ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንስችስኮስ ለደሆች በተዘጋጀ የምሳ ግብዣ ላይ መገኘታቸው ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ትናንት እሑድ ህዳር 9 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ በተዘጋጀ የምሳ ግብዣ ላይ መገኘታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው 1500 ከሚጠጉ ችግረኛ ቤተሰብ ጋር ሆነው ለምሳ የተዘጋጀውን ማዕድ መካፈላቸው ታውቋል።

ቅዱስነታቸው በአዳራሹ የተገኙትን በሙሉ ለምሳ ወደ ተዘጋጀው ገበታ ዙሪያ እንዲቀርቡ ጠርተው፣ የእለቱን ማዕድ ላቀረቡት፣ በምዕዱ ዙሪያ ያገለገሉትንም በሙሉ አመስግነው የቀረበውን ማዕድ እግዚአብሔር ባርኮ እንዲሰጣቸው ጸሎት አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በጸሎታቸው በአዳራሹ የተገኙትን በሙሉ፣ የልባቸውንም መሻት እግዚአብሔር እንዲባርክ በጸሎታቸው አስታውሰው በሕይወት ጉዞአቸውም እግዚአብሔር አብሮአቸው እንዲሆን በማለት ጸሎታቸውን አቅርበው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ምክንያት በማድረግ በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተዘጋጀውን ምሳ አብሮአቸው ለመካፈል ለመጡት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው መልካም ምሳ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

ማዕድን አብሮ መቋደስ የሚሰጠው እርካታ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ከተገኙት ምዕመናን፣ ነጋዲያንና የሃገር ጎብኝዎች ጋር ሆነው የዕኩለ ቀን የብስራተ ገብርኤል ጸሎታቸውን ካቀረቡት በኋላ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ሄደው፣ በተለያዩ ማሕበራት የሚታገዙ ወደ 1500 ከሚጠጉ ድሆች ጋር ማዕድ መካፈላቸው ታውቋል። ለምሳ የቀረበውን መብል ያሰናዱትም በሮም የሂልተን ኢጣሊያ ማሕበር ከታቦር የሥነ ምግባር ማህበርተኞች ጋር በመተባበር እንደሆነ የታወቀ ሲሆን ስነ ስርዓቱን ያዘጋጁት በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል ስርጭት አገልግሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት፣ ከካሪታስ ካቶሊካዊ እርዳታ ሰጭ ድርጅት፣ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር፣ ኦርዲነ ዲ ማልታ የተሰኘ በጎ አድራጊ ድርጅት፣ ኑዎቪ ኦሪዞንቲ እርዳታ አቅራቢ ማሕበረሰብ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ማሕበር፣ 2016 ወንድም የተሰኘ ማሕበር፣ በሮም የአንቶኒያ በጎ አድራጊ ድርጅት፣ በኢጣሊያ የክርስቲያን ሠራተኞች ማሕበር፣ የቅዱስ ቪንሰንት የበጎ አድራጎት አገልግሎት አቅራቢ ቡድኖችና በየቁምስናዎች የተዋቀሩ የበጎ አድራጊ ማሕበራት በጋራ ሆነው እንደሆነ ታውቋል። በገበታው ላይ የቀረቡት የምግብ ዓይነቶችም በኢጣሊያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚዘጋጁ ባሕላዊ ምግቦች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ በቀረበው የምሳ ግብዣ ስነ ስርዓት ላይ ለተገኙት፣ ወደ 1500 ለሚጠጉት ተጋባዦችና ከተለያዩ ማሕበራት መጥተው የመስተንግዶ አገልግሎትን ላቀረቡት፣ ምግብን አዘጋጅተው ላመጡት በሙሉ፣ የሙዚቃ ዝግጅቶችን በማቅረብ ለምሳ ግብዣው ድምቀትን ለሰጡት አርቲስቶችም በሙሉ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በመጨረሻም በግብዣው ላይ የተገኙት በሙሉ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለው የግብዣ አዳራሹን ለቀው ከመሄዳቸው በፊት ከሕጻናት፣ ከደሃ ቤተሰቦች ጋር ሰላምታ ተለዋውጠው የማስታወሻ ፎቶግራፎችንም ተነስተዋል።

በተመሳሳይ ዕለት ማለትም ትናንት እሑድ ህዳር 9 ቀን 2011 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የድሆችን ቀን በማስታወስ በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኙት የተለያዩ ቁምስናዎችም እንደዚሁም በኢጣሊያ ውስጥ የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችም በሮቻቸውን በመክፈት በአካባቢው ለሚገኙ ደሃ ቤተሰቦች የምሳ ግብዣ ስነ ስርዓት ማዘጋጀታቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

 

19 November 2018, 15:47