ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ሕዝብን በጸሎታቸው አስታወሱ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ታህሳስ 21 ቀን 2011 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ከተገኙት ምዕመናንና እንግዶች ጋር ሆነው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት ካቀረቡ በኋላ በአደባባዩ ለተገኙት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያንና የሃገር ጎብኝዎች እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጡት እንግዶች በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው አጭር ንግግር አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣

በዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ውስጥ በአመጽና በኢቦላ ወረርሽኝ ምክንያት ለሚሰቃዩት በሙሉ እንጸልይ። የዚህች አገር ሕዝቦች በመካከላቸው ሰላምን በመፍጠር በሃገራቸው የሚካሄደውን ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲያካሂዱ አደራ እያልኩኝ በጋራ ሆነን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎታችንን እናቅርብ።

በዚህ አደባባይ ለተሰበሰቡት በሙሉ፣ ከሮም ከተማና ከሌሎች ስፍራዎች ለመጣችሁ መንፈሳዊ ነጋዲያን፣ ከተለያዩ ቁምስናዎች ለመጣችሁ ምእመናን፣ መንፈሳዊ ማሕበራትና ወጣቶች በሙሉ ልባዊ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ዛሬ ደግሞ በዚህ ስፍራ ለተገኙት ቤተሰቦች እና በቤታቸው ሆነው ይህን ዝግጅት በተለያዩ  ማሕበራዊ መገናኛዎች በኩል ለሚከታተሉ ቤተሰቦች በሙሉ ልዩ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ቤተሰብ ውድ ሃብት በመሆኑ ልዩ ትኩረትን በመስጠት ሁል ጊዜ መጠበቅና መንከባከብ ያስፈልጋል። የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ ለጉዞአቸው ብርሃን በመሆን ይምራቸው፣ ይጠብቃቸው።

ከኢጣሊያ ውስጥ ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጡት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችና አገልጋዮቻቸው፣ ከእነዚህም መካከል ከሌኛሮና ከግራኛኖ ለመጡት ምዕመናን በሙሉ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ከቪላባቴ ለመጡት የስካውት አባላት፣ ከቢቶሪዮ ቨነቶ ለመጡት የቅዱስ ሜሮን ምስጢር ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ ልጆች፣ እንደዚሁም ከቤርጋሞ ሃገረ ስብከት የተለያዩ ቁምስናዎች ማለትም ከኩራኖ፣ ከፓላዛጎ፣ ከግሮሞሎንጎ፣ ከባርዛኖና ከአልመኖ ለመጡት ምዕመናን በሙሉ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። የስፔንና የፖላንድ ባንዲራዎችን ላነገቡት ሁለት የደናግል ማሕበር አባላትን ሰላምታዬን አቀርባለሁ።

በዚህ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተገኛችሁ በሙሉ በልካም ዕለተ ሰንበት እንዲሆንላችሁ፣ ዓመቱም በሰላም እንዲገባደድ እመኛለሁ። በጸሎታችሁ ስለረዳችሁኝ በድጋሚ እያመሰገንኩ፣ አሁንም ጸሎታችሁን ሳታቋርጡ ዘወትር እንድታግዙኝ አደራ እላለሁ። መልካም ምሳን እመኝላችኋለሁ።” ካሉ በኋላ የዕለቱን ስነ ስርዓት አጠቃልለዋል።

31 December 2018, 17:05