣ ነገር ግን ከዓላማው ጋር ጥብቅ የሆነ ቁርኝት እንዲኖረው፣ የነፍሱን ምስጢር በጥልቀት እንዲረዳ እንዲረዳው፣ እንዲያስችለው ራሱ ብቻውን በመሆን የሚጸልይበት ስፍራዎችን ይፈልጋል፣ እርሱ የበረሃውን ድንጋዮች የሚያውቅና ወደ በተራሮች ከፍ ከፍ ብሎ መሄድን የሚውቅ ነብይ ነው። በመስቀል ላይ ከመሰቀሉ በፊት የነበረው የኢየሱስ የመጨረሻ ቃላት የነበሩት የአይሁዳዊያን ጸሎት ሲሆን ይህም ማለት በልጅነቱ እናቱ ያስተማረችውን የአይሁዳዊያንን ጸሎት ነበር የጸለየው።
በዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች እንደ ሚጸልዩ ሁሉ ኢየሱስም ይጸልያል። ነገር ግን በሚጸልይበት ሁኔታ ውስጥ በደቀመዛሙርቱ ዓይኖች የማይታወቅ አንድ ሚስጥር በውስጡ አለ፣ በዚህ ምክንያት የተነሳ ነው በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደ ምናገኘው “ጌታ ሆይ መጸለይ አስተምረን” ብለው የጠየቁትም በዚህ የተነሳ ነው። ኢየሱስ ሲጸልይ አይተው ያንን ጸሎት ለመማር ፈልገው "ጌታ ሆይ መጸለይ አስተምረን” ብለው ይጠይቁታል። ኢየሱስም ይህንን ጥያቄያቸውን አልቃወመም፣ ከአብ ጋር ያለውን ጥብቅ ግንኙነት አላስቀናውም ነገር ግን እሱ ከአብ ጋር ያለውን ግንኙነት በትክክል ለማስተማር መጣ። በዚህም መልኩ የደቀ መዛሙርቱ እና የኛም የጸሎት አስተማሪ መምህር ሆነ። እኛም በበኩላችን “ጌታ ሆይ መጸለይ አስተምረኝ” ብለን ልንጠይቀው የገባል።
ለበርካታ ዓመታት የጸለይን ሰዎች ብንሆንም እንኳን ሁልጊዜ ጸሎት እንዴት መጸለይ እንደ ሚገባን መማር አለብን! የሰው ልጅ ጸሎት በተፈጥሮ ከሕይወቱ የመነጨ ጸሎት፣ ከአጽናፈ ሰማይ ውስጥ እጅግ በጣም ጥብቅ ሚስጥሮች አንዱ ሊሆን ይችላል። ወደ እግዚኣብሔር አባታችን የምናቀርባቸው ጸሎቶች እግዚኣብሔር የሚፈልጋችው ዓይነት ጸሎቶች ይሁኑ ወይም አይሁኑ ማረጋገጥ ግን አንችልም። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ያልተጣራ ጸሎትን አስመልክቶ ምስክርነትን ይሰጠናል፣ በመጨረሻም በእግዚአብሔር የተፀየፈውን የፈሪሳዊውን ሰው ጸሎት ምሳሌ ማስታወስ ይቻላል። “ ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ከሄዱ ሰዎች መካከል ወደ ቤቱ በሰላም የተመለሰው ቀራጭ የነበረው ሰው ነበር። ፈሪሳዊም ይጸልይ የነበረው በኩራት መንፈስ ነበር፣ እርሱ በሚጸልይበት ሰዓት ሰዎች የጸሎት ሰው እንደ ሆነ እንዲመለከቱት በማሰብ በእብሪት መንፈስ ተሞልቶ ነበር የሚጸልየው። ልቡ ቀዝቃዛ ነበር። ኢየሱስም እንዲ አላቸው ከዚያ ፈሪሳዊ ይልቅ ይህ ቀራጭ የነበረ ሰው ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል” (ሉቃስ 18፡14) በማለት መናገሩ ያታወሳል። ጸሎት ከማድረጋችን በፊት በቅድሚያ ልንወስደው የሚገባ እርምጃ ትሁት መሆን ነው፣ ወደ አባታችን በመሄድ “ተመልከተኝ እኔ አጥያተኛ የሆንኩ ሰው ነኝ፣ እኔ ደካማ የሆንኩ ሰው ነኝ፣ እኔ መጥፎ ሰው ነኝ” በማለት እያንዳንዳችን ምን ማለት እንዳለብን ማወቅ ይኖርብናል። ምንም ይሁን ምን ሁል ጊዜም ቢሆን በትህትና መጀመር ይኖርብናል፣ ከእዚያም እግዚኣብሄር የሰማናል።
ትሁት የሆነውን ጸሎት እግዚኣብሔር ይሰማል።
ስለዚህ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙርያ ላይ የምናደርገውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በምንጀምርበት ወቅት ሁላችንም ልናደርገው የሚገባን ጉዳይ ውብ እና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ደቀመዛሙርቱ "መምህራቸውን መጸለይ አስተምረን” ብለው ያቀረቡትን ጥያቄ በድጋሚ መድገም ሊሆን ይገባል። በተለይም ደግሞ በዚህ ባለንበት በስብከተ ገና ሰሞን “ጌታ ሆይ መጸለይ አስተምረኝ” በማለት በድጋሚ ልንጠይቀው ይገባል። ሁላችንም ከዚህ ባሻገር በመሄድ በጣም የተሻለ ጸሎት ማድረግ እንችል ይሆናል፣ ነገር ግን “ጌታ ሆይ መጸለይ አስተምረኝ” ብለን ልንጠይቀው የገባል። ይህንን በዚህ በያዝነው የስበከተ ገና ወቅት እንፈጽም፣ በእርግጥ እርሱ የእኛን የመማጸኛ ጸሎት እንዲሁ በከንቱ ሳይሰማ አያልፍም።