ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከ25ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሊጧኒያ በሌቶኒያና በኤስቶኒያ ያደረጉትን 25ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ሲመለሱ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በጉዞ ላይ እያሉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው፣ ከቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ጋር የተደረሰው ስምምነት የእርሳቸው ምኞት እንደሆነ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫቸው በሊጧኒያ፣ በሌቶኒያና በኤስቶኒያ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝትና የጦር መሣሪያ ውግዘት አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ መስጠታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከረጅም ዓመታት የጭቆናና የጦርነት ዓመታት በኋላ ዛሬ ወደ ነጻነት ጎዳና ያመሩትን እነዚህን ሦስቱን የባልቲክ አገሮች በማስመልከት በሰጡት አስተያየታቸው በመካከላቸው እውነተኛ እርቅን የማድረጋቸው ምልክት እንደሚታይና መልካም የወደፊት ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡበት መልስ እንዳስረዱት ሊጧኒያ፣ ሌቶኒያና ኤስቶኒያ በጨካኝ ወራሪ ሃይላት ነጻነታቸውንና ማንነታቸውን ተነፍገው የቆዩ መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም ዛሬ በማጣጣም ላይ ያሉትን ነጻነት በመጠቀም ለወጣቱ ትውልድ መልካም ባሕላዊ፣ መንፈሳዊና የስነ ጥበብ እሴቶችን የማስተላለፍ ግዴታ አለባቸው ብለዋል። በቪልኒውስ ቤተ መዘክር የተመለከቱትንና በሕዝቡ ላይ ይደርስ የነበረውን ስቃይና ግድያን በማስታወስ ለዚህ ሁሉ ስቃይ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር አስተዋጽዖ እንዳደረገ አስረድተዋል። አንድ መንግሥት የአገርን ሉዓላዊነት የማስከበርና ጸጥታን የማስጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ቢታመንም ይህን ታዲያ ምክንያታዊ መንገዶችን በመጠቀም ያለጦርነት በሰላማዊ መንገድ ማከናወን እንዳለበት አስረድተዋል። የስደተኞችን ጉዳይ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ የባልቲክ አገሮች መሪዎች እንግዳን ተቀብሎ የማስተናገድ ባሕል ታላቅነት የተገነዘቡ ይመስላል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በእነዚህ ቀናት ውስጥ በዜና ማሰራጫዎች በስፋት ስለሚነገረው የቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥትና የቅድስት መንበር ግንኙነት ወደ መልካም አቅጣጫ መመለሱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫቸው በሁለቱ ወገኖች መካከል ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ውይይት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው፣ ሃላፊነትን በመውሰድ እርሳቸው የፈረሙት ይህ ጊዜያዊ ስምምነት እስካሁን በስደት ላይ ለኖረች የቻይና ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መልካም የተስፋ ጭላንጭል እንድታይ ማድረጉን ገልጸው አሁንም በጸሎት መበርታት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ አጋጣሚ ረጅም ዓመታትን በወሰደው ውይይት ላይ የተሳተፉትን የቅድስት መንበር ተወካዮች፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ አቡነ ቼሊንና ክቡር አባ ሮታ ግራሲዮሳን አመስግነው የቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናን የእምነት ጥንካሬንና የብጹዓን ጳጳሳት ሕብረትን አወድሰው ከቅድስት መንበር ጋር ያላቸውን አንድነት በተግባር ያስመሰከሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።                   

25 September 2018, 17:50