VATICAN-POPE-AUDIENCE VATICAN-POPE-AUDIENCE 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ፡ ከእግዚኣብሔር ጋር ሐሰተኛ የሆነ ግንኙነት ማድረግ በፍጹም አይገባም!

ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ማንም ሰው ራሱን ሊያዋርድ እና በራሱ ሕልውና ላይ ከፉ የሆነ ነገር ማሰብ አይችልም።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረዕቡ እለት በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ወይም ደግሞ እዳስፈላጊነቱ እና እንደ አየሩ ሁኔታ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በዚህም መሰረት በሰኔ 6/2010 ዓ.ም ቀትር ላይ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ባደርጉት የክፍል አንድ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ገለጹት “እግዚኣብሔር ገዢያችን ሳይሆን አባታችን ነው” ማለታቸውን መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን በሰኔ 13/2010 ዓ.ም ደግሞ አሁንም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ባደረጉት የክፍል ሁለት የጠቅላላ አስተምህሮ “የእግዚኣብሔርን ቃል ኪዳን በሕይወታችን ለመተግበር በሚያስችሉን” ዐሥርቱ ትዕዛዛት ዙሪያ ላይ ያተኮረ አስተምህሮ ማደርጋቸውንም መገለጻችን ይታወሳል።

በሰኔ 20/2010 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባደረጉት የክፍል ሦስት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ሕግ ከእግዚእብሔር ፍቅር በላይ ሆኖ ሲታይ ትርጉም ያጣል፣ እመንት ሊጀምር የሚገባው ከነጻናት ስሜት ነው እንጂ ከግዴታ ሊሆን አይገባውም” ማለታቸውን መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ከዚያም በመቀጠል በሰኔ 27/2010 ዓ.ም ባደረጉት የክፍል ዐራት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከአስርቱ ትዕዛዛት የመጀመሪያው በሆነውን “ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አትምልክ” በሚለው የመጀመሪያው ትዕዛዝ ዙሪያ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የጠቅላላ አስተምህሮ ማድረጋቸውን መገለጻችን ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በነሐሴ 02/2010 ዓ.ም ያደርጉት ክፍል አምስት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መሰርቱን አድርጎ የነበረው “ጣዖትን አታምልክ” በሚለው ሁለተኛው ትዕዛዝ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የነበረ ሲሆን “በተከፈተው የድክመታችን በር የእግዚኣብሔር የማዳን ኃይል ይገባል” ማለታቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከዚህ በፊት በተከታታይ ቀጣይነት ባለው መልኩ በዐስርቱ ትዕዛዛት/ቃላት ላይ ተመርኩዘው አድርገውት የነበረውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ይህንን ያህል ካስታወስናችው በዛሬው ዕለት ማለትም በነሐሴ 16/2010 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ለተገኙ ምዕመናን ያደረጉት  የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ” (ዘጸ. 20፡7) በሚለው ሦስተኛው ትዕዛዝ ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በዚህ ላይ ተመርኩዘው ባደረጉት አስተምህሮ “ከእግዚኣብሔር ጋር ሐሰተኛ የሆነ ግንኙነት ማድረግ በፍጹም አይገባም” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በነሐሴ 16/2010 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ለተገኙ ምዕመናን ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል፣ አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ዕለት አስተምህሮዋችን የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ” (ዘጸ. 20፡7) የሚለውን ትዕዛዝ እንመለከታለን። በእርግጥ ይህንን ቃል በምናነብበት ወቅት የአምላክን ስም ያለአግባቡ እንዳንጠቀም እና የእግዚኣብሔርን ስም ያለቦታው እንዳሻን እንዳንጠቀም የቀረበልን ግብዣ እንደ ሆነ እንረዳለን። ይህ ግልጽ ትርጓሜ እነዚህን ውድ ቃላት የበለጠ ለማብራራት ያዘጋጀናል።

እስቲ በደንብ እናዳምጥ! በከንቱ አትጥራ” የተሰኙ ቃላት በዕብራይስጥ እና በግሪክ ቋንቋ ትርጓሜዎች እንዲሁ በግርድፉ ሲታይ ለራስህ አታውለው፣  ለራስህ ጥቅም አታድርገው” የሚለውን ትርጓሜ ያሰማል።

በከንቱ” የሚለው አገላለጽ ደግሞ በጣም ግልጽ የሆነና በባዶ፣ ምንም የሌለው” የሚሉትን ትርጓሜዎች የሚያሰማ ሲሆን እነርሱም የሚያመለክቱት ባዶ የሆነ እቃ እና ይዘት የሌለው ነገርን ያመለክታሉ። ይህ የግብዝነት፣ ነገሮችን ለይስሙላ የማድረግ እና የውሸት ባህሪ ያመለክታል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ስም” ስለ ነገሮች እና በተለይም ስለ ሰዎች ጥልቅ እውነቶችን መግለጫ ነው። ብዙን ጊዜ ስም ተልዕኮን ይወክላል። የሕይወታቸው አቅጣጫ መለውጡን ለማሳየት አዲስ ስም የተቀበሉትን (ኦዘ. 17፡5) ውስጥ የተጠቀሰውን የአብርሃምን እና በቅዱስ ወንጌል (ዮሐ. 1፡42)  ውስጥ የተጠቀሰውን  የስምዖን ጴጥሮስን ታሪክ በምሳሌነት ለመውሰድ ይቻላል። የእግዚአብሔርን ስም በትክክል ማወቅ በራሱ በሕይወት ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ያደርጋል፣ ሙሴ የእግዚኣብሔርን ስም በትክክል ባወቀ ጊዜ ታሪኩ ሲልወጥ አይተናል (ዘጸ.3፡13-15)።

በአይሁዳዊያን ስርዓተ አምልኮ የእግዚኣብሔር ስም የሚጠራው በታላቁ የይቅርታ ቀን ላይ ብቻ ሲሆን ይህም የሚሆነው ሕዝቡ ይቅርታን የሚያገኘው የእግዚኣብሔርን ስም በሚጠራበት ወቅት መሐሪ ከሆነው ከእግዚኣብሔር ምሕረት ጋር በቀጥታ ሰለሚገናኝ ነው።

ከዚያም "የእግዚአብሔርን ስም መውሰድ" ማለት ከእርሱ ጋር ጠንካራና የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር እውነታውን መቀበል ማለት ነው። ለእኛ ክርስቲያኖች ይህ ትዕዛዝ "በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም" መጠመቃችንን እንድናስታውስ የሚያደረግ ጥሪ ነው፣ ይህንንም ብዙን ጊዜ የመስቀል ምልክት በማድረግ በምናማትብበት ወቅት እናረጋግጠዋለን፣ በዕለት ተዕለት ተግባራችን ከእግዚያብሔር ጋር በኅብረት ለመኖር እና በእውነቱ ይህም ማለት በእግዚኣብሔር ፍቅር ለመኖር ያለንን ቁርጠኝነት እናረጋግጣለን ማለት ነው።

የእግዚአብሔር ስም በግብዝነት፣ በይስሙላ እና በከንቱ የራሳችን መጠሪያ አድርገን መጠቀም ይቻላል ወይ? በማለት አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። ያለመታደል ሆኑ መልሱ “አዎን” የሚል አዎንታዊ ምላሽ ነው። አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሐሰት ግንኙነት መስርቶ መኖር ይችላል። እናም እነዚህ ዐስርቱ ትዕዛዛት ያለ ግብዝነት ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘትና ማንነታችንን በሙሉ ለእርሱ በአደራ በማስረከብ ከእርሱ ጋር እውነተኛ የሆነ ዝምድና እንድንመሰርት የቀረበልን ጥሪ ነው። እኛ ሁላችንም ማንነታችንን ለእግዚኣብሔር በማስረከብ ከእርሱ ጋር እስከ መጨረሻው ድረስ ለመኖር ራሳችንን ካላዘጋጀን፣ በእጆቻችን እርሱን በመንካት በእርሱ ውስጥ ሕይወት ማግኘት ካልቻልን ሕይወታችን እንዲሁ እንደ ዋዛ አንድ ንድፈ-ሐሳብ ሆኖ ብቻ ይቀራል ማለት ነው።

ይህ ልብን የሚነካ ክርስትና ነው። ቅዱሳን ልብን መንካት የቻሉት እንዴት ነው? ምክንያቱም በቅዱሳን ውስጥ ልባችን የሚመኘውን ሐቀኝነት፣ እውነተኛ ግንኙነት እና ስር-ነቀል ለውጥ ስለምንመለከት ነው። ይህም እውነታ “በበራችን አጠገብ የሚገኙ ቅዱሳንን”  ለምሳሌም ለልጆቻቸው መልካም አብነት ለመሆን በተጨባጭ ሁኔታ የሚጥሩ፣ የዋህ የሆኑ፣ታማኝ እና ለጋሽ የሆኑ ቤተሰቦችን ሳይቀ የሚመለከት ጉዳይ ነው።

ያለምንም ግብዝነት የእግዚኣብሔርን ስም የራሳቸው አድርገው የሚወስዱ ክርስቲያኖች የሚበራከቱ ከሆነ፣ አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ውስጥ የሚገኘውን ስምህ ይቀደስ”  የሚለውን በቀዳሚነት በሕይወታቸው የሚለማመዱ ከሆነ፣ ቤተ ክርስቲያን የምታውጀው ነገር ሁሉ በይበልጥ ተደማጭነትን ያገኛል፣ ቤተ ክርስቲያን የበለጠ ታማኝ እንድትሆን ያደርጋል። እውነተኛ ሕይወታችን የእግዚአብሄርን ስም የሚገልጽ ከሆነ፣ ምስጢረ ጥምቀት ምን ያህል ውብ እንደ ሆነና ቅዱስ ቁርባን ለምን ታላቅ ስጦታ እንደ ሆነ እናያለን! በእኛ አካል እና በእርሱ በክርስቶስ አካል መካከል ያለው እጅግ የላቀ ውህደት እርሱ በእኛ ውስጥ እና እኛም በእርሱ ውስጥ እየኖርን መሆናችንን እረዳለን።

ክርስቶስ በመስቀል  ላይ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ማንም ሰው ራሱን ሊያዋርድ እና በራሱ ሕልውና ላይ ከፉ የሆነ ነገር ማሰብ አይችልም።  ምክንያቱም እርሱ ለእኛ አንድ ነገር ፈጽሞልናል። የእያንዳንዳችን ስም በእርሱ ትከሻ ላይ ይገኛል። የእግዚኣብሔርን ስም የራሳችን መጠሪያ ማድረግ በራሱ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ሲሆን ምክንያቱም እርሱ በጥልቀት የእኛን ስም እስከ መጨረሻ፣ በውስጣችን ክፉ ነገሮች ቢኖሩም እንኳን እርሱ በልባችን ውስጥ ዘልቆ በመግባት የእርሱን ፍቅር በልባችን ውስጥ ስለሚያኖር ነው። እግዚአብሔር በትዕዛዙ እኔ የራሴ አድርጌ ስለወሰድኩህ እንተም የራስ አድርገህ ውሰደኝ” በማለት ያወጀውም በዚህ ምክንያት ነው። ማነኛውም ሰው በማነኛውም ሁኔታ ውስጥ ሁሉ የጌታን ቅዱስ ስም፣ ታማኝ፣ አፍቃሪ እና መሐሪ የሆነ ስሙን ሊጠራ ይችላል። እግዚአብሔር ከልብ በሚጠራው ልብ ላይ አይጨክንም።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
22 August 2018, 10:12