Viaggio Apostolico in Irlanda - IX Incontro Mondiale delle Famiglie a Dublino 2018.08.25 Viaggio Apostolico in Irlanda - IX Incontro Mondiale delle Famiglie a Dublino 2018.08.25 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የቤተሰብን ቀን ከዓለም ዙሪያ ከመጡት ቤተሰቦች ጋር ሆነው አከበሩ።

በዳብሊን ኮርክ ስታዲየም ውስጥ፣ ቁጥራቸው ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑ ምዕመናን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በደስታ ተቀብለዋቸዋል፤ ቅዱስነታቸውም ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው በስፍራው ከተሰበሰበው ሕዝብ ጋር መሆናቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ፣ ለከሰዓት በኋላ በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሠረት በዳብሊን ከተማ ውስጥ በሚገኘው በኮርክ ስታዲየም፣ ቁጥራቸው ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑ ምዕመናን ላደረጉላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው በስፍራው ከተሰበሰበው ሕዝብ ጋር በመሆናቸው የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ ገልጸዋል። በመቀጠልም በጋራ መጸለይ ስብዕናችንና ክርስቲያንነታችን ጎልቶ እንዲታይ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር አውቀን ከሌሎች ጋር በደስታ እንድንካፈል በማድረግ፣ በዕለታዊ ጉዞአችንም ደግፎን ወደ ራሱ ይጠራናል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 24ኛቸው የሆነውን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ቅዳሜ ዕለት ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ. ም. ወደ አይርላንድ መጓዛቸው ይታወቃል። ቅዱስነታቸው ወደ ዳብሊን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ከመንግሥት ባለስልጣናትና ከሃይማኖት መሪዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ከዚህ በመቀጠልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዳብሊን ቤተ መንግሥት ተገኝተው ለአይርላንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት እና ለዲፕሎማቲክ አካላት ንግግር ማድረጋቸው የታወቀ ሲሆን ወደ አይርላንድ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ ግብዣን ላቀረበው፣ በመንግሥት ምክር ቤት የባሕልና ሃይማኖት ሚኒስቴር ልባዊ ምስጋናቸውን ማቅረባቸው ታውቋል።

እያንዳንዱ የቤተሰብ በዓል፣ የቤተሰብ አባላትን ከሩቅ ቦታ ጠርቶ እንደሚያሰበስብ ሁሉ፣ ዛሬ በአይርላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን የተሰበሰብንበት ዋና ዓላማም በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ቤተሰብ በመሆናችን ለዚህ ያበቃንን እግዚአብሔር በዓል በማዘጋጀት ለማመስገን ነው ብለዋል። ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ልጆች ቤተሰብ ናት። የአንድ ቤተሰብ ልጆች በመሆናችን ከሚደሰቱት ጋር እንደሰታለን፣ ከሚያለቅሱትም ጋር እናለቅሳለን። ለእያንዳንዳችን ከሚጨነቅልን ቤተሰብ መካከል እንገኛለን። ምክንያቱም እግዚአብሔር አባታችን በምስጢረ ጥምቀት ልጆቹ አድርጎናልና። ሕጻናት ሲወለዱ ምስጢረ ጥምቀትን እንዲቀበሉ የምናደርግበት ምክንያት በትልቁ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ቶሎ ብለው አባል እንዲሆኑ ለማድረግ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱን ሰው ወደዚህ የደስታ በዓል መጋበዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

ቤተሰብ ትልቁ የእግዚአብሔር ሕዝብ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለ ቤተሰብ ቤተክርስቲያን ምን ልትሆን ትችል ነበር ብለው ብዙ ችግሮች ቢያጋጥሙትም ቤተሰብ እጅግ አስፈላጊነት መሆኑን ለማስገንዘብ በማለት “ከፍቅር የሚገኝ ደስታ” የተሰኘውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ልኬላችኋለሁን ብለዋል። በአይርላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን ለተደረገው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ መሪ ቃል “የቤተሰብ ወንጌል ለዓለም ደስታ ነው።” የሚል እንዲሆን ፈልጌአለሁ ብለዋል። የእግዚአብሔር ፈቃድ እያንዳንዱ ቤተሰብ የፍቅር ደስታን ለዓለም እንዲበራ የሚያደርግ መሆን አለበት። ይህም ማለት እኛ የእግዚአብሔር ፍቅር የተቀበልን፣ በዕለታዊ ኑሮአችን በኩል በቃልም ሆነ በሥራ ለሌሎች እንዲታይ ማድረግ ያስፈልጋል። ቅድስና ማለትም ይህ ነው። ስለ ቅዱሳን ማውራት እወዳለሁ። ምክንያቱም እነዚያ ሰዎች የእግዚአብሔርን አለኝታነት በዕለታዊ ኑሮአቸው መካከል ሳያቋርጡ ስለሚያስታውሱት ነው። የፍቅርና የቅድስና ጥሪ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተዘጋጀ አይደለም። በእውነት የሚመለከት ዓይን ካለን የፍቅርና የቅድስና ጥሪ ከአጠገባችብ መሆኑን እንረዳለን። ለሌሎች ፍቅርን፣ ምሕረትንና ይቅርታን በሚያደርጉ ቤተሰቦች ልብ ውስጥ እንዳለ እንገነዘባለን። ከቤተሰብ የሚመነጭ መልካም ዜና በእውነት የዓለም ደስታ ነው። ከቤተሰቦቻችን ከሚመነጭ መልካም ዜና ውስጥ፣ በናዝሬት ከቅዱስ ቤተሰብ ጋር የኖረው ኢየሱስ ክርስቶስ ይገኝበታል።

ክርስቲያናዊ ጋብቻ እና የቤተሰብ ሕይወት አንድ ላይ በመሆን በአምሳሉ በፈጠረን በእግዚአብሔር ፍቅር በመታገዝ፣ ለፍቅሩንና ለቅድስናው ምስጋናን ለማቅረብ እንድንችል ያደርገናል። የቤተሰብ አባላት በሙሉ ከቤታቸው የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲቀበሉ ተጠርተዋል። የእግዚአብሔር ጸጋም በየቀኑ በአንድ ልብ እንዲንኖር ያግዘናል። ከእግዚአብሔር ልብ የሚፈልቅ የጸጋ ሃብት ከቁስሎቻችን በመዳን፣ አእምሮአችንንና ልባችንን ከፍተን፣ እርስ በርስ እንድንደማመጥ፣ እንድንስማማና ይቅር እንድንባባል ያደርገናል ብለዋል።

የቡርኪና ፋሶ ተወላጅ የሆኑት ፈለሲቴ፣ ከይስሐቅ እና ጊስሌን የሰጡትን የሕይወት ምስክርነት አዳምጠናል። በቤተሰብ መካከል የተደረገውን ይቅርታ አስመልክተው ማራኪ የሆነ ታሪክ ነግረውናል። ገጣሚው  “ስህተት ከሰው ነው፣ ምሕረትም ከእግዚአብሔር ነው” እንዳለው በእርግጥም ምሕረትን ማድረግ ከእግዚአብሔር የተሰጠን፣ ቁስሎቻችንን የሚፈውስ፣ ወደ እግዚአብሔር ወደ ሰዎች እንድንቀርብ የሚያደርገን ልዩ ስጦታ ነው። በቤተሰብ መካከል አንዱ ሌላውን ይቅርታ መጠየቅ፣ ምስጋናን መስጠት አስፈላጊ ነው። ሙሉ በሙሉ ትክክለኛ የሆነ ቤተሰብ የለም። ያለ ይቅርታና ያለ ምስጋና የሚኖር ቤተሰብ ቀስ በቀስ ይፈርሳል ብለዋል።

ለበደሉን ይቅርታ ማድረግ ማለት ራሳችንን አሳልፈን መስጠት ማለት ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ፣ ኢየሱስ ዘወትር ይቅር ይለናል፤ ከእርሱ በምናገኘው ሃይል በመታገዝ፣ ፍላጎቱ ካለን እኛም ሌሎችን ይቅር ማለት እንችላለን። “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ውስጥ እንደሚገኘው የምሕረት ጥያቄ ሳይሆን ሕጻናት ስለ ምሕረት የሚማሩት ወላጆች እርስ በርስ ይቅርታን ሲደራረጉ በመመልከት ነው። ይህንን የምንገነዘብ ከሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ስላስተማረንና በጋብቻ መካከል ሊኖር ስለሚገባው የታማኝነት ምስጢር አስፈላጊነትን እንገነዘባለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ለበደላችን በመሞት ምሳሌ የሆነልን እኛም ሌሎችን ይቅር እንድንልና ከሌሎች ጋር ይቅር እንድንባባል ነው። እንደ ቤተሰብም እንደ ግል ሰውም እውነቱን መማር ይኖርብናል፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ መልዕክቱ፣  “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል።” (1ኛ ቆሮ.13,8)።

ቅዱስነታቸው በቤተሰብ ውስጥ የማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ ከሕንድ የመጡት ቤተሰብ፣ ኒሻንና ቴድ ልጆቻቸውን በማሕበራዊ ሚዲያ በኩል ለማስተማር የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀው እነዚህ ወላጆች ማሕበራዊ ሚዲያን በመጥፎ መመልከት ሳይሆን በሰዎች መካከል ጓደኝነትንና አንድነትን በመፍጠር የመልካምነት መገለጭእቸውን እንድንገነዝብ አድረገውናል ብለዋል። ማሕበራዊ መገናኛዎች በአግባቡና በጥንቃቄ የተጠቀምናቸው ከሆነ ለቤተሰብ መቀራረብና ማሕበራዊ እድገት ጠቃሚ ሊሆኑ እንደምችሉ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል፣ በቤተሰብ ውስጥ የሚገኝ ፍቅርና እምነት፣ በጦርነት ምክንያት ለሚመጣ አመጽና ጥፋት የሰላምና የብርታት ምንጭ በመሆን ሊያገለግል እንደሚችል ገልጸው፣ የጦርነት ሰለባ የሆኑ በርካታ ቤተሰቦች በየዕለቱ የሚያጋጥማቸውን ስቃይ፣ መኖሪያ ቤታቸውንም ለቅቀው እስከመሰደድ እንደሚደርሱ አስታውሰዋል። ነገር ግን በቤተሰብ መካከል በሚደረግ ፍቅርና እገዛ አማካይነት በአደጋ ላይ የወደቀውን ቤተሰብ ኑሮ በማቃናት፣ መልሶ መገንባት እንደሚቻል አስረድተዋል። በማንኛውም ሕብረተሰብ መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ በማርገብ፣ ሰላምን በመፍጠር፣ ፍቅርን በማስተማርና ይቅርታ በማድረግ፣ ሕብረተሰብ ሊጎዳ ከሚችል ከጥላቻ መንገድ ለመውጣት ቤተሰብ ትልቅ አስተዋጽዖን ሊያበረክት ይችላል ብለዋል።                                  

26 August 2018, 13:58