ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ፡ “በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን እመቤታችን ማርያም ወደ ልጇ ታቀርባቸዋለች”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከነሐሴ 19-20/2010 ዓ.ም (ለሁለት ቀናት ያህል ማለት ነው) 24ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ የአየርላንድ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ደብሊን አቅንተው እንደ ነበረ መግለጻችን ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዚያው በነበራቸው ቆይታ በሁለተኛው ቀን ጉብኝታቸው የዛሬ 150 አመት ገደማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለ15 በተለያዩ የእድሜ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰዎች ኖክ በመባል በሚታወቀው ስፍራ ውስጥ በወቅቱ ትንሽዬ በነበረችው ቤተ ክርስቲያን አናት ላይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱስ ዮሴፍ እና ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር በጋር በተገለጸችበት ሥፍራ ላይ በሚገኘው የኖክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ተገኝተው የዚህ 24ኛው ዓለማቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማጠናቀቂያን በማስመልከት ለእምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በግል ጸሎት ማድረሳቸው እና በዚያም እርሳቸውን በመጠባበቅ ላይ ለነበሩ 45ሺ ለሚሆኑ ምዕመናን ቅዱስነታቸው ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት በማንኛውም ዓይነት “ስቃይ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን እመቤታችን ማርያም ወደ ልጇ ታቀርባቸዋለች” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በደብልን በሚገኘው የኖክ የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ለተገኙ ከ45 ሺ በላይ ለሚሆኑ ምዕመናን በትላንትናው እለት ማለትም በነሐሴ 20/2010 ዓ.ም ያደርጉትን ንግግር ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ

በዚህ በዓለማቀፍ የቤተሰብ ቀን ላይ ለመገኘት እና በአየርላንድ ሕዝቦች ተወዳጅ የሆነውን ይህንን ቤተመቅደስ ለመጎብኘት እድል በማግኘቴ እግዚኣብሔርን ላመሰግን እውዳለሁ። ሊቀ ጳጳስ ኒዬሪን እና የእዚህ ቤተመቅደስ የበላይ ጠባቂ የሆኑት አባ ጊቦንስ ደማቅ አቀባበል ስላደርጉልኝ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተገለጸችበት የጸሎት ቤት ተገኝቼ በዓለም ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን እና በተለይም ደግሞ እዚህ የተገኛችሁ ምዕመናን ቤተሰቦችን፣ እንዲሁም አየርላንዳዊያንን በሙሉ ተወዳጅ ለሆነው ለማርያም አማላጅነት በአደራ አስረክብያለሁ። እናታችን ማርያም በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ የሚገኘውን ደስታ እና መከራ ታውቃለች። ንጹህ በሆነው ልቧ ሁሉን ነገሮቻችንን በፍቅር ወደ ልጇ ዙፋን ታቀርባለች።

ለዚህ ለእኔ ጉብኝት ማስታወሻ ይሆን ዘንድ በወርቅ የተሠራ መቁጠርያ ስጦታ አምጥቻለሁኝ። የመቁጠርያ ጸሎት በዚህ ሀገር ባህል ውስጥ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አውቃለሁ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተሳታፊ የሆነችበትን በብርሃን፣ በደስታ፣ በሕማማት እና በክብር የተሞሉ የክርስቶስን ምስጢሮችን በማሰላሰል ብዙ አባቶች፣ እናቶች እና ልጆች በየዓመቱ መጽናናትን እና ጥንካሬን አግኝተዋል።

ማርያም እናታችን የቤተ ክርስቲያንም እናት ናት፣ ዛሬ የዚህን ታማኝ የእግዚኣብሔር ሕዝብ ጉዞ ለእርሷ በአደራ እንሰጣለን። ቤተሰቦች የክርስቶስን መንግሥት ለማስፋፋትና ታናናሽ የሆኑ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ለመንከባከብ ያላቸው ቁርጠኝነት እንዲጨምር እንድትረዳን እርሷን እንጠይቃለን። በጊዜያችን ከሚነፍሱት ንፋሶች እና ማዕበል መካከል በሀገር ደረጃ ያላችሁን ምርጥ ልምዶች በመጠቀም እና በእነዚህ ልምዶች ላይ በመመስረት በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን ወንድና ሴት ክብር የሚያበላሹ እና እውነተኛ ያልሆኑ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ፍጻሜ ያማይመሩ ነገሮችን ማስወገድ ትችላላችሁ።

በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ልጇ ታቀርባቸዋለች። በአየርላንድ በቤተ ክርስቲያን ሰዎች አማካይነት በልጆች ላይ ተፈጽሞ የነበሩትን በደሎች ሁሉ በማርያም ሀውልት ሥር በመገኘት ለእርሷ አቅርቢያለሁ። ማናችንም ብንሆን በደል የደረሰባቸውን ሕጻናት የስቃይ ትዝታዎች ከማሰብ የምንባዝን ሳንሆን ይህ ታሪክ ያለተጋባ አሳዛኝ የሆነ ታሪክ የሁላችንንም ልብ የሚነካ ክስተት ነው። ይህ ግልጽ የሆነ መቅሰፍት ጽኑ እና ቆራጥ በመሆን ለእውነት እና ለፍትህ ፍለጋ እንድንሄድ ያደርገናል። ለእነዚህ ኃጢኣቶች የእግዚኣብሔርን ምህረት እየተማጸንኩኝ በተለይም ደግሞ የእግዚኣብሔር ሕዝቦች በሆኑ ቤተሰቦች ላይ የተፈጸመውን ከፍተኛ ክህደት እና መጥፎ የሆነ ተግባር እግዚኣብሔር ይቅር ይለን ዘንድ እጸልያለሁ። የዚህ ጥቃት ሰለባ የሆኑትን ሰዎች ሁሉ ከደረሰባቸው መጥፎ ጠባሳ ይፈወሱ ዘንድ እና እንዲህ ዓይነቱ ተግባር በድጋሚ የእግዚኣብሔር ሕዝብ በሆኑ ቤተሰቦች ላይ እንዳይፈጸም ሁሉም ዘብ ይቆም ዘንድ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በአደራ አቀርባለው።

በዚህ በኖክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቀደስ የነበረኝ ቆይታ ተወዳጁን የሰሜን አየርላንድ ሕዝብ እንድገናኝ አጋጣሚውን ፈጥሩዋል። ለዚህ ዓለማቀፍ የቤተሰብ ቀን በተዘጋጀው ሐዋርያዊ ጉብኝቴ ሰሜን አየርላንድን የጠቃለለ እንዳልነበረ በሚገባ ባውቅም ለእናንተ ያለችን ፍቅር እና በጸሎት ከእናንተ ጋር መሆኔን ግን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ሁሉም በአየርላንድ የሚገኙ የቤተሰብ አባላት በእርቅ መንፈስ እንደ ወንድም እና እንደ እህት ሆነው ወደ ፊት እንዲጓዙ ለእቤታችን ጸሎቴን አቀርባለሁ። ለነበረን ከፍተኛ ኅበረት እና መቀራረባችን በመሻሻሉ፣ እንዲሁም በክርስቲያን ማኅበርሰብ ውስጥ የሚታየው አብሮ የመሥራት በሕል እየጨመረ በመሄዱ ይህ ነገር ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ሁሉም የክርስቶስ ደቀ-መዛሙርት በቋሚነት፣ ቀጣይነት ባለው መልኩ፣ በብርታት ለሰላም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ኅበረት ያለው አንድ ማኅበረሰብ ይፈጠር ዘንድ ብርታቱን እንዲሰጠን ጸሎቴን ወደ እግዚኣብሔር አቀርባለሁ።

አሁን በዚህ ሐሳብ እና በልባችንም ውስጥ ሳይቀር ያሉትን ሐሳቦች የብስራተ ገብርኤል ጸሎት በማድረግ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናቅርብ።

27 August 2018, 08:48