ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “በአይርላንድ ከጾታዊ ጥቃት ቁስሎች ይልቅ እምነት የበለጠ ጠንካራ ነው”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አይርላንድ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ትናንት እሁድ፣ ባገሩ የሰዓት አቆጣጠር 1 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ላይ ከዳብሊን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተው ወደ ሮም ባገሩ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ መድረሳቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በበረራ ላይ ሆነው ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸውም የታወቀ ሲሆን በመግለጫቸው፣ የአይርላንድ ሕዝብ ለእምነቱ ያለውን ጽናት አድንቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአይርላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን ከነሐሴ 15 እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ. ም. በተካሄደው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን ላይ ለመገኘት ወደ አይርላንድ ያደረጉትን የሁለት ቀን ሐዋሪያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ቅድስት መንበራቸው ሲመለሱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው እንደገለጹት በአይርላንድ ሕዝብ ውስጥ ጠንካራ የእምነት ጽናት እንዳለ ተረድቼአለሁ ብለዋል። የአይርላንድ ሕዝብ ለእምነቱ እንቅፋት የሚሆኑ ብዙ አሳዝኝ ክስተቶችን ያሳለፈ ቢሆንም እውነቱ የቱጋ እንደሆነ ለይቶ ማወቅ ይችላል ብለዋል። ሕዝቡ ላይ የደረሰውን በደል ለመለየት በሚደረገው ጥረት፣ ለእምነቱ እንቅፋት ሆነው የቆዩ ችግሮች እየታወቁ መምጣታቸውን ገልጸው በእነዚህ እንቅፋቶች መካከልም የአይርላንድ ሕዝብ በእምነቱ ምን ጊዜም ጠንካራ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

ምንም አስተያየት የለኝም፣

በአይርላንድ ሕዝብ መካከል ከቤተ ክሕነት በኩል የተፈጸሙትን ወሲባዊ ጥቃቶች በማስመልከት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልስ ሰጥተውባቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአይርላንድ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በሁለተኛ ቀናቸው፣ በሰሜን አሜርካ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ልኡክ የነበሩ ሊቀ ጳጳሳት ካርሎ ማርያ ቪጋኖ እንደተናገሩት፣ የዋሽንግተን ሊቀ ጳጳሳት የነበሩት ካርዲናል ማክ ካሪክ በዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ላይ ፆታዊ ትንኮሳን ፈጽመዋል የተባለውን በተመለከተ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት፣ ከዚህ በፊት ጉዳዩን በማስመልከት ይፋ የተደረገ ሰነድ መኖሩ አስታውሰው፣ ጋዜጠኞቹ ይህን ሰነድ በጥንቃቄ ካነበቡት በኋላ ፍርድ ይስጡበት ብለዋል።

ለእያንዳንዱ የክስ ጉዳይ ችሎት ይኑረው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሌሎች ጉዳዮችም ለምሳሌ አንድ ጳጳስ ክስ ቢመሠረትባቸው ወደ ሕግ ዘንድ የማቅረቡን ሂደት በማስመልከት መወሰድ ስላለበት እርምጃ ገለጻ ሰጥተውበታል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ራሳቸው ባቋቋሙት የወሲባዊ ጥቃት ጉዳይ አጣሪ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ውስጥ አባል የነበሩ፣ የጥቃቱም ሰለባ የሆኑ ማሪ ኮሊንስን ጉዳይ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ፣ በእርሳቸው የግል ትዕዛዝ መሠረት እነዚህን ጉዳዮች የሚያጣራ ልዩ ችሎት እንደተቋቋመ ገልጸው በርካታ ወሲባዊ ጥቃቶችን የሚያጣራ አንድ ብቸኛ ችሎት ከመመስረት ይልቅ ለእያንዳንዱ ክስ የራሱ ችሎት ቢኖር መልካም እንደሚሆን መወሰናቸውንም ገልጸዋል። በዚህ መሠረት ውጤታማ ሥራ እንደሚከናወን ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት ቀርቦ የሚገኘውን፣ በኒዮርክ ሀገረ ስብከት የጓም ሊቀ ጳጳስ አንቶኒ ሳብላን አፑሮን አስታውሰዋል።

ወሲባዊ ጥቃቶችን ቶሎ ብሎ ማሳወቅ አስፈላጊ ሆኖ ሳለ በፍርድ አሰጣጥ ላይ ግን ጥንቃቄ ይደረግበት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ “የእግዚአብሔር ሕዝብ” በማለት ለመላው ዓለም ምዕመናን በላኩት ደብዳቤ የገለጹትን መልዕክት መሠረት በማድረግ በሰጡት መልስ፣ ከካህናት በኩል በልጆች ወይም በማንኛውም ምዕመናን ወገን ጾታዊ ጥቃት ቢፈጸም በድፍረት ቶሎ ብሎ መናገር እንደሚያስፈልግ አሳስበው ብዙን ጊዜ ወላጆች የልጆቻቸውን ብሶት አለማዳመጥ ትክክል እንዳልሆነ አስረድተዋል። ከዚህም ጋር አያያዘው አንድ ጉዳይ እውነት ወይም ሐሰት መሆኑ ሳይረጋገጥ ወደ አደባባይ ላይ ማውጣትም ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ይህን በተመለከተ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለ ምንም ጥፋት ተከስሰው ወደ ፍርድ ዘንድ የሚቀርቡ ካህናት እንዳሉና ጉዳያቸው ሲጣራ ነጻ ሆነው እንደሚወጡ አስረድተዋል። ይህን ካሉ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ምክራቸው የጋዜጠኝነት ሥራ የዋዛ አለመሆኑን በመገንዘብ ከሁሉ አስቀድሞ የሚያቀርቡት መረጃ እውነትነት ያለውና ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

የልጆቹን ብሶት የማያዳምጥ ወላጅ እውነተኛ ወላጅ አይደለም፣

የአየርላንድ ሴት መነኩሴዎች፣ በወላጅ አልባ ሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ፈጽመዋል የተባለውን ድርጊት በማስመልከት የአይርላንድ ሚኒስትር የተናገሩትን በጽሞና ያዳመጡት ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ፣ ጉዳዩ ወደ ሕግ ዘንድ ቀርቦ እየተጣራ መሆኑን ገልጸው፣ በማጣራት ሂደት ውስጥ የቤተክርስቲያን ሃላፊዎች እጅ ይኑር አይኑር ማረጋገጫ እየተፈለገ መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ሚኒስትሯ ያቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሚዛናዊነት ያላቸውና ወቅታዊም በመሆናቸው አድናቆትን ችረውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሯ በመጨረሻም፣ ልጆች ለወላጆቻቸው፣ ግብረሰዶማዊ መሆናቸውን ቢገልጹ የወላጅ ምላሽ ምን መሆን አለበት ብለው ላቀረቡላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ወላጅ አባት ወይም ወላጅ እናት ለልጆቻቸው መጸለይ እንደሚያስፈልግ፣ ከመኮነን ይልቅ መወያየት፣ ለጉዳዩ ጊዜን ሰጥተው በመነጋገር ለመረዳት መሞከር ያስፈልጋል ብለው ይህን ከማድረግ ችላ ያሉ እንደሆነ ግን የወላጅነትን ሃላፊነት አልተወጡም ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ያነሱት ሌላው ጉዳይ ቢኖር ስደተኞችን የሚመለከት ሲሆን በቅርቡ ስደተኞችን የጫነ አንድ መርከብ ከአሥር ቀን የባሕር ላይ ቆይታ በኋላ ስደተኞችን በኢጣሊያ ግዛት ወደ ሆነችው ወደ ሜሲና ከተማ እንዲደርስ ስለመደረጉ ሲናገሩ፣ የስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ አንድ አገር በጥንቃቄ የተረቀቀ ሕግ ሊኖረው ይገባል ብለው ስደተኞች በደረሱበት አገር ውስጥ ከማሕበረሰቡ ባሕልና ወግ ጋር የጠበቀ ግንኙነትን መፍጠር እንደኣሚያስፈልግ አሳስስበው፣ ከአሥር ቀን የባሕር ላይ ቆይታ ወደ ጣሊያን ግዛት ውስጥ እንዲገባ ለተደረገው መርከብና ለስደተኞች ለተደረገው አቀባበል የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ፋውንዴሽንና የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤን አመስግነዋል።

27 August 2018, 18:29