ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “በሰዎች መካከል ልዩነት እየፈጠሩ መፍረድ ትክክል አይደለም”።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት ምዕመናንና የሃገር ጎብኝዎች በዕለቱ ከማርቆስ ወንጌል ምዕ. 9፤ 38-43. 45. 47-48 ተውስዶ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው ባደረጉት አስተንትኖ “በሰዎች መካከል ልዩነት እየፈጠሩ መፍረድ ትክክል አይደለም” ማለታቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያደረጉት አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ፣
ከማር. ወንጌል ተውስዶ የተነበበው የዚህ እሑድ ንባብ የኢየሱስ ክርስስቶስና የደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር በሚያከናውኗቸው ሥራዎች ግልጽ ያደርግልናል። ደቀ መዛሙርቱ ከዕለታት አንድ ቀን ከመካከላቸው አንዱ ራሱን ወጣ በማድረግ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በሽተኞችን ሲፈውስ ይመለከቱትና፣ ዮሐንስም በወጣትነት ስሜት እንዲሁም ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ታማኝነት ለመግለጽ ፈልጎ የዚያን ሰው የፈውስ ሥራ ሊያስቆመው ፈለገ። ነገር ግን ኢየሱስ ዮሐንስንም ሆነ ሌሎች ደቀ መዛሙርት እንዲህ አላቸው፣ “በስሜ ተዓምር እያደረገ ወዲያውኑ በእኔ ላይ ክፉ የሚናገር ስለሌለ ተውት አትከልክሉት፣ ምክንያቱም እኛን የማይቃወም ሁሉ ከእኛ ጋር ነው” አላቸው። (የማር. 9. 39-40)
ዮሐንስና ሌሎች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እነርሱን በማይመልከታቸው የአገልግሎት ዘርፍ ወይም ተግባር ላይ ለመሰማራት አልፈለጉም ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንፈስ በሕዝቡ መካከል ያለ ገደብ እንዲገለጥ፣ እርሱን በማይቃወም በማንም በኩል እንዲሰራ እድል በመስጠት፣ ለደቀ መዛሙርቱም ነጻነትን ሰጣቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ነጻነትን በመስጠት እንዳስተማራቸው ሁሉ ለእኛም ውስጣዊ ነጻነትን በመስጠት ሊያስተምረን ይፈልጋል።
ታዲያ እኛም ወደ ሕሊናችን መለስ ብለን በዚህ የወንጌል ክፍል ላይ ማስተንተኑ መልካም ይሆናል። ደቀ መዛሙርቱ የያዙት አቋም እጅግ ሰብዓዊ፣ በሁሉም ዘንድ የተለመደና በሁሉም ክርስቲያናዊ ሕብረተሰብ መካከል እንዲሁም በእኛ ማሕበረሰብ መካከል ሊከሰት ይችላል። በጥሩ እምነት እና ቅንዓት ተነሳስተን መልካም ልማዶቻችን በአንዳንድ ሐሰተኛ እና አስመሳይ አገልጋዮች በኩል ጉዳት እንዳይደርስባቸው መጠበቅ ይቻላል። በሌላ በኩል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገውና እስካልተቃወመን ድረስ አገልግሎትን ለሁሉም ነጻ ማድረግ ይቻላል። ይህን ያደረግን እንደሆነ አንዱ ከሌላው በልጦ ለመታየት በሚያድደርገው እሽቅድድም ምክንያት አንዱ የሌላውን መልካም ሥራ ወይም ተግባር አያደንቅም ወይም አያመሰግንም። የእኛን መልካም ሥራ የማያደንቅ ሁሉ ከእኛ ወገን አይደለም። ከሆነ ይህን የመሰለ የፉክክር መንፈስ በሐይማኖቶች መካከል ልዩነትን በመፍጠር፣ ሰዎች እምነታቸውን ትተው ወደ ሌላ እምነት እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እንዳሉት ቤተክርስቲያን የምታድገው በፉክክር ወይም የሰዎችን እምነት በማናጋት ሳይሆን ከመንፈስ ቅዱስ በምታገኘው ሃይል በመታገዝ በምታሳየው ምስክርነት ሌሎችን በመሳብ ነው።
እግዚአብሔር የሚሰጠን ይህ ታላቅ ነጻነት፣ ወደ ራሳችን ልቦና ተመልሰን፣ የምንከተለውን የእምነት አቅጣጫ እንድንመረምረው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ የሚጋብዘን ይህን እንድናደርግ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጠራን በሰዎች መካከል ልዩነትን ፈጠረን፣ ወዳጅ ወይም ጠላት፣ እኛ ወይም እነርሱ፣ የእኔ ወገን ወይም የሌላ ወገን፣ የእኔ ወይም የእርሱ እንድንል ሳይሆን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት፣ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ በማንጠብቃቸው ቦታዎች፣ ከእኛ ወገን ካልሆኑ ሰዎች መካከልም እንደሚገለጥ ለማወቅ እንድንችል ልባችንን መክፈት ያስፈልጋል። ይልቅስ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን በማንም እጅ የሚከናወኑና መልካምና እውነት መስለው የሚታዩ ሥራዎች በማን ስም፣ በማን ሃይል እንደሚከናወኑ ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ፣ የዛሬው ወንጌልም እንደሚለን በማንም ላይ ከመፍረዳችን አስቀድመን ራሳችንን መመልከት ያስፈልጋል። በእምነታቸው ደካማ የሆኑትን ሰዎች ሊያሰናክላቸው የሚችሉትን ነገሮች በሙሉ ማስወገድ ያስፈልጋል።
የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በእምነት የተቀበልች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እኛም እንደ እርሷ፣ እግዚአብሔር እኛ በማንገምተው ጊዜና በማንጠብቀው ቦታ በመካከላችን በመገኘት የሚያከናውነውን ድንቅ ሥራ እንድናውቅ ትርዳን። ማሕበረ ሰባችንን ከልብ እንድንወድ፣ መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን በመገኘት ድንቅ ሥራውን እንዲያከናውን ፈቃደኞች እንድንሆን ታስተምረን”።