2018.10.29 Capitolo Generale Congregazione Missionari di San Carlo - Scalabrini 2018.10.29 Capitolo Generale Congregazione Missionari di San Carlo - Scalabrini 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የሰይጣንን ጥቃት በሕብረት እንከላከል”።

በ15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ሲኖዶስ መዝጊያ ላይም፣ ለሲኖዶሱ ብጹዓን አባቶች ባቀረቡት ተማጽኖአቸው ቤተክርስቲያን አሁን ያለችበትን አስቸጋሪ ጊዜን አስታውሰው፣ ከዚህ ችግር መውጣት የሚቻለው በሕብረት በመጓዝ፣ በጸሎት በመተባበር ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቤተክርስቲያን ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት መከላከል የሚቻለው ዘወትር በመጸለይ፣ ሕብረትን አጠንክሮ በጋራ ሆነን የወንጌልን መልካም ዜና ለዓለም በማዳረስ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳሰቡ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የከዚህ በፊት ማሳሰቢያቸው በያዝነው የጥቅምት ወር በያለንበት ሆነን የመቁጠሪያን ጸሎት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድናቀርብ ማሳሰባቸው ይታወቃል። በተጨማሪም ቤተክርስቲያንን ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት እንዲሁም መከፋፈል እንዲከላከላት ወደ ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል ዘንድ ጸሎት እንድናቀርብ ማሳሰባቸው ይታወቃል። በ15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ሲኖዶስ መዝጊያ ላይም፣ ለሲኖዶሱ ብጹዓን አባቶች ባቀረቡት ተማጽኖአቸው ቤተክርስቲያን አሁን ያለችበትን አስቸጋሪ ጊዜን አስታውሰው፣ ከዚህ ችግር መውጣት የሚቻለው በሕብረት በመጓዝ፣ በጸሎት በመተባበር ነው ብለዋል። ክፉ መንፈስም የቤተክርስቲያንን ደካማ ጎን እየፈለገ በማጥቃት ላይ መሆኑን አስረድተው፣ እናት ቤተክርስቲያን ቅድስት ብትሆንም ልጆችዋ ግን እጆቻቸው ያደፉ ናቸው ብለዋል። እናት ቤተክርስቲያን ምን ጊዜም ቢሆን ቅድስናዋን ጠብቃ ትኖራለች ብለዋል። ጥቃት እንዳይደርስባት ግን ልጆችዋ በሙሉ በያሉበት ሆነው በጸሎትና በሱባኤ መተባበር ያስፈልጋል ብለዋል።

15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ይገባደድ እንጂ ፍሬውን በተግባር ለመተርጎም ገና ከጅምሩ ላይ ነን ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አብሮ መጓዝ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተው ይህ ማለት ደግሞ፣ ሲኖዶስ የሚለው ቃል ትርጉሙ ከኢየሱስ ክርስቶስና እርሱ ለመሠረታት ቤተክርስቲያን የበላይ አገልጋይ ከሆነው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር መተባበር እንደሆነ አስረድተው በደስታ፣ በመከራ፣ ተስፋን በማድረግና በወንጌል ምስክርነት መተባበር ያስፈልጋል ብለዋል። ክፉ መንፈስ በመካከላችን ክፍፍልን በመፍጠር ከእግዚአብሔርም ሊለየን ዘወትር ጥረት እንደሚያደርግ አስታውሰው ቤተክርስቲያንን ማዳን የሚቻለው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን በማጥቃት ነው በማለት ለሚያስቡት ትልቅ የፈተና ጊዜ እንደሆነ ገልጸዋል።  በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ከአደጋ ለማምለጥ እርስ በርስ መደማመጥና በጋራ መጸልይ እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሞኞች ያሏቸው የገላቲያ ሰዎችን የክርስትናን እምነት ከመቀበላቸው በፊት፣ ድነት የሚገኘው ሕግን በማከበር ነው ብለው ያምኑ እንደነበር ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ለሕግ ብቻ ታዛዥ ልሁን ብሎ የሚያስብ በእውነት ለሕግ ታዛዥ እንደማይሆን፣ ምክንያቱም ሕጉን ከሰጠው ጋር ግንኙነት ስለማይኖረውና ሕግም ስብዕናውን፣ የሕጉ ባለቤት የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር መገንዘብ ስለማይችሉ፣ ሕግም ትርጉሙን በማጣት ዋስትናን ሊሰጥ አይችልም ብለዋል።

በእግዚአብሔር መታመን፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ሊቃወም የሚነሳ ማንም ሰው ካለማወቅ የተነሳ ኢየሱስን እየተቃወመ ይገኛል ያሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ በጸጋው አብሮን ይጓዛል፣ ይህን ጸጋ ለመቀበል እምነትን በተግባር በመግለጽ፣ ለሌሎች ፍቅርን በመግለጽ ወደ ፊት መጓዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ አብርሃም በእምነቱ ምክንያት ከሚኖርበት አገር ምንም ወደ ማያውቀው ባዕድ አገር መጓዙን ጠቅሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስን በመጥቀስ እንዳስረዱት፣ የክርስቲያን እምነት የመጽሐፍ ሐይማኖት አይደለም፣ ክርስትና በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ እንደ መሆኑ ሥጋ የለበሰና ሕያው የሆነ እንጂ በጽሑፍ የተቀመጠ የማይናገር ቃል አይደለም። ቅዱሳት መጽሐፍት ሙዉት መልዕክቶች ሆነው እንዳይቀሩ፣ የሕያው እግዚአብሔር ዘላለማዊ ቃል ክርስቶስ፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ቅዱሳት መጽሐፍትን መረዳት እንችል ዘንድ አእምሮአችንን መክፈት አለበት። በማለት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ቁጥር 108 ላይ የተገለጸውን አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል የእግዚአብሔር ቃል ዘወትር መናገርን የማያቋርጥ፣ በየጊዜው አዲስ እየሆነ የበለጠ ግልጽ በመሆን አብሮን እንደሚጓዝ አስረድተው ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አስገንዝበዋል። ይህ በመሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስን ማግኘትና መከተል ያስፈልጋል ብለው ኢየሱስ ክርስቶስ ለጥቃት እንዳንጋለጥ ከእርሱም እንዳንለይ፣ እንደኛ ሁላችን ደካማ የሆነውን ሰው ጴጥሮስን በአገልግሎት ላይ አስቀምጦታል ብለው ክፉ መንፈስ በመካከላችን ልዩነትን በመፍጠር እንድንለያይ፣ በፍቅር ላይ የተመሠረተ እውነተኛ ነጻነት ከሚሰጠን፣ አዳኛችን ከሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሊለየንና ሊያርቀን ይፈልጋል ብለዋል። የክፉ መንፈስ ፈተናም እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ እያስመሰለ የእርሱ አገልጋዮች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ፒዮስ 10ኛ አደራ፣

እውነተኛውን የእምነት ባሕልን የሚከተል ሁሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ባለ አደራ ጋር ሕብረት አለው፣ እርሱንም ከልቡ ያፈቅረዋል በማለት ር. ሊ. ጳጳሳት ቅዱስ ፒዮስ 10ኛን፣ ሕዳር 9 ቀን 1905 ዓ. ም.  ለካህናት ሐዋርያዊ አንድነት ማህበር ያስተላለፉትን የአደራ መልዕክት፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ያለንን ፍቅር በተግባር መግለጽ ከተፈለገ የመጀመሪያው ተግባር መታዘዝ ነው ብለዋል። ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መታዘዝ ማለት ደግሞ አብረው በመሆን፣ በጋራ በመወያየት ለቀረበው መልክት ትክክለኛን ሃሳብ ለመረዳት መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ጥያቄውንም በቃል ብቻ ሳይሆን በጽሑፍም ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ትዕዛዝ ጥርጣሬ ሊገባን አያስፈልግም ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሚለይ ባሕል የለም፣

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ያስገኛቸውን የተሃድሶ መንገዶችን በመመርኮዝ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ፣ ለብጹዕ አቡነ ለፈብሬ በጻፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ ከሐዋርያት ዘመን አንስቶ ቤተክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ እገዛ እንዳልተለያት የገለጹትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል። ቤተክርስቲያን ከሐዋርያት ዘመን አንስቶ ስትከተል የቆየችውን እምነት፣ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስንና እንደ ቤተክርስቲያን መስራች፣ የቤተክርስቲያንን አንድነት እንዲያስጠብቅ ለአገልግሎት የሰየመውን ሐዋርያው ጴጥሮስን ወደ ጎን ማድረግ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ታማኝነትን ማጉደል ይሆናል ብለዋል።

አብሮ የመጓዝ መልካምነት፣

15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ቢጠናቀቅም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለን ግንኙነት ይቀጥላል፣  ከዚህም የሚገኘውን ደስታ እንድንመሰክር ተጠርተናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሕብረት በመጓዝ የሚገኝ የአንድነትን ውበት፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ሊኖር የሚገባው የጠበቀ ግንኙነት፣ መንፈስ ቅዱስ የሚለውን ማዳመጥ፣ ሊከፋፈል የሚፈልገውን ክፉ መንፈስ መቃወም፣ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ የቃረበውን ጸሎት በእምነት ማደረስ ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ በታች የሚገኘውን ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ

                     

30 October 2018, 16:23