ፈልግ

2018.09.27 Papa Francesco - Partecipanti al Corso di formazione promosso dal Tribunale della Rota Romana 2018.09.27 Papa Francesco - Partecipanti al Corso di formazione promosso dal Tribunale della Rota Romana 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የጋብቻን ክብር ለሌሎች መስክሩ”።

ብዙን ጊዜ ከጋብቻ በኋላ በትዳር መካከል ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች የጋብቻን ምስጢር በሚገባ ካለመረዳት የተነሳ በድንገት የሚመጣ ችግር ብቻ ሳይሆን በክርስትና እምነት መዳከም ምክንያት፣ ወጣት ተጋቢዎች ከጋብቻ በኋላ ከቤተክርስቲያናቸው ወይም ከቁምስናቸው በኩል ሊደረግ የሚገባው እንክብካቤ ሲጓደልባቸው በሚሰማው የብቸኝነት ስሜት ምክንያት ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም በሚገኘው በላተራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲትይ በጋብቻና በቤተስብ እንክብካቤ ላይ ስልጠናን በመከታተል ላይ ላሉት አባላት ባደረጉት ንግግር የጋብቻን ክብር እንዲመሰክሩና በችግር ላይ የወደቁትን ባለትዳሮች መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ። በዚህ ማሳሰቢያቸው በችግር ውስጥ ያሉ ባለትዳሮች ከምስጢረ ተክሊል የሚገኘውን ፀጋን በድጋሚ  እንዲገነዘቡ መርዳት፣ በአንዳንድ አጋጣሚዎችም እስከመፋታት ለሚደርሱ ባለትዳሮች ሕጋዊ ሂደቶችን በማሳየት መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በመጀመሪያዎቹ የጋብቻ ዓመታት ለባለ ትዳሮች ክትትል በማደረግ ምክሮችን መስጠት፣ ከምስጢረ ተክሊል የሚገኘውን ጸጋ አስቀድሞ ከሚሰጠው ትምህርት በሚገባ እንዲገነዘቡ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ 850 ለሚያህሉ ለሰልጣኞች አስረድተው ምስጢረ ተክሊል ምስጢራትን የሚያድሉ ካህናት፣ የቤተሰብን ጉዳይ በቅርብ ሆነው የሚከታተሉ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራንንና የክርስቲያን ባለትዳሮችን አብሮ መስራትን የሚጠይቅ እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። 

በሚገባ ተረድተው የሚያደርጉት ውሳኔ፣

የቤተሰብን ጉዳይ በስፋት በመመልከት በስልጠናው የተካተቱ ሐዋርያዊ ርዕሶችን ያነሱት ቅዱስነታቸው ክርስቲያናዊ ጋብቻ በቤተክርስቲያን እና በሕብረተሰብ ውስጥ የሕይወት መሠረት እንደሆነ አስረድተው በተጨማሪም ለሕዝቦች የጋራ ጥቅም የቆመ ሰፊ፣ ውስብስብ የሆነ ሐዋርያዊ ዘርፍ እንደሆነ ገልጸዋል። ከፍቅር የሚገኝ ደስታ በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ስለቤተሰብና ስለ ጋብቻ በስፋት ማስረዳታቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ክርስቲያናዊ ጋብቻን ለመፈጸም ረጅምና በቂ ዝግጅት ማድረግ  እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ጋብቻ ባሕላዊ ወይም ማሕበራዊ ስነ ስርዓት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ጸጋዎች የሚገለጥበት በመሆኑ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ እንዲሁም በሚገባ ተገንዝበው የሚያደርጉት ውሳኔ እንደሆነ አስረድተው ሁለቱ ተጋቢዎች ብጋራ ሆነው አምነውበትና ወስነውበት፣ አንዱ ለሌላው የገባውን ቃል ኪዳን ላለማፍረስ ቆርጠው የሚገቡበት ሕይወት እንደሆነ አስረድተዋል።

ወጣት ተጋቢዎችን ብቻቸውን መተው አያስፈልግም፣

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረስብከቶች በቤተሰብ ዙሪያ ወቅታዊ የሆኑ ሐዋርያዊ እቅዶችን አውጥተው ስልጠናዎችን፣ ሱባኤዎችንና የጸሎት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ለክርስቲያን ወጣት ባለትዳሮች የስነ ልቦና ድጋፍና የቤተሰብ ተሞክሮን እያካፈሉ መሆናቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግረዋል። ብዙን ጊዜ ከጋብቻ በኋላ በትዳር መካከል ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች የጋብቻን ምስጢር በሚገባ ካለመረዳት የተነሳ በድንገት የሚመጣ ችግር ብቻ ሳይሆን በክርስትና እምነት መዳከም ምክንያት፣ ወጣት ተጋቢዎች ከጋብቻ በኋላ ከቤተክርስቲያናቸው ወይም ከቁምስናቸው በኩል ሊደረግ የሚገባው እንክብካቤ ሲጓደልባቸው በሚሰማው የብቸኝነት ስሜት ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የጋብቻ ሕይወት እንቅፋት ሊያጋጥመው የሚችለው በዕለታዊ ሕይወታቸው መካከል እድገትን ሊያመጡ የሚችሉ መስዋዕትነትን አንዱ ለሌላው ካለማድረግ የተነሳም ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።

ዝግጅትና እገዛ ከጋብቻ በኋላም ያስፈልጋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን በመቀጠል ወደ ምስጢረ ተክሊል የሚያደርስ ዝግጅት እየጨመረ በመጣ ቁጥር ወጣት ተጋቢዎች ስለ ምስጢረ ተክሊል ጸጋና ከእግዚአብሔር ስለሚቀበሉት እርዳታ የበለጠ እየተገነዘቡ እንደሚመጡ፣ የሚያጋጥማቸውን ዕለታዊ ችግሮች ለመቋቋም ጥረት ያደርጋሉ ብለዋል። ለወጣት ተጋቢዎች የሚሰጠው ሐዋርያዊ እንክብካቤ፣ በጋብቻቸው ዕለት የሚያበቃ ሳይሆን ከጋብቻቸው በኋላም ለተወሰኑ የመጀመሪያ ዓመታት ጭምር የሚዘልቅ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። በማከልም ከወጣት ተጋቢዎች ጋር በግልም ሆነ በጋራ መገናኘት የሚቻልበትን አጋጣሚዎች በማመቻቸት የጋብቻ ጥሪያቸውን በደስታ ሊኖሩበት የሚያስችላቸውን የምክር አገልግሎትን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። ይህን መንገድ የሚከተሉ ከሆነ ባለትዳሮች በእምነታቸው እንዲያድጉ የሚያደርጋቸውን ጸጋ ሊያገኙ ይችላሉ።

በጋብቻ ላይ የሚከሰቱ ችግሮችና አዲስ መንገድ፣

በኑሮአቸው መካከል የተለያዩ ችግሮች የሚያጋጥሟቸውን ወጣት ባለትዳሮን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እምነታቸውን እንዲያሳድሱና ከምስጢረ ተክሊል የሚገኘውን መንፈሳዊ ጸጋን እንዲረዱ ማገዝ ያስፈልጋል ብለው አንዳንድ ጊዜ በትክክለኛ እና ውስጣዊ ነፃነት በመጠቀም የደረሰባቸውን ችግሮች መመልከት እንደሚያስፈልግ አስታውሰው በአንዳንድ አጋጣሚዎችም እስከመፋታት ለሚደርሱ ባለትዳሮች ሕጋዊ ሂደቶችን በማሳየት መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በርካታ ባለ ትዳሮች በቤተክርስቲያን ምስጢረ ተክሊልን ከተቀበሉ በኋላ የጀመሩት ሕይወት ትክክለኛ አለመሆኑን በመገንዘብ ከጳጳሳ ከካህናት፣ ከትምህርተ ክርስቶስ መምህራን እርዳታን በሚጠይቁበት ጊዜ ወደ ሕግ ዘንድ ከመድረሱ አስቀድሞ ስላጋጠማቸው ችግር በእርጋታ ማዳመጥና መረዳት እንደሚገባ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም የጋብቻ ፍችን ቤተክርስቲያን ትክክለኛ ለማደረግ የምትከተላቸውን አዲስ መንገድ በማጤን የመጨረሻ ውሳኔን መውሰድ እንደሚያስፈልግ አሳስበው ይህ ውሳኔ በተለይም ደሃ የሆኑትን ባለትዳሮችን ያስተዋለ መሆን ይስፈልጋል ብለዋል።

ከጋብቻ ውጭ አብረው ለመኖር የወሰኑትን ማሰብ ያስፈልጋል፣

የነፍሳት ዘለዓለማዊ ድነትን ይስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቁምስናም ይሁን በሀገረ ስብከት ለቤተሰብ የሚሰጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት የወንጌልን መልካም ዜና መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበት አሳስበው ይህን በምንልበት ጊዜ ከጋብቻ ሕይወት ውጭ በሆነ መንገድ ለሚኖሩት የጋብቻ ሕይወት ክቡርነትን መመስከር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።          

28 September 2018, 16:41