Sinodo_vescovi_famiglia_2014.jpg Sinodo_vescovi_famiglia_2014.jpg 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የጳጳሳት ሲኖዶስ የተቋቋመው የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማገልገል ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በሕብረት በመሥራት፣ ለቤተክርስቲያን እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ናቸው ለሚባሉት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ልዩ ጥበብና ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል። የወንጌል ተልዕኮን በቋሚነት ለማበርከት ቤተክርስቲያን በደረሰችበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የጳጳሳት ሲኖዶስ የወንጌልን መልካም ዜና ለዛሬው ዓለም ለማዳረስ የተሻለ መንገድ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጭው ጥቅምት ወር 2011 ዓ. ም. የካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት 15ኛው ጠቅላላ መደበኛ ሲኖዶስ በሮም ከመካሄዱ አስቀድሞ ባወጡት ሐዋርያዊ ድንጋጌ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ሲኖዶስ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማገልገል ነው ማለታቸው ታውቋል። በሚቀጥለው ወር የካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በዋናነት የሚወያዩባቸው ሦስት አበይት ርዕሶች ከዚህ በፊት ተመርጠው መቀመጣቸው የሚታወቅ ሲሆን እነርሱም፣ “ወጣቶች፣ እምነታቸውና፣ ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተዋል በታከለበት አኳኋን ለይተው ማወቅ” የሚሉ እንደሆነ ይታወቃል። የብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ድንጋጌ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ ጳውሎስ ስድስተኛ በ1957 ዓ. ም. የደነገጉት እንደነበር ይታወሳል።

ይህ የብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ድንጋጌ፣ መላው ሕዝበ እግዚአብሔር በሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የበላይነት፣ በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከምትመራው ቤተክርስቲያን ጋር የሚያደርገው ውይይት ወደ ብርሃን ጎዳና ሊመራ ይችላል በማለት ያሳስባል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስከረም 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ያወጡት ሰነድ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሚካሄደውና፣ “ወጣቶች፣ እምነታቸውና፣ ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተዋል በታከለበት አኳኋን ለይተው ማወቅ” በሚሉት የመወያያ ርዕሶች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ታውቋል።

ለቤተክርስቲያን እድገት፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ የደነገጉትን ሐዋርያዊ ሰነድ በሚገባ ካስታወሱትና ውድ የሆነ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ውርስ መሆኑን በማስገንዘብ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በሕብረት በመሥራት፣ ለቤተክርስቲያን እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ናቸው ለሚባሉት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ልዩ ጥበብና ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል። የወንጌል ተልዕኮን በቋሚነት ለማበርከት ቤተክርስቲያን በደረሰችበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የጳጳሳት ሲኖዶስ የወንጌልን መልካም ዜና ለዛሬው ዓለም ለማዳረስ የተሻለ መንገድ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

የጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ ጳውሎስ 6ኛ አስቀድመው እንደተመለከቱት፣ ዓመታት በተፈራረቁ ቁጥር የጳጳሳት ሲኖዶስም በዚያው መጠን፣ ዓለማችን ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ጋር እኩል ለመራመድ በማለት በሚያደርገው ጥረት የጳጳሳት ሲኖዶስ መተዳደሪያ ደንቦችን እንደገና በማጤን ማሻሻያን ያደርጋል። በዚህም መሠረት በ1998 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ በጳጳሳት ሲኖዶስ መተዳደሪያ ሰነድ ላይ  ማሻሻያ ማድረጋቸው ይታወሳል። በዚህ የማሻሻያ ሂደት መሠረት የጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሀላፊነቶች እንደገና መዋቀራቸውና ቀስ በቀስ እየተጠናከሩ መምጣታቸው ይታወቃል።                      

ለመላዋ ቤተክርስቲያን አንድነት፤

አሁን መልካም ፍሬው እየታየ የመጣው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጥረት፣ የቤተክርስቲያን አባቶች በየጊዜው ተገናኝተው በመምከር የወሰዱት መልካም እርምጃና ለተለያዩ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ለመስጠት ያደረጉት ጥረት ውጤት እንደሆነ ታውቋል። በዚህም መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደገለጹት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የቤተክርስቲያንን አንድነት በመጠበቅ ውጤታማነቱን እንዲያሳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ምኞት አለ ብለዋል። ይህን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥልቀት ሲያስረዱ፣ የቤተክርስቲያን አባቶች የእግዚአብሔርን ቅዱስ ሕዝብ ለማገልገል ባላቸው ጽኑ እምነትና በተቀበሉት የምስጢረ ጥምቀት ጸጋ  ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ማዳመጥ ያስፈልጋል፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ብጹዓን ጳጳሳት መምህራንም ሐዋርያትም እንደመሆናቸው፣ ተልዕኮአቸውን በትጋት እንዲወጡ በተሰጣቸው ሃላፊነት፣ በሚያገለግሏቸው የእግዚአብሔር ሕዝቦች በኩል የሚደርሳቸውንና የማይካደውን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ማዳመጥ ያስፈልጋል ብለዋል። በዚህም መሠረት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚደመጥበት መሳሪያ ሊሆን የተገባ መሆን ይኖርበታል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም የጳጳሳት ሲኖዶስ የጳጳሳት ጉባኤ በመሆኑ ከተቀሩት የምዕመናን ወገን ተነጥሎ መኖር አይችልም ብለው የጳጳሳት ሲኖዶስ በጳጳሳት ጉባኤ አማካይነት ወይም በእያንዳንዱ ጳጳስ በኩል ለእግዚአብሔር ሕዝብ መመሪያን ለመስጠት የተቋቋመ ነው ብለው የጳጳሳት ጉባኤ በተጨማሪም እምነትን የሚጠብቅ፣ የሚያስተምርና የሚመሰክር ነው ብለዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚካሄዱት የጳጳሳት ጉባኤዎች በጳጳሳዊ ሲኖዶስ በኩል ቤተክርስቲያን የምትገለጥበትና የልዩ ልዩ ባሕሎች አንድነት የሚስተዋልበት እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል። የጳጳሳት ሲኖዶስ በቤተክርስቲያን ውስጥ በምዕመናንና በጳጳሳት መካከል፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትና በጳጳሳት መካከል የጠበቀ ግንኙነት እንዳለ በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል።           

በክርስቲያኖች መካከል አንድነት ይኑር፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሊካሄድ የተቃረበው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቲያኖች መካከል አንድነት እንዲመጣ የበኩሉን አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። የጳጳሳት ሲኖዶስ የአንድነትን ጎዳና በማዘጋጀት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደተናገሩት ቤተክርስቲያን የምትመራበትን ጳጳሳዊ የላይነት ስልጣን ተልዕኮ ዘላቂ እንዲሆን ያግዛል ብለዋል።     

19 September 2018, 17:01