Papa Francesco - Viaggio Apostolico in Irlanda - IX Incontro Mondiale delle Famiglie a Dublino 2018.08.25 Papa Francesco - Viaggio Apostolico in Irlanda - IX Incontro Mondiale delle Famiglie a Dublino 2018.08.25  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በአይርላንድ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናን አቅርበው ንግግርም አሰምተዋል።

ቤተክርስቲያን የቤተሰቦች ሕብረት እንደመሆኗ፣ እነዚህ ቤተሰቦች፣ በሕብረተሰብ መካከል ሊያከናውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበሉትን አደራ በታማኝነትና በደስታ እንዲፈጽሙ ማገዝ ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 24ኛቸው የሆነውን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ. ም. ወደ አይርላንድ መጓዛቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ወደ ዳብሊን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ከመንግሥት ባለስልጣናትና ከሃይማኖት መሪዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ከዚህ በመቀጠልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዳብሊን ቤተ መንግሥት ተገኝተው ለአይርላንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት እና ለዲፕሎማቲክ አካላት ንግግር ማደርጋቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናትና የዲፕሎማቲክ አካላት በሙሉ በደረጉት ንግግር፣ በቅድሚያ በመንግሥት ምክር ቤት የባሕልና ሃይማኖት ሚኒስቴር ላደረገላቸው ጥሪ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበው እንዲሁም ከአይርላንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና ከዲፕሎማቲክ አካላት ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው በዓለም ዘንድ በሚታወቀው በአይርላንድ ሕዝብ የእንግዳ አቀባበል ሥነ ሥርዓት ለተደረገላቸው አቀባበል የአይርላንድ መንግሥት ፕሬዚደንትን አመስግነው  በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት የሰሜን አይርላንድ የመንግሥት ልኡካን ልባዊ አድናቆታቸውን ከምስጋና ጋር ገልጸውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው ወደ አይርላንድ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ፣ በዳብሊን ከተማ በመካሄድ ላይ ባለው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እንደሆነ ገልጸዋል። ንግግራቸውን በመቀጠል  ቤተክርስቲያን የቤተሰቦች ሕብረት እንደመሆኗ፣ እነዚህ ቤተሰቦች በሕብረተሰብ መካከል ሊያከናውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበሉትን አደራ በታማኝነትና በደስታ እንዲፈጽሙ ለማገዝ ነው ብለዋል። በዳብሊን በመካሄድ ላይ ያለው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ፣ ቤተሰቦች የተጠሩበትን ዓላማ በፍቅርና በታማኝነት ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ፣ ከእግዚአብሔር ለተቀበሉት መለኮታዊ የሕይወት ስጦታዎች በሙሉ ክብርን ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ሌሎችን በማስተማርና በመምከር ማሕበራዊ እድገትን ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት ለመመስከር እድል እንዲያገኙ ለማድረግ ነው ብለዋል።

ከትውልድ ወድ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ ውድ የሆኑ መንፈሳዊና ስነ-ምግባራዊ እሴቶች በክብር ተጠብቀው በመቆየት በዚህ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ ላይ ምስክርነት ሲሰጥባቸው መስማት ደስታን ይሰጠኛል ብለዋል። ፈጣን ለውጥ እያሳየ ባለው ሕብረተሰብ መካከል የሚገኘው ቤተሰብ፣ የሚያጋጥሙትን የተለያዩ ችግሮች ለመመልከት፣ ዛሬም ቢሆን ነገ በተለያዩ ደረጃዎች በጋብቻ ሕይወት መካከል የሚታዩ ቀውሶችን በቀላሉ ለመገንዘብ ወይም ለመመልከት ነብይ መሆን አያስፈልግም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቤተሰብ የኅብረተሰብ ግድግዳ በመሆኑ በማንኛውም ጊዜና ቦታ የሚሰጠው ትኩረት የበለጠ እንጂ ያነሰ መሆን የለበትም ብለዋል።

የእያንዳንዳችን እድገት የመጣው በቤተስብ ውስጥ በማለፋችን ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በቤተሰብ መካከል ሆነን አብሮ መኖርን፣ ለራስ ብቻ ማሰብ እንደሌለብን፣ ልዩነት ማስወገድን፣ ከሁሉም በላይ እውነተኛ የሆነ የሙሉ ሕይወት ትርጉምን የተማርነው ከቤተሰብ ነው ብለዋል። መላውን ዓለም እንደ አንድ ቤተሰብ ብንመለከተው በስብእናችን መካከል ያለውን ግንኙነት በመረዳት፣ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን፣ በተለይም አቅመ ደካማ ከሆኑት ጋር ሊኖረን የሚገባውን ወዳጅነት ማወቅ እንችላለን ብለዋል። ብዙን ጊዜ የዘርና የጎሳ ጥላቻን፣ ግጭቶችንና ሁከቶችን፣ የሰው ልጅ መሠረታዊ የመብት ጥሰቶችን፣ በሃፍታምና በደሃ መካከል የሚታየውን ልዩነት ለማስወገድ ወይም ለመቀንስ አቅም እንደሌለን ይሰማናል። በእያንዳንዱ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ የአንድ ሕዝብ እውነተኛ ቤተሰብ መሆናችንን ለመረዳት ምን ማድረግ ይኖርብናል! አንዳችን ለሌላው የፍቅርና የእርቅ ባለአደራዎች እንድንሆን የተጠራንበትን ተስፋ መዘንጋት የለብንም ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል፣ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ ወንድማማችና እህትማማች የአይርላንድ ሕዝብ እንዲለያይ ረጅም ዓመታትን የወሰደ ጦርነት መካሄዱን አስታውሰው ከሃያ ዓመታት ጀምሮ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በሰሜን አይርላንድ የተደረገውን የስቅለተ አርብ ዕለት ስምምነት መኖሩንም ጠቅሰዋል። የአይርላንድ መንግሥት የፖለቲካ ባለስልጣናት፣ የሐይማኖት መሪዎች፣ የሰሜን አይርላንድና የብሪታኒያ መንግሥት ከሌሎች አገሮች መንግሥታት መሪዎች ጋር በመተባበር ከፍተኛ የንብረትና የሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት በሆኑት ርእሰ ጉዳዮች ላይ በመምከር ላለፉት ሃያ አመታት ሰላም እንዲነግስ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በማከልም ይህ ታሪካዊ የሆነው የሰላም ስምምነት፣ እስካሁን እንቅፋት ሆነው ለቆዩት ጉዳዮችም በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ጥርጣሬ አስወግዶ መተማመንን በማምጣት ወደ እርቅ እንዲደርሱ መንገድ እንደሚያስገኝ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

እውነተኛ የሰላም ስጦታ የሚገኘው ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ እንደሆነ ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል የሉት ቅዱስነታቸው፣ ይህ ዘላቂ እርቅን የሚያመጣው የሰላም ስጦታ በሰዎች ልብ ውስጥ ዘልቆ ገብቶ ለዓለም ሁሉ ዘንድ መድረስ አለበት ብለው ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ የልባችን መለወጥ እና የሚፈለገውን እርቅና ሰላም ለማየት ጠንካራ መሠረት ያለውን ሕብረተሰብ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል። ለኤኮኖሚ እድገት ብቻ መልፋት ወይም በፍጨርጨር ፍትሃዊ ሕብረተሰብን ለመገንባት አይችልም ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ ቁሳዊ እድገት ይባስ ብሎ በሰዎች መካከል ልዩነትን በመፍጠር፣ በተለይም አቅመ ደካማና ተንከባካቢ የሌላቸው የቤተሰብ ክፍሎች መብት እንዳይከበር መንገድ ከፍቷል ብለዋል።  

25 August 2018, 14:37