ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሊጧኒያ ዋና ከተማ በቪልኒውስ የሚገኘውን ቤተ መዘክር ጎበኙ።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሊጧኒያ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በትናንትና ዕለት በቪልኒውስ ከተማው የሚገኘውን የግዞትና የነጻነት ሙዜምን ለመጎብኘት በሄዱበት ጊዜ ጸሎታቸውን ማቅረባቸው ታውቋል።
በማቴ. ወንጌል ምዕ. 27 ቁ. 47 ላይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ ወደ አባቱ ያቀረበውን፣ አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተወሄኝ የሚለውን የስቃይ ጸሎት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡት የሊጧኒያ ሕዝቦች ከወራሪዎች በኩል የደረሰባቸውን ግፍ፣ ጭቆናና ግድያን አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በሙዜሙ ተገኝተው ባቀረቡት ጸሎት፣ “ጌታ ሆይ! ስቃይ በስቶባቸው ጩሄታቸውን የሚያሰሙትን የልጆችህን ድምጽ ካንተ ድምጽ ጋር አንድ በማድረግ ወደ አባትህ ዘንድ እንድታቀርብ እንለምንሃለን። ስቅለተ አርብ በስቃይ፣ በመሰናከልና በጭካኔ ድርጊት የተመላ መሆኑን ስናስታውስ የሊጧኒያ ሕዝብም ብርቱ የስቃይ የመከራ ጊዜያትን ማሳለፉን እናስታውሳለን።
ጌታ ሆይ የሊጧኒያ ሕዝብ ስቃይ በሚታወስበት በዚህ ቦታ ላይ ተገኝተን ጸሎታችንን ወደ አንተ ስናቀርብ ያንተ የስቃይ ጩሄት ዘወትር እንዲያነቃን እንለምንሃለን። ያንተ የስቃይ ጩሄት ከመንፈሳዊ በሽታዎች በመፈወስ የመከራንና የስቃይን ሕይወት ያሳለፉትን አባቶቻችንን እንድናስታውስ ይርዳን ብለን እንለምንሃለን።
ባንተ የስቃይ ጩሄትና እንዲሁም የስቃይን ሕይወት ካሳለፉት ከአባቶቻችን ጥንካሬና ድፍረት በመታገዝ አንተ የሰጠሄንን ሰብዓዊ ክብር ለማሳነስ የሚጥሩትን ተግባራት ዛሬም ቢሆን ወደ ፊት ነገ እንድንቃወምና እንድንዋጋ እርዳን።
ጌታ ሆይ ሊጧኒያ የተስፋ ብርሃን እንድትሆንና ማንኛውንም ኢፍትሃዊ ተግባርን ለመቃወም ጥረት የሚደረግባት ሀገር ትሁን፣ የእያንዳንዱን ሰው መብት ለማስከበት ጥረት የሚደረግባት አገር ትሁን፣ የተለያዩ ሕዝቦች እርቅን በማውረድ ተስማምተው በጋራ መኖርን የሚማሩባት አገር ትሁን።
ጌታ ሆይ የስቃይና የመከራ ጩሄታቸውን ወደ አንተ ወደ ዘንድ በማቅረብ ላይ ያሉትን የልጆችህን ድምጽ የምናዳምጥ እንድታደርገን እንለምንሃለን በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።