ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የአምላክ መንግሥት በሰዎች ላይ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል!”

የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንግሥት፣ የኢየሱስ ፍቅር በልባችሁ ውስጥ ሥር እንዲሰድ ብታደርጉ ሰላም ታገኛላችሁ፣ ነጻነት ይኖራችኋል እንዲሁም ደስተኛ የሆነ ሕይወት ትኖራላችሁ።

የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በትላንትናው እለት ማለትም በሕዳር 16/2011 ዓ.ም ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ መሆኑ የሚዘከርበት አመታዊ በዓል በታላቅ መንፈሳዊነት ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መሪነት በተደረገ መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉን ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ከመስዋዕተ ቅዳሴው በመቀጠል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኝዎች በተገኙበት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መሪነት “የእግዚኣብሔር መልኣክ ማሪያምን አበሰራት” የሚለው ጸሎት ከተደገመ በኋላ ቅድስነታቸው በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ መሰረቱን ባደረገ ሳምንታዊ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ገለጹት “የእግዚኣብሔር መንግሥት ለሰው ልጆች ሰላምን ይሰጣል፣ በጦር መሣሪያ አማካይነት ሰላም ለማስፈን የሚሞክሩ ሁሉ ይወድቃሉ” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

መንግሥታት በእውቀትና በስልጣን ላይ ተመስርተው በጦር መሣርያ ተደግፈው ሰላም ለማስፈን ይሞክራሉ በዚህም የተነሳ በአብዛኛው ሰላምን ከማስፈን ይልቅ ውድቀታቸውን ያፋጥኑ እንደ ነበረ ከታሪካችን እንረዳለን ብለዋል። በተቃራኒው ደግሞ በፍቅር አማካይነት እና በልባችን ውስጥ ሥር መሰረት ባለው የእግዚአብሔር መንግሥት አማካይነት ዘላቂ የሆነ ሰላም ማረጋገጥ ይቻላል፣ ለሕይወታችን አዲስ የሆነ ጣዕም የሚሰጠው ኢየሱስ ብቻ ነው” በማለት አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው አንዳንዴም በስህተትና በኃጢያቶቻችን ምክንያት የተነሳ የዓለም ንጉሥ የሆነውን ኢየሱስን መከተል ትተን የዓለምን እና በዓለም ውስጥ የሚገኙ ነገሮች አመክንዮዎችን በመከተል እምቢተኛ የሆነ መንፈስ እናጸባርቃለን ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት አድማጮቻችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሕዳር 16/2011 ዓ.ም የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ምዕመናን ዘንድ በላቲን የስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት 34ኛ ሳምንት እለተ ሰንበት ላይ የተከበረውን ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ አመታዊ ክብረ በዓለ አስመልክተው በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ

ዛሬ (ሕዳር 16/2011 ዓ.ም) በዓመቱ የስርዓተ አምልኮ ማብቂያ ላይ የምናከብረው ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ ዓመታዊ በዓል የፍጥረታት ሕይወት እንዲሁ በጋጣሚ የተገኘ ነገር እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ወደ አንድ መጨረሻ ግብ የሚያመራ፡ የታሪኮች እና የፍጥረታት ሁሉ ጌታ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ የመጨረሻ ግልጸት እንደ ሚያመራ የሚያሳይ ነው። የታሪኩ መደምደሚያ ዘለዓለማዊ መንግሥቱ ይሆናል ማለት ነው። የዛሬው የወንጌል ምንባብ (ዮሐ. 18፡33-37) ስለ ክርስቶስ መንግሥት፣ ስለ ኢየሱስ መንግሥት፣ ኢየሱስ በጌተሰማኒ ከታሰረ በኋላ ስለደረሰበት ውርደት ሁኔታ በመጥቀስ ያሳለፈውን ታሪክ ያመለክታል፡ "ታስሯል፣ ተሰድቡዋል፣ ተከሱዋል በኢየሩሳሌም ባለሥልጣናት ፊት ቀርቦአል"። ከዚያም በኋላ ፖለቲካዊ ለሆነ ሥልጣን እና የአይሁድ ንጉሥ ለመሆን እንደ ሚፈልግ ተደርጎ በሮም አቃቤ ሕግ ፊት እንዲቆም ይደረጋል። ጲላጦስ ጥያቄውን በማቅረብ አስገራሚ የሆነ ምርመራ ማድረግ በጀመረበት ወቅት እርሱ ንጉሥ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ሁለት ጊዜ ይጠይቀዋል (ዮሐ 18፡33,37)።

ኢየሱስም በቅድሚያ “የእኔ ምንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም” በማለት ይመልሳል። ከዚያን በኋላ ደግሞ “አንተ እንዳልከው ነኝ” በማለት ያረጋግጣል። ይህም ኢየሱስ በመላው ሕይወቱ ፖለቲካዊ ለሆነ ስልጣን ምንም ዓይነት ፍላጎት እንዳልነበረው ያሳያል።

ኢየሱስ በአምስት እንጀራ እና በሁለት ዓሳ ብቻ 5ሺ የሚሆኑ ሰዎችን ከመገበ በኃላ በዚህ ተዓምር እጅግ በጣም ተደንቀው የነበሩ ሰዎች የሮማን መንግሥት ገርስሶ የእስራኤል መንግሥት እንዲገነባ ፈልገው እርሱን ልያነግሱት ፈልገው እንደ ነበረ እናስታውሳለን። ነገር ግን ለኢየሱስ መንግሥት ማለት ርዕዮት፣ ብጥብጥ እና መሳሪያ የታጠቀ ኃይል ማለት አይደለም። 5ሺ ሰዎችን በአምስት እንጀራ እና በሁለት ዓሳ ከመገበ በኋላ ሕዝቡ ልያነግሡት በፈለጉ ወቅት እነርሱን ትቶ ወደ ተራራ የወጣው በዚሁ ምክንያት ነው (ዮሐ 6፡5-15)። አሁን ለጲላጦስ መልስ ሲሰጥ ደቀ መዛሙርቱ እሱን ለመከላከል አልተዋጉም ነበር። “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” (ዮሐ. 18፡36) በማለት የመለሰውም በዚሁ ምክንያት ነው። ኢየሱስ ከፖለቲካው ኃይል በላይ እጅግ የላቀ የሆነ፣ በሰው ልጆች አማካይነት ሥልጣን ላይ ያልተቀመጠ መሆኑን ግልፅ ማድረግ ይፈልጋል። እርሱ ወደ ምድር የመጣው ኃይል ተጠቅሞ ዓለምን ለመግዛት ሳይሆን በፍቅር ስለእውነት ለመመስከር ነው። ይህም የቅዱስ ወንጌል ዋና መልእክት የሆነው “እግዚኣብሔር ፍቅር ነው” የሚለው መለኮታዊ እውነት ሲሆን እርሱ በዓለም ውስጥ የእርሱን የፍቅር፣ የፍትህ እና የሰለም መንግሥት ለመመስረት ነው የመጣው። እናም ይህ ኢየሱስ የነገሠበት እና እስከ መጨረሻው ዘመን የሚዘልቅ ነው። ከታሪክ እንደ ምንማረው በጦር መሳሪያ እና በምድራዊ ስልጣን ላይ  መሰርቱን በማድረግ የተገነባ መንግሥት በመጀመሪያ በቀላሉ ይበታተናሉ ቀጥሎም ብዙ ሳይቆይ ተዳክመው የፈራርሳሉ። ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት በፍቅር ላይ የተመሰረተ እና በልባችን ውስጥ ሥር መሰረት ያለው ነው፡ የእግዚኣብሔር መንግሥት በልባችን ውስጥ ሥሩን ይዘረጋል-ይህንን የሚቀበል ሰው ደግሞ ሰላምን ያገኛል፣ ነጻነትን ይጎናጸፋል ምልኣት ያለው ሕይወት ይኖራል። ሁላችንም ሰላምን እንፈልጋለን፣ ሁላችንም ነጻነት እንፈልጋለን፣ ሁላችንም ምልኣት ያለው ሕይወት እንፈልጋለን። ታዲያ ይህንን እንዴት ማግኘት እንችላለን? የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንግሥት፣ የኢየሱስ ፍቅር በልባችሁ ውስጥ ሥር እንዲሰድ ብታደርጉ ሰላም ታገኛላችሁ፣ ነጻነት ይኖራችኋል እንዲሁም ደስተኛ የሆነ ሕይወት ትኖራላችሁ።

ኢየሱስ ዛሬ እርሱ የሕይወታችን ንጉሥ ይሆን ዘንድ እንድንፈቅድለት ይጠይቀናል። በቃሉ፣ በመላካም አብነቱ፣ በመስቀል ላይ ተሰውቶ እኛን ከሞት ያዳነን ይህ ንጉሳችን የደጉን ሳምራዊ መንገድ እንድንከተል በማመልከት በጥርጣሬ ለተሞላው ሕይወታችን አዲስ የሕይወት ሕልውና ብርሃን በመስጠት ከፍርሃት ነጻ ሆንን እና በእየእለቱ ከሚገጥሙን ፈተናዎች ተላቀን እንድንኖር ይረዳናል። ነገር ግን እኛ የኢየሱስ መንግሥት ከዚህ ዓለም እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ በስህተቶቻችንን እና በኃጢአቶቻችንን እንድንፈትሽ ጊዜ በመስጠት፣ የዓለምን እና የዓለም ምንግሥታት አምክንዮ  እንዳንከተል በማድረግ ህይወታችን አዲስ ትርጉም እንዲኖራት ያደርጋል።

ኢየሱስን የሕይወታችን ንጉሥ አድርገን እድንቀበል እና የእርሱ መንግሥት እንዲሰፋ ለማድረግ እውነት ለሆነው ለእርሱ ፍቅር ምስክርነት በመስጠት መኖር እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።

 

25 November 2018, 16:06