ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ሁለንተናዊ እና ዘላቂ የሆነ ልማት ለማምጣት ገና ብዙ መንገድ መጓዝ ይኖርብናል

ከትላንት ከሕዳር 05/2011 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተውጣጡ 80 የጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ አባላት በቫቲካን አመታዊ ስብሰባቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዚህ ስብሰባ ላይ በሕዳር 05/2011 ዓ.ም ተገኝተው ለጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ አባላት ንግግር ማድረጋቸውን ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “እናንተ አሁን በተለያዩ ዘርፎች እያደረጋችሁ የምትገኙት ምርምሮች የዓለም ሕዝብን መመገብ እና ከጥማታቸው ማላቀቅ የሚችል፣ እንዲሁም የዓለማችን ሕዝቦች ሁሉ ለስልጣኔ ማብቃት የምያስችል ምርምር ሊሆን የገባል”  ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን በተለይም ደግሞ የዓለም መንግሥታት አውዳሚ የሆነውን የኒውክለር የጦር መሣሪያ ትጥቅ ይፈቱ ዘንድ ማግባባት ይኖርባችኋል ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

“ውድ የሳይንስ ሊቃውንት እና የሳይንስ ወዳጆች፣ ለእናንተ የእውቀት ቁልፎች በአደራ ተሰጥቷችኋል" በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ የእናንተን ሳይንሳዊ ጥበብ መቋደስ ላልቻሉ የዓለማችን ሕዝቦች፣ በተለይም ደግሞ በቂ የሆነ ምግብ፣ የጤና መስጫ ተቋም፣ ትምህርት፣ የመገናኛ አውታሮች፣ ማኅበራዊ ዋስትና እና ሰላም ለሌላቸው የማኅበርሰብ ክፍሎች ሁሉ ጠበቃ ልትሆኑ ይገባል” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የጦር መሣርያ ስርጭትን ለማስቆም የሚችል ፖሌቲካዊ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል

“ሁለንተናዊ እና ዘላቂ የሆነ ልማት ለማምጣት ገና ብዙ መንገድ መጓዝ ይኖርብናል” በማለት መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህንን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ አሁን እየኖርንበት ያለውን የአኗኗር ዘይቤ መቀየር እንደ ምያስፈልግ ገልጸው በተለይም ደግሞ በላቲን ቋንቋ “Laudato si’ በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም “ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በተሰኘው ሐዋርያዊ መልእክታቸው ውስጥ ይህንን ጉዳይ የተመለከቱ ቁልፍ የሆኑ ሐሳቦች እንደ ተካተቱበት ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው አስታውሰዋል።

“በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ውስጥ ጦርነት እንዲቀጣጠል ባማድረግ ላይ የሚገኘውን የጦር መሣርያ ዝውውርን ለማስቆም የሚችል፣ ታጋሽ የኃይል ምንጮችን ለመጠቀም የምያስችል፣ ንጹዕ የመጠጥ ውሃን ለሁሉም ለማሰራጨት የተያዘውን እቅድ ለማስፈጸም፣ ምግብ እና የጤና ተቋማትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ፣ አላግባብ የሚባክነውን ገንዘብ ማኅበራዊ ዋስትናን ለማረጋገጥ መጠቀም ይቻል ዘንድ እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ በጎ ተግባራትን ገቢራዊ ለማድረግ የምያስችል ፖሌቲካዊ ቁርጠኝነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደ ሚጎድል” ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ጨምረው ገለጸዋል።

የሳይንስ ማህበረሰብ ሰብአዊው ቤተሰብን ማገልገል አለበት

የሳይንስ  ማኅበርሰብ ከማኅበርሰቡ ውስጥ የፈለቁ መሆናቸውን ማሰብ እንጂ ከማኅበርሰቡ የተለዩ አድርገው ራሳቸውን መቁጠር እንደ ሌለባቸው” የገለጹት ቅዱስነታቸው “የሳይንስ ማኅበርሰብ ይህንን በመረዳት ሰብዓዊ የሆኑ የማኅበርሰብ ክፍሎችን ለማገልገል መነሳት እንደ ሚኖርባቸው በመልእክታቸው ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት በምድራችን ላይ እየተክሰተ ያለው ከፍተኛ ስነ-ምዕዳራዊ ለውጥ በሰው ልጆች ተግባር ምክንያት የተከሰተ መሆኑን ለሁሉም ግልጽ አድርገው ማሳወቅ እንደ ሚጠበቅባቸው ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

“ስለዚህ በምድራችን ላይ የሚኖሩ ሕዝቦችን ጤንነት ለመጠበቅ የሚያስችል በቂ የሆነ ምላሾች እንደ ምያስፈልጉ” የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህም ሊተገበር የሚገባው በነዳጅ ዘይቶች እና በደን ጭፍጨፋ ምክንያት፣ እንዲሁም በሰው ልጆች አማካይነት በምድራችን ላይ እየተቃጡ በሚገኙ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሐብት ብዝበዛ የተነሳ ለአደጋ የተዳረገችሁን ምድራችንን መተደግ የሚያስችል እቅዶችን መቅረጽ እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ የሆነ ችግር በማስከተል ላይ የገኛል

"በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየተከሰተ ያለው ከፍተኛ ችግር ባሻገር ዓለማችን ለከፍተኛ ስጋት እየዳረጋት የሚገኘው የኒውክለር የጦር መሳርያ ለመታጠቅ የሚደርገው ጥረት እንደ ሆነ” በመልእክታቸው አጽኖት ሰጥተው የተናገሩት ቅዱስነታቸው ይህንን ጅምላ ጨራሽ እና አውዳሚ የሆነውን የኒውክለር የጦር መሣሪ ለመታጠቅ በአሁኑ ጊዜ እየተደረገ የሚገኘው ሩጫ ለመግታት የሚያስችል እቅዶችን በማውጣት የዓለማችንን ገዦዎች በማሳመን ይህንን አውዳሚ እና ጅማላ ጨራሽ የሆነውን የኒውክለ ጦር መሳርያ ስርጭት ለመግታት የዓለማችንን መሪዎች ለማሳመን የራሳችሁን ድርሻ መወጣት ይኖርባችኋል” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

14 November 2018, 16:01