10-09-2013 Visita Papa Francesco ai rifugiati nel Centro Astalli 10-09-2013 Visita Papa Francesco ai rifugiati nel Centro Astalli 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰዎችን ማግለል የዘመናችን በሽታ መሆኑን ገለጹ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው በሕዝቦቻችን መካከል መሠረታዊ ለውጥን ለማምጣት ማንኛውንም ዓይነት ኢፍትሃዊ ሥርዓትን፣ በሰዎች መካከል ልዩነቶችንና የማግለል ባሕልን ማስወገድ ያስፈልጋል ብለው እነዚህም የዘመናችን ተዛማች በሽታዎች ናቸው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስደተኞችን አስመልክቶ እየተደረገ ባለው ስምንተኛው ዓለም አቀፍ ማሕበራዊ መድረክ በላኩት መልዕክታቸው፣ ሰዎችን ማግለል የዘመናችን በሽታ መሆኑን ገልጸዋል። መሰደድ፣ ስደተኞች ራሳቸውን እንዲያቋቋሙ መርዳት ወይም ጥረት ማድረግ፣ ስደት ከሚያስከትለው ችግር ነጻ መሆንና ስደተኛ ሕብረተሰብንም መለወጥ በሚለው ርዕስ ዙሪያ ወይይት እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው በሕዝቦቻችን መካከል መሠረታዊ ለውጥን ለማምጣት ማንኛውንም ዓይነት ኢፍትሃዊ ሥርዓትን፣ በሰዎች መካከል ልዩነቶችንና የማግለል ባሕልን ማስወገድ ያስፈልጋል ብለው እነዚህም የዘመናችን ተዛማች በሽታዎች ናቸው ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን መልዕክታቸውን የላኩት በሜሲኮ ሲቲ እስከ ነገ እሑድ ጥቅምት 25 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ፣ ስደተኞችን አስመልክቶ በሚደረገው ስምነተኛው ዓለም አቀፍ ማሕበራዊ መድረክ ላይ እንደሆነ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት መልዕክት ድምጻቸው እንዲዘጋ ለተደረጉት፣ ድምጽ እንዲሆንና ፍትህን እንዲያገኙ፣ ከእነዚህም መካከል ስደተኞች፣ ተፈናቃዮች፣ የተገለሉ፣ የተጨቆኑ፣ የተሰቃዩት፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን የተገፈፉት  በማለት እንደሆነ ገልጸዋል። በሰዎች ላይ ጉዳት የሚያስከትሉትን ማጋለጥ ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት ቅዱስነታቸው ለችግሩ መፍትሄ የሚገኝበትን አቅጣጫ ማግኘት ያስፈልጋል ብለው ይህንን ለማድረግ ሰዎች የሥራ ድርሻቸውንና ሃላፊነታቸውን ለይተው ማወቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ስደትን የተመለከትን እንደሆነ ስደተኞችና ተፈናቃዮች ራሳቸውን እንዲችሉ መርዳት፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን የሚያስከብሩበትን መንገድ መፍጠር፣ ተስፋቸው ለጨለመባቸው ተስፋ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በሜክስኮ ሲቲ የተዘጋጀው ስምንተኛው ዓለም አቀፍ ማሕበራዊ መድረክ፣ የዘመናችንን የስደት ችግሮችን፣ ከእነዚህም መካከል፣ ሰብዓዊ መብት፣ የየአገሮችን ድንበር፣ ፖለቲካዊ ዋስትና፣ የካፒታሊስት ስርዓት፣ የአየር ለውጥና በመንግሥታት መካከል ያለውን ግንኙነቶች በሚሉ ርዕሠ ጉዳዮች በስፋት እንደሚወያይ ታውቋል። ባሁኑ ወቅት ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በሁለት ዋና ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን እነርሱም ለስደተኞ ሕይወት ሕጋዊ ደህንነት ዋስትና መስጠት ሲሆን ሌላው ለጥገኝነት ጠያቂዎችም ተመሳሳይ ትኩረት እንዲሰጥ የሚጠይቁ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑማድረግ እንደሆነ ታውቋል።

ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያደርጉ 20 አስተያየቶች፣

ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፣ ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በተመለከተ የወሰዳቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያግዙ ገንቢ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትዕዛዝ መሠረት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ ነሐሴ 11 ቀን 2008 ዓ. ም. መዋቀሩ የሚታወስ ነው።  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደገለጹት ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያደርጉ አራት ርዕሶችና ማጠናከሪያ የሚሆኑ ተጨማሪ 20 ነጥቦችን የያዙ ሃሳቦች መቅረባቸውን ገልጸዋል። አራቱ ርዕሶችም ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ፣ መንከባከብ፣ በሕብረተሰቡ መካከል ትክክለኛ ግንዛቤን እንዲኖር ማድረግና ስደተኞች ከሕብረተሰቡ ጋር አብረው መኖር እንዲችሉ ማድረግ የሚሉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንደሆኑ ታውቋል።

ውይይትና መተጋገዝ እንዲኖር ያስፈልጋል፣

የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ በአገራት ወይም በመንግሥታት መካከል በውይይት መስማማትና መተጋገዝ እንዲኖር ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እነዚህ ውይይቶች ባሉበት አካባቢ በሙሉ ቤተክርስቲያን የራሷን ድርሻ ለማበርከት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በስምንተኛው ዓለም አቀፍ ማሕበራዊ መድረክ ላይ የተሳተፉት ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሙሉ በመካከላቸው ገንቢ ውይይቶችን በማካሄድ እርስ በርስ በመተጋገዝ ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነቶች ላይ እንደሚደርሱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ
03 November 2018, 16:19