“ንጹዕ የመጠጥ ውሃ ለሁሉም የዓለማችን ሕዝቦች ተደራሽ ማድረግ” “ንጹዕ የመጠጥ ውሃ ለሁሉም የዓለማችን ሕዝቦች ተደራሽ ማድረግ”  

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ “በንጹዕ ውሃ እጥረት ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ማየት ባጣም ያሳዝናል!”

በአሁኑ ወቅት በዓለማቀፍ ደረጃ “ንጹዕ የመጠጥ ውሃ ለሁሉም የዓለማችን ሕዝቦች ተደራሽ ማድረግ” በሚል መሪ ቃል በሮም በሚገኘው በሁርባኒያና ጳጳሳዊ ዮኒቬርሲቲ “የጋራ መልካም አስተዳደር ለሁሉም ሰው ንጹዕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ” በሚል ጭብጥ ዙሪያ በመካሄድ ላይ ባለው ዓለምቀፍ ኮንፈረንስ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት “በአሁኑ ወቅት በ21ኛው ክፈለ ዘመን በዓለም ውስጥ በንጹዕ የመጠጥ ውሃ እጥረት ምክንያት ሕይወታቸውን እያጡ የሚገኙት ሰዎች መመልከት በራሱ በጣም አሳፋሪ የሆነ ጉዳይ ነው” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን “ንጹዕ የመጠጥ ውሃ የማገኘት መብት ከሰብአዊ ክብር የሚመነጭ በመሆኑ የተነሳ ውሃን እንደ ማነኛውም ሽቀጥ አድርጎ መቁጠር በራሱ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

“ውሃ ለሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆነ መሰረታዊ ነገር ነው። በዓለም ዙሪያ ለሚኖሩ ለብዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ንጹዕ የመጠጥ ውሃ ተደራሻ ባለመሆኑ የተነሳ ክብር ያለው ሕይወት እየኖሩ አይደለም። ውሃን በተመለከተ የተደረጉት ጥልቅ ጥናቶች ውጤት እንደ ምያሳየው በተለይም ደግሞ በዓለማችን የተለያዩ በሽታዎች መንስሄ እና ለብዙ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የንጹዕ ውሃ እጥረት መሆኑን መግለጹ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለሚኖሩ የሰው ልጆች ሁሉ ትልቅ ውርደት ነው” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

ተጠምቼ ነበር ...

“በእምነት ዓይን ስንመልከት በማቴዎስ ወንጌል ላይ እንደ ተጠቀሰው ማለት ነው፣ በእያንዳንዱ የተጠማ ሰው ላይ "ተጠምቼ ነበር እናንተ ግን አላጠጣችሁኝም" የሚለውን የእግዚአብሔርን ተመሳሳይ ምስል እናያለን” ብለዋል።

በኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ምክንያት የንጹዕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽ እንዳይሆን ተደርጉዋል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዚህ “የጋራ መልካም አስተዳደር ለሁሉም ሰው ንጹዕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደረሽ ለማድረግ” በሚል መሪ ቃል በመካሄድ ላይ ባለው ዓለማቀፍ ኮንፈረንስ ላይ ባስተለለፉት መልእክት ቅዱስነታቸው ጨምረው  እንደ ገለጹት “የጦር መሳርያን ለመታጠቅ በሚደረገው እሽቅድድም እና በሙስና ምክንያት የንጹዕ የመጠጥ ውሃ እጥረት በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨምረ መምጣቱ የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ እንደ ሆነ” አጽኖት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን “በሚያሳዝን ሁኔታ” አሉ ቅዱስነታቸው “ማኅበረሰቡ ቀጣይነት ባለው መልኩ ንጹዕ የመጠጥ ውሃ አዘውትሮ በማያገኝባቸው አብዛኞቹ ሀገሮች ውስጥ የጦር መሣሪያዎች እና ጥይቶች አቅርቦት እጥረት በፍጹም ገጥሞዋቸው አያውቅም፣ ይህም የንጹዕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሁኔታ እያሽቆለቆለ እንዲሄድ አድርጎታል” ያሉት ቅዱስነታቸው “በሙስና እና ኢኮኖሚያዊ በሆኑ ፍላጎቶች ምክንያት የንጹዕ የመጠጥ ውሃ እጥረት እየተባባሰ ይገኛል፣ ነገር ግን ማነኛውም ኢኮኖሚ በቅድሚያ ተጨባጭ በሆነ መልኩ ንጹዕ የመጠጥ ውሃን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ የገባዋል” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

 

የቤተክርስቲያን ቁርጠኝነት

“ንጽዕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረትን በተመለከተ በተከታታይ የተደረጉ ጥልቅ የሆኑ ዓለማቀፍ ጥናቶች ውጤት እንደ ሚያሳየው” ይህንን በጣም አደገኛ የሆነ ችግር ለመፍታት ዓለማቀፋዊ የሆኑ ምላሾች በአስቸኳይ እንዲደረግ የሚጠቁሙ በመሆናቸው የተነሳ ችግሩን ለመፍታት “ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት እንደ ሚያስፈልግ ያመልክታል፣ በዚህም የተነሳ ሁሉም ዓለማቀፍ ተቋማት፣ ድርጅቶች፣ የትምህርት መስጫ ተቋማት እና የቴክኖሎጂ ማዕከላት ተባብረው የሚሰሩ ከሆነ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል የገንዘብ አቅም ሊኖር ይችላል” ማለታቸው ተገልጹዋል። “ቅድስት መንበር እና በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም የሰው ልጆች ንጹህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደ ሆኑ” በመግለጽ መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህ ቁርጠኝነት ተግባራዊ ለማድረግ መሰረተ ልማቶች፣ ስልጠና፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በማካሄድ በዚህ አደጋ ላይ የሚገኙ ሕዝቦች ንጹዕ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ በማድረግ ከቅዱስ ወንጌል እና ከጤናማ ከሰነ-ስብዕ በሚመነጩ የስነ-ምግባር መርሆዎች በመታገዝ ንጹዕ የመጠጥ ውሃን ለሁሉም ተዳራሽ ለማድረግ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሙሉ አቅሟ እየሠራች መሆኗን” መግለጻቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

አስደንጋጭ የሆኑ የጥናት ውጤቶች

በቅርብ የተደረጉት ግምታዊ ጥናቶች እንደ ሚያሳዩት  ከ 2.1 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕዝቦች በቤት ውስጥ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ውሃ ሳያገኙ እንደ ሚኖሩ የሚጠቁሙ ሲሆን ንጹዕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽነትን በተመለከተ የተደርጉ ጥናቶች እንደ ሚያሳዩት በዓለማቀፍ ደረጃ 1 ቢልዮን የሚሆኑ ሕዝቦች ንጹዕ የመጠጥ ውሃ እንደ ማያገኙ መገለጹ የሚታወስ ሲሆን ይህም በጣም አስደንጋጭ የሆነ ክስተት እንደ ሆና ያሳያል። በተጨማሪም ከሦስት እስከ ዐራት ቢልየን የሚገመቱ የዓለማችን ሕዝቦች ቀጣይነት ባለው መልኩ በቂ ንጹዕ የመጠጥ ውሃ አያገኙም። ዓለማቀፉ የሕጻናት መርጃ ድርጅት በእንግሊዜኛው ምጻረ ቃል “UNICEF” ይፋ ካደረገው ወቅታዊ መረጃ ለመረዳት እንደ ተቻለው በአሁኑ ወቅት በዓለማቀፍ ደረጃ በየቀኑ ከ700 በላይ የሚሆኑ ሕጻናት ንጹዕ የመጠጥ ወሃ እጥረት፣ በውሃ እጥረት የተነሳ በሚከሰት የንጽሕና ጉድለት ጋር በተያያዘ መልኩ በሚከሰተው ውሃ ወለድ በሽታ የተነሳ በየቀኑ ለሞት እንደ ሚዳረጉ መግለጹ ይታወሳል። የተበከለው ውሃ እንደ ታይፎይድ፣ ኮሌራ፣ ተቅማጥ፣ ፖሊዮ የመሳሰሉ በሽታዎችን ያስከትላል። የሕጻናት አድን ድርጅት በእንግሊዜኛው “Save the children” በመባል የሚታወቀው ዓለማቀፍ የእርዳታ መስጫ ድረጅት ያወጣው መረጃ እንደ ሚያሳየው በእየቀኑ ከ 5 ዓመት በታች ከሆኑ 5 ሕፃናት ውስጥ አንዱ የሚሞተው በንጹዕ ውሃ እጥረት በሚከሰተው የውሃ ወለድ በሽታ አማካይነት መሆኑን መግለጹ ይታወቃል።

 

09 November 2018, 15:20