ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ክርስቲያን እውነተኛን እንጂ የግብዝነት ሕይወት መኖር የለበትም”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ ከሚያደርጉት ከእኩለ ቀን የብስራተ ገብሬል ጸሎት በፊት በዕለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በመመርኮዝ አስተንትኖ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሠረት በትላንትናው ዕለት ማለትም እሁድ ነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ. ም. ከማር. 7. 1-8 14-15 እና 21-23 በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው ባደረጉት አስተንትኖ እንደ ገለጹት፣ ክርስቲያን እውነተኛ ሕይወትን እንጂ የግብዝነት ሕይወት መኖር የለበትም ብለዋል። ክቡራትና ክቡራን አድማጮቻችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ትናንት እሑድ በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት በሺዎች ለሚቆጠሩ ምዕመናንና ሀገር ጎብኝዎች ያደረጉትን የወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ተርጉመን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ

በዛሬው እሑድ ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ ወደ ጻፈው ቅዱስ ወንጌል ተመልሰን በምናስተነትንበት ጊዜ  በዚህ የወንጌል ክፍል ማለትም በማር. 7. 1-8፣ 14-15 እና 21-23 የተጻፈውን በምናነብበት ጊዜ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ፣ በእርሱ ለምናምን በሙሉ አንድ ወሳኝ የሆነ ርዕሰ-ጉዳይ በማንሳት ይናገረናል። ይህም ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ ስለ መሆንና ከማንኛውን የዓለማዊ እድፍና ከግብዝነት ራሳችንን ስለ መከላከል ነው። መልዕክቱ የሚነሳው የሙሴ ሕግ መምህራንና ፈሪሳዊያን፣ ሐዋርያት የሽማግሌዎችን ወግና ሥርዓት በመጣሳቸው የተነሳ እየከሰሷቸው ወደ ኢየሱስ ዘንድ ስለመቅረባቸው ነው። የሙሴ ሕግ መምህራንና ፈሪሳዊያን ይህን ያደረጉበት ዋና ዓላማ የኢየሱስን ክርስቶስን ስልጣን በመቃወም እርሱን ለመውጋት ፈልገው ነው። ኢየሱስን እንዲህ ይሉት ነበር፣ ይህ መምህር ደቀ መዛሙርቱ  የሽማግሌዎችን ወግና ሥርዓት ሲጥሱ ምንም አይላቸውም።  ኢየሱስ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፣ እናንተ ግብዞች፣ ኢሳያይስ ስለ እናንተ “ይህ ሕዝብ በአፉ ብቻ ያከብረኛል እንጂ ልቡ ከእኔ በጣም የራቀ ነው፣ የሰውንም ሥርዓት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል”። ኢየሱስ የተናገረው ቃል ግልጽና ከበድ ያለ ነው። እርሱም ግብዝነት የሚል ነው። ግብዝነት የሚለው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ ከሚጠቀማቸው ጠንከር ካሉት ቃላት መካከል አንዱ ነው። ግብዞች ያሏቸውም እነዚያን የሐይማኖት መምህራን ነን፣ አዋቂዎች ነን  የሚሉትን ነበር።       

ኢየሱስ የሙሴ ሕግ መምህራንና ፈሪሳዊያን ግብዞች ያላቸው፣ ከወደቁበት ስህተት ለማውጣት ስለፈለገ ነው። እነዚህ ሰዎች የወደቁበት ስህተት ምን ነበር? ስህተታቸው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማቃለል ነበር። ትዕዛዞቹን ችላ ብለው የሰውን ሥርዓቶችንና ልምዶች ማክበራቸው ነበር። በዚህም የኢየሱስ ክርስቶስ አቋም ጠንከር ያለበት ምክንያት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሊኖር ስለሚገባው እውነተኛ ክርስቲያናዊ ሕይወትን ስለሚመልከት ነበር። ምክንያቱም ግብዝነት እውነተኛ ያልሆነ የውሸት ሕይወት ነውና።

ዛሬም ቢሆን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጋብዘን ለክርስትና ሕይወት አደገኛ ከሆነው ግብዝነት አምልጠን  ለእግዚአብሔር ፈቃድ የበለጠ ትኩረት እንድንሰጥ ነው።  ዘወትር የሚጠራንም፣ የእምነታችን መሠረት የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ሌሎች በተግባር መግለጽ ስላለብን ፍቅር ጠንቅቀን እንድናውቅ ነው። ይህን የእግዚአብሔር ፍቅር ከግብዝነት የጸዳ እንዲሆን ማድረግ ይኖርብናል።  

የዛሬው የወንጌል መልዕክት በሐውርያው ያዕቆብ መልዕክት የታገዘ እንደሆነ እንገነዘባለን። ሐውርያው ያዕቆብ እውነተኛው ሐይማኖት ምን መምሰል እንዳለበት ሲናገ፥ “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው”። (የያዕ. መ 1፤27)

ወላጆች የሌላቸውን ልጆችንና ባልቴቶችንም፣ በመከራቸው ጊዜ መጠየቅ ማለት፣ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው፣ በችግር በቀላሉ ለሚጠቁና በሕብረተሰቡ መካከል ለተናቁ በሙሉ ቸርንርትን በማድረግ፣ ፍቅርን በተግባር ማሳየት ማለት ነው። እነዚህ ችግርተኞች እግዚአብሔር በተለየ መንገድ በየዕለቱ የሚያስብላቸው ስለሆነ እኛም እንደ እርሱ እንድናስብላቸው ይጠይቀናል።  

“በዓለም ላይ ከሚገኝ እድፍ ራስን መጠበቅ ነው” ማለት ከእውነታ ራስን ማግለል ማለት አይደለም። ፈጽሞ እንዲህ ማለት አይደለም። ራስን ማግለል ስንል ውጫዊውን ሰውነታችንን ሳይሆን በአንዳንድ በተሳሳተ የዘመኑ አስተሳሰብ ምክንያት ውስጣዊ ማንነታችንን በከንቱነት በስግብግብነትና በትዕቢት እንዳይበከል ነቅተን መመልከት ያስፈልጋል። በከንቱነት በስግብግብነትና በትዕቢት ተውጦ የሚኖር አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት፣ በሌላ ወገን የክርስቲያን ሕይወት የሚኖሩ እየመሰሉ በሌላ ላይ የሚፈርዱ ከሆነ፣ የግብዝነት ሕይወት የሚባለው እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት ነው።

የእግዚአብሔርን ቃል ወደ ልባችን ውስጥ እንዴት እንደምንቀበል እናስተውል። በየእሁዱ በመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት መካከል የእግዜብሔር ቃል ሲነበብ ወይም ሲሰበክ እንሰማለን። በዚህን ጊዜ በጽሞና አስተውለን ካላዳመጥነው፣ ነገር ግን በሌላ ነገር የምንረበሽ ከሆነ ብዙም ጥቅም አናገኝም። ነገር ግን ቃሉ ሲንበብና ሲሰብክልን አእምሮአችንንና ልባችን ከፍተን መቀበል ያስፈልጋል፣ ፍሬን እንደሚሰጥ እንደ ለም መሬት ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው የዘሪው ምሳሌ፣ በመልካም መሬት የተዘራ ዘር ብዙ ፍሬን ያፈራል። የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኛ ውስጥ ገብቶ ፍሬን መስጠት መቻል ያስፈልጋል። የእግዜብሔር ቃል ልባችንን በማንጻት በመልካም ሥራዎቻችን ከእግዚአብሔር ጋር፣ ከወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት እውነተኛ በማድረግ ከግብዝነት ነጻ ያደርገናል።

እግዚአብሔርን ከልባችን በማክበር፣ ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለሌሎች በምናደርገው መልካም ተግባር መግለጽን እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ትርዳን”።

02 September 2018, 18:27