ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ፡ ክርስቶስ ሁላችንንም እንደ ወደደን በቤተሰብ ውስጥ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ!

በዚህ የዓለም የቤተሰብ ቀን መደምደሚያ ላይ እንደ አንድ ቤተሰብ በመሆን በጌታ መዕድ ፊት ተሰብስበናል። በቤተሰቦቻችን ውስጥ ለተቀበልነው ብዙ በረከቶች/ጸጋዎች/ ጌታን እናመሰግነዋለን።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት  ፍራንቸስኮስ በአየርላንድ ዋና ከተማ በደብሊን በአሁኑ ወቅት እያደርጉ የሚገኙትን 24ኛውን ዓለማቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝ በዛሬው ቀን ማለትም በነሐሴ 20/2010 ዓ.ም እንደ ሚያጠናቅቁ ይታወቃል። ቅዱስነታቸው ይህንን 24ኛውን ዓለማቀፍ ሐዋሪያዊ ጉብኝታቸውን በአየርላንድ ዋና ከተማ በደብሊን ያደርጉት በተመሳሳይ ጊዜ ከባለፈው ከነሐሴ 15/2010 ዓ.ም ጀምሮ በደብሊን ሲካሄድ በነበረው 9ኛው ዓለማቀፍ የቤተሰብ ቀን ላይ ለመሳተፍ ሲሆን ቅዱስነታቸው በትላንትናው እለት ማለትም በነሐሴ 19/2010 ዓ.ም ወደ እዚያው አቅንተው በትላንትናው ምሽት በርካታ ምዕመናን እና በተገኙበት በደብሊን በሚገኘው በክሮክ ስታዲዬም የቤተሰብ በዓለ ከ500 ሺ በላይ ምዕመናን በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በደብሊን የሚያደርጉት 24ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት ዛሬ (ነሐሴ 20/2010 ዓ.ም) አመሻሹ ላይ እንደ ሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ሲሆን ቅዱስነታቸው ይህንን 24ኛውን ዓለማቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እና ከባለፈው ከነሐሴ 15-20/2010 ዓ.ም ድረስ ሲካሄድ የነበረው 9ኛው ዓለማቀፍ የቤተሰብ ቀን በይፋ ከመጠናቀቃቸው በፊት በአየርላንድ ዋና ከተማ በደብሊን ፎኒክስ ፓርክ ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ በጊዜያዊነት በተሰራው መንበረ ታቦት ላይ 500 ሺ ምዕመናን በተገኙበት ቅዱስነታቸው መስዋዕተ ቅዳሴን አሳርገዋል።

ቅዱስነታቸው በውቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙት ስብከት በዕለቱ በላቲን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት በተነበበው “ጌታ ሆይ ወደ የት እንሄዳለን፣ አንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል ነህና” (ዮሐ. 6፡68) በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ አስተንትኖ አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው ዕለት (በነሐሴ 20/2010 ዓ.ም) በደብሊን በሚገኘው ፎኒክስ ፓርክ ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ በጊዜያዊነት በተሰራው መንበረ ታቦት ላይ 500 ሺ ምዕመናን በተገኙበት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ቅዱስነታቸው ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል አብራችሁን በመሆን እንድተከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

“አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህና!” (ዮሐ 6፡68)

በዚህ የዓለም የቤተሰብ ቀን መደምደሚያ ላይ እንደ አንድ ቤተሰብ በመሆን በጌታ መዕድ ፊት ተሰብስበናል። በቤተሰቦቻችን ውስጥ ለተቀበልነው ብዙ በረከቶች/ጸጋዎች/ ጌታን እናመሰግነዋለን። የሕጻኑ ኢየሱስ ማኅበር አባል የነበረችው ቅድስት ትሬዛ ልብ በሚነካ ቃላት “ፍቅር የቤተ ክርስቲያን ልብ ነው” እንዳለችው እኛም በዚህ መሰረት ምልኣት ባለው መልኩ የሕይወት ጥሪያችንን ለመኖር ለመትጋት እንፈልጋለን።

በዚህ በጣም አስደሳች በነበረው እርስ በእርሳችን እና ከጌታ ጋር የነበረን ኅበረት አንድ ጊዜ ቆም ብለን ብናስብ እነዚህ የተቀበልናቸው መልካም የሆኑ ነገሮች ሁሉ ምንጭ ምን እንደ ሆነ መጠየቅና ማገናዘብ ይኖርብናል። ኢየሱስ ዛሬ በተነበበልን ቅዱስ ወንጌል ውስጥ ለደቀ-መዛሙርቱ በተናገረው ቃል የዚህ ጸጋ ምንጭ ምን እንደ ሆነ ይገልጽልናል። ብዙዎቹ በእርሱ ቃላት ተቆጭተዋል፣ ግራ ከመጋባታቸው አልፎ ተርፎም ተበሳጭተዋል፣ ከዚህ ዓለም ጥበብ በተቃራኒ ጎራ የሆነውን የእርሱን “ጠንካራ የሆኑ ቃላት” ለመቀበል ወይም ላለመቀበል ሲከራከሩ እናያለን። ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄያቸው “እኔ የነገርኩዋችሁ ቃል መንፈስ እና እውነት ነው” (ዮሐ. 6፡63) በማለት በቀጥታ ይመልስላቸዋል።

እነዚህ ቃላት ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታቸው ኢየሱስ በገባልን ቃል ኪዳን መሰረት በእምነት አማካይነት ሕይወታችንን ይሞሉታል። በእነዚህ ቀናት ውስጥ የተቀበልናቸው እና የተለማመድናቸው መልካም ነገሮች ሁሉ የመነጩት በዓለም ውስጥ አዲስ ህይወት፣ በልባችን ውስጥ፣ በቤተሰብ ውስጥ፣ በቤታችን ውስጥ እና በየቁምስናችን ውስጥ በአዲስ መልክ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ከሚነፍሰው ከእግዚአብሔር መንፈስ ነው። በእየቀኑ በየቤተሰባችን ውስጥ የሚከሰቱ አዳዲስ ቀናት፣ በዕየለቱ የሚከሰቱ አዳዲስ ፍጥረቶች በራሳቸው አዲስ የጴንጤቆስጤ ተስፋን ያመጡልናል፣ በኛው በአከባቢያችን የሚከሰት የጴንጤቆስጤ ልምድ ይሆናል ይህም ኢየሱስ ጠበቃችን፣ አጽናኛችን እና በእውነት ብርታትን የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስን እላክላችኋለው ባለው መሰረት ነው።

ዓለማችን ይህ የእግዚአብሔር የማበረታቻ እና የተስፋ ቃል ነው በጣም ያስፈልጋታል! ይህንን ዓለማቀፍ የቤተሰብ ቀን በመካፈላችን የተነሳ ብዙ የብዙ መልካም ፍሬዎች ተካፋዮች እንደ መሆናችን መጠን ወደ እየቤታችንሁ ተመልሳችሁ በምትሄዱበት ወቅት ሌሎችን በማበረታታት የእርሱ ኢየሱስ ክርቶስ “የዘላለም ሕይወት ቃል" ተካፋይ ይሆኑ ዘንድ ማበረታታት ያስፈልጋል።

ዛሬ በተነበበልን ሁለተኛው ምንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ሚገልጸው ጋብቻ ክርስቶስ እና ቤተ ክርስቲያን ለዘለዓለም የፈጸሙት ቃል ኪዳን ምስጢር ወስጥ መግባት ማለት ነው (ኤፌ 5፡32)። ይሁን እንጂ ይህ የማስተማሪያ ቃል አስደናቂ ቢሆንም ለአንዳንድ ሰዎች ግን "እንደ አንድ ጠንካራ የሆነ ቃል" ሆኖ ሊታይ ይችላል። ምክንያቱም ክርስቶስ እኛን እንደ ወደደን እኛም በፍቅር ውስጥ ሆነን መኖር እርሱ ራሱን የሰዋልንን መስዋዕት በማሰብ በዚሁ አግባብ ውስጥ ሆነን መኖር ይገባናል፣ ዘለዓለማዊ ፍቅር በድጋሚ ለመወለድ በውስጣችን ሞተን መነሳት እንደ ሚኖርብን በዚህም አገባብ መኖር እንዳለብን ያስተምረናል። አሁን ባለንበት ዓለማችን ውስጥ ከሚታዩ የኃጢኣት ባርነት፣ ራስ ወዳድነት፣ ቅናት እና የግድዬለሽነት መንፈስ ውስጥ መውጣት የምንችለው በዚህ ዓይነት ፍቅር ብቻ ነው። ይህ በኢየሱስ ክርስቶስ የምናውቀው ፍቅር ነው።

እነዚህ ነገሮች በምልኣት የመመስከር ሥራ ግን ቀላል አይደለም። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖች እያጋጠማቸው ያለው ፈተና በራሱ የመጀመሪያዎቹ አየርላንዳዊ ሚስዮናዊያን ካጋጠሟቸው አደጋዎች ሁሉ በጣም ያነሱ ናቸው። ቅዱስ ኮሎንቦስ እና ተከታዮቹ የወንጌልን ብርሃን ወደ አውሮፓ ሀገሮች በማምጣታቸው የጨለማን ዘመን እና የጠፋውን ባሕል መልሶ እንዲቆጠቁጥ አድርጉዋል። የእነሱ እጅግ ትልቅ የሆነ ሚስዮናዊ ስኬት የተገኘው በትክክለኛ ዘዴዎች ወይም ስልታዊ እቅዶች ላይ ተመኩዘው ባከናወኑት ተግባር ሳይሆን፣ ነገር ግን ትሁት እና ነጻ በሆነ መልኩ በእግዚኣብሔር መንፈስ በመነሳሳት ነው። ለክርስቶስ ታማኝ መሆናቸውን በየቀኑ የሚያረጋግጡበት ምስክርነታቸውን የገለፁትና የአውሮፓ ባህል እንዲዳብር አስተዋጾ ያደረጉት በምስጋና መንፈስ እና የሰውን ልብ በማነሳሳት ብቻ ነበር። ይህ ምስክር ለአማኞች እና ለቅዱሱ የእግዚአብሔር ሕዝቦች መንፈሳዊ እና ሚስዮናዊ እድሳት ምንጭ በመሆን ለብዙ ጊዜ አገልግሉዋል።

ይሁን እንጂ ለራሳችን ታማኞች ከሆንን የኢየሱስ ትምህርቶች አስቸጋሪ እንደሚሆኑ በትህትና አምነን እንቀበላለን። እኛን የበደሉንን ሰዎች ይቅር ማለት ሁልጊዜ ምንኛ ከባድ ነው! የእኛ የሁል ጊዜ ትልቁ ፈተና የሚሆነው ስደተኞችን እና መጤዎችን መቀበል ነው! የተፈጸሙትን አሳዛኝ ሁኔታዎች መቃወም ወይም ክህደት መፈጸም ምንኛ የሚያሳዝን ነገር ነው! ለጥቃት የተገለጡ ሰዎችን፣ ገና በማህጸን ውስጥ ያሉ ያልተወለዱ ሕጻናትን ወይም አረጋዊያንን መብት ማስጠበቅ የእኛን የነፃነት ስሜት የሚረብሽ ነገር መስሎ ይሰማናል።

ከሁሉም በላይ ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለምንገኝ ለእኛ ጌታ “እናንተም ለመሄድ ትፈልጋላችሁ ወይ?” (ዮሐ. 6፡67) በማለት ይጠይቀናል። ሁልጊዜ ከሚያበረታታን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እና ሁል ጊዜ ከጎናችን ከሚገኘው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመሆን “እኛ አንተ የእግዚኣብሔር ቅዱስ ልጅ እንደ ሆንክ አምነን ተቀብለናል” (ዮሐ 6፡69) በማለት ለመመለስ እንችላለን። እንዲሁም ከእስራኤል ሕዝቦች ጋር በጋራ በመሆን “እኛም ጌታን እናገለግላለን፣ ምክንያቱም እርሱ አማላካችን ነውና” (ኦዘ. 24፡18) ማለት ይጠበቅብናል።

27 August 2018, 08:40