ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ “ሕይወት ለሌሎች የምንለግስበት እንጂ ሀብት የምንሰበስብበት ወቅት አይደለም!”

“ድህነት በተስፋፋበት በአሁኑ ዘመን ሀብት ማህበራዊ ገጽታ ሊኖረው ይገባል!”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ ዕለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎቢኚዎች ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መረሀ ግብር መሰረት በዛሬው ዕለት ማለትም በጥቅምት 28/2011 ዓ.ም ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከሳምንታት በፊት በዐስርቱ ትእዛዛት ዙርያ ጀምረውት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “አትስረቅ” በሚለው በሰባተኛው ትእዛዝ ላይ ያተኮረ እንደ ነበረ ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የዓለማችን ሀብት በጥቂት ሀብታም በሆኑ ሰዎች እጅ እንደ ሚገኝ፣ በተቃራኒው ደግሞ እጅግ በጣም ብዙ የዓለማችን ሕዝቦች በድህነት እና በስቃይ ውስጥ እንደ ሚገኙ ጠቅሰው “ድህነት በተስፋፋበት በአሁኑ ዘመን ሀብት ማህበራዊ ገጽታ ሊኖረው ይገባል!” ማለታቸው ተገልጹዋል።

በዕለቱ የተነበበው ምንባብ

“ወደ እዚህ ዓለም ምንም ይዘን አልመጣንም፣ ከዚህ ዓለም ይዘን የምንሄደው ምንም ነገር የለም። የምንበላውን እና የምንለብሰውን ካገኘን ይበቃናል። ሀብታሞች ለመሆን የሚፈልጉ ግን በፈተና ይወድቃሉ። ሰዎችን በሚያበላሽ እና በሚያጠፋ ከንቱ እና አደገኛ በሆነ በብዙ የምኞት ወጥመድ ይያዛሉ። ምክንያቱም የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ምንጭ ነው፣ አንዳንድ ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት በመመኘት ከእምነት ርቀዋል፣ ልባቸውንም በሐዘን ጦር ወግተዋል” (1ጢሞ. 6፡7-10)።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው ዕለት ማለትም በጥቅምት 28/2011 ዓ.ም ከዐስርቱ ትእዛዛት መካከል አንዱ በሆነው “አትስረቅ” በሚለው በሰባተኛው ትእዛዝ ላይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል፣ አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ከዚህ ቀደም በዐስርቱ ትእዛዛት ዙርያ የጀመርነውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል ዛሬ ደግሞ “አትስረቅ” የሚለውን ሰባተኛ ትእዛዝ እንመለከታለን።

ይህንን ትእዛዝ ስንሰማ ስርቆት እና የሌሎችን ንብረት መመኘት የሚሉት ጭብጦች ወደ ሐሳባችን ይመጣሉ። ስርቆትን እና ብዝበዛን የሚፈቅድ ባሕል የለም፣ እንዲያውም የሰው ልጅ ንብረቱን ለመከላከል ያለው ስሜት በጣም ከፍተኛ ነው።

ነገር ግን ይህንን ቃል ሰፋ ባለ መንገድ ለመረዳት እና ስለንብረት ያለን ግንዛቤን በክርስቲያን ጥበብ ብርሃን ለመመልከት እንችል ዘንድ ራሳችንን መክፈት ይኖርብናል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ንበረት ዓለማቀፋዊ የሆነ ግብ እንዳለው ይገልጻል። ይህ ምን ማለት ነው? ይህንን በተመለከተ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የትምሕርተ ክርስቶስ አሰተምህሮ ምን እንደ ሚል እናዳምጥ “መጀመርያ ላይ እግዚኣብሔር ምድርንና የያዘቻቸውን ሃብቶች የሰው ልጅ በጋራ እንዲጠቀምባቸው፣ በሥራ አማካይነት እንዲቆጣጠራቸው ፍሬዎቻቸውን እንዲበላ በአደራ ሰጥቶታል። የተፈጥሮ አብቶች በጠቅላላ ለሰው ሁሉ ጥቅም እንዲውሉ የታቀዱ ናቸው” (2402) ይላል። በተጨማሪም “ሠርተው ያፈሩትም ይሁን ከሌሎች በውርስና በስጦታ ያገኙት ሀብት ባለቤት የመሆን መብት፣ መሬት መጀመርያ ላይ ለሰው ልጆች ሁሉ በስጦታነት መሰጠቷን አይሽርም። ምንም እንኳን የጋራ ጥቅምን ማጎልበት የግል ሀብት የማፍራትና ባለቤት የመሆን መብት መከበር ያለበት ቢሆንም ነገር ግን ሀብት የሁሉም መሆኑ ከመጀመርያ ጊዜ ጀምሮ የነበረ ነው” (2403) ይለናል።

ይሁን እንጂ ይህ ስጦታ "በተከታታይ" ሲገለጽ አናይም፣ ልዩነቶች አሉ፣ ስለዚህ አንዱ ለሌላው በመሰጣጣት እርስ በእርስ መኖር ይችላል። ዓለማችን ለሁሉም ሰዎች የሚሆን መሰረታዊ ነገሮችን ለማቅረብ የምያስችላት የተፈጥሮ ጸጋ አላት። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ በአስከፊ ድህነት አረንቋ ሥር ይኖራሉ፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን ያለምንም መስፈርት በመጠቀማችን የተነሳ የተፍጥሮ ሀብቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመኑ ይገኛሉ። ነገር ግን ዓለማችን አንድ ብቻ ናት! ሕዝቦቹዋም አንድ ናቸው!

በምድር ላይ ርሃብ ከተከሰተ፣ ርሃቡ የተከሰተው የምግብ እጥረት ስላለ አይደለም! በእርግጥም አንዳንዴ የገበያ ፍላጎቶችን ለማነሳሳት በማሰብ እጥረት እንዲከሰት ምግብ ሲጣል እናያለን። ነገር ግን ማነቆ የሆነው ነገር በቂ የሆነ ምርት ማምረት እና ጥሩ የመተዳደሪያ ስርዓት በመዘርጋት በትብብር እና በቅንጅት ምርቶችን ለሁሉ በበቂ ሁኔታ ማዳረስ አለመቻሉ ነው። አሁንም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ እንዲህ ይለናል፡ “ሰው በነገሮች በሚገለገልበት ወቅት የግሉ የሆኑት ውጫዊ መገልገያዎች በሕጋዊ መንገድ የእርሱ ቢሆኑም እንኳን፣ እርሱ እንደ ሚጠቀምበት ሁሉ ሌሎችም እንዲጠቀሙ በማሰብ፣ የእርሱ የራሱ ብቻ ሳይሆን የጋራ እንደ ሆኑ አድርጎ ማየት አለበት” (2404) ይለናል።

በዚህ ሰፊ በሆነ ግንዛቤ ስንመለከት "አትስረቅ" የሚለው ትእዛዝ አዎንታዊና ሰፊ ትርጉም ይኖረዋል። በተጨማሪም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ “የየትኛውም ንብረት ባለቤትነት ባለ መብቱን የአምላክ አቃቤ ያደርገዋል” በማለት ይናገራል። ማንኛውም ሀብት ኃላፊነትን መውሰድ ይጠይቃል፣ እያንዳንዱ ሀብት የመነጨው ከእግዚኣብሔር ነው የሚለው ሰነ አመክኒዮ በመረሳት ላይ የገኛል። በእርግጥ ካለኝ ሀብት ሁሉ ለሌሎች ማካፈል ይኖርብኛል። በእርግጥ ካለኛ ለሌሎች የማላካፍል ከሆነ ያለኛ ሀብት እኔን ባርያ የማድረግ ስልጣን በእኔ ላይ አለው ማለት ነው። ሀብት የተሰጠን የፈጠራ ችሎታችንን በመጠቀም እንዲበዛ በማድረግ፣ በለጋስነት እንድንጠቀም ሲሆን በዚህም መንገድ በነጻነት እና በፍቅር መንፈስ እያደገ ይመጣል።

ክርስቶስ ራሱ አምላክ ሆኖ ሳለ “ራሱን እንደ አምላክ አድርጎ ስይቆጥር፣ ራሱን ባዶ በማድረግ የባርያን መልክ ለበሰ” (ፊሊ 2፡6-7) በእርሱ ድህነት እኛ ሀብታሞች እንድንሆን አድርጉዋል።

የሰው ልጅ የበለጠ ሃብት ለማግኘት ሲታገል፣ እግዚኣብሔር ራሱን ድሃ በማድረግ ይዋጀዋል፣ ያ በመስቀል ላይ የተሰቀለው “በምሕረት የተሞላው” ሰው ለሁላችንም በዋጋ የማይገመት መስዋዕት ከፍሎልናል።

የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገና የቅዱሳን መጻሕፍትን ሙሉ ትርጉም እንድንረዳ ስሜታችንን ያነሳሳል። “አትስረቅ” ማለት በሀብትህ አማካይነት ሌሎችን ውደድ፣ በተቻለ መጠን ለማፍቀር የምያስችልህን መንገድ ለማግኘት ተጠቀምበት ማለት ነው። ከዚያም ሕይወት ለአንተ መልካም ይሆናል፣ ሀብትህም የጸጋ ምንጭ ይሆናል። ምክንያቱም ሕይወት የሀብት ማከማቻ ወቅት ሳይሆን የፍቅር ወቅት ሊሆን ይገባል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በጥቅምት 28/2011
07 November 2018, 15:03