ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ላይ ለሚሰሩ ሰዎች ጸሎት አደረጉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ዛሬ ሚያዝያ 28/2012 ዓ.ም በሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በዚህ አሁን በምንገኝበት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው እውነታውን ለዓለም በመዘገብ ላይ ለሚገኙ በመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ላይ ለሚሰሩ ሰዎች እግዚአብሔር ብርታቱን እንዲሰጣቸው መጸለያቸው ተገልጿል።፡፡

የቫቲካን ዜና

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዕለቱ ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ የጀመሩት በመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ላይ ለሚሰሩ ሰዎች የሚከተለውን ጸሎት በማቅረብ ነበር . . .

በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ለሚሰሩ ወንዶችና ሴቶች ዛሬ እንጸልይ። በዚህ የወረርሽኝ ጊዜ ውስጥ ብዙ አደጋ እየተጋፈጡ ብዙ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛሉ። በዚህ እውነትን ለዓለም ለማሳወቅ በሚያከናውኑት ተግባር የእውነት ጌታ እንዲረዳቸው እንጸልይ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለቱ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያደረጉት ስብከት “ማንም በእኔ ቢያምን በእኔ ብቻ ሳይሆን በላከኝም ማመኑ ነው፤ እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። በእኔ የሚያምን በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። ቃሌን ሰምቶ በማይፈጽመው ላይ የምፈርደው እኔ አይደለሁም፤ ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ላይ ልፈርድ አልመጣሁምና። በማይቀበለኝና ቃሌን በሚያቃልል ላይ የሚፈርድበት አለ፤ የተናገርሁት ቃል ራሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል፤ ምክንያቱም እኔ ከራሴ አልተናገርሁም፤ ነገር ግን የላከኝ አብ ምን እንደምናገርና እንዴት እንደምናገር አዘዘኝ። የእርሱ ትእዛዝ ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚያደርስ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህም የምለው ሁሉ አብ እንድናገረው የነገረኝን ብቻ ነው” (ዮሐ 12፡44-50) በምለው የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር።  

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በእዚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተመርኩዘው ባደረጉት ስብከት እንደ ገለጹት “ይህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል በኢየሱስ እና በአባቱ መካከል የነበረውን የጠበቀ ግንኙነት ያሳየናል።  አብ እንዲያደርግ ያዘዘውን ነገር ሁሉ ኢየሱስ አደረገ። ተልዕኮውም ገልጽ ነበረ፣ ‘በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ’” ብሎ ተናግሮ እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው የኢየሱስ ተልዕኮ ለእኛ ብርሃን መስጠት ነው፣ እርሱ ራሱ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሎ መናገሩን አስታውሰዋል።

ነቢዩ ኢሳይያስ “በጨለማ የሚራመዱት ሰዎች ሁሉ ታላቅ ብርሃን እዩ” በማለት ስለእዚህ ብርሃን አስቀድሞ ተናግሯል ያሉት ቅዱስነታቸው  ይህ “ሰዎችን የምያበራ የብርሃን ተስፋ ነው፣ የሐዋርያትም ተልእኮ እንዲሁ ብርሃን መስጠት ነው ፣ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ እንደ ምናገረው እርሱ የተመረጠው ብርሃን ለመስጠት እንደ ሆነ በመግለጹ የተነሳ እኛም  የራሳችንን ሳይሆን ነገር ግን ብርሃን የሆነውን የእርሱን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ለሰዎች ለመስጠት ተጠርተናል” ብለዋል። ዓለም በጨለማ ውስጥ ስለሆነ የኢየሱስ እና የሐዋርያቱ ተልዕኮ ብርሃን መስጠት ነው ብለዋል።

ዮሐንስ በወንጌሉ የመጀመሪያ ክፍል ላይ ብርሃንን በተመለከተ እንደገለጸው ብርሃን ሆኖ ወደ ምድር የመጣው ኢየሱስ በወቅቱ ተቀባይ ማጣቱን መግለጹን ያስታወሱት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ወደ ራሱ ወገኖች መጣ፤ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፤ ከብራሃን ይልቅ ጨለማን ይወዱ ነበር” ብሎ ወንጌላዊው ዮሐንስ ተናግሮ እንደነበረ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። ከጨለማ ጋር ስለተዋወቁ እና በጨለማ ውስጥ ስለሚኖሩ “ብርሃንን ሊቀበሉ አይችሉም ፣ እነሱ የጨለማ ባሪያዎች ናቸው” ብለዋል። የኢየሱስ ትግል ይህ ነው፣ ብርሃን እንዲኖር ማድረግ፣ ነገሮች እንዴት እንደ ሆኑ መመልከት እንችል ዘንድ፣ ነጻነትን እና እውነትን ማግኘት እንችል ዘንድ ለማድረግ ኢየሱስ በትጋት እንደ ሚሰራ ቅዱስነታቸው የገለጹ ሲሆን ከኢየሱስ ጋር በምንሆንበት ወቅት ሁሉ ብርሃን በሕይወታችን ይሞላል ብለዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ጌታን ባገኘው ጊዜ ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚደረግ ሽግግር ልምድ እንዳገኘ የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እኛ ይህንን ብርሃን ምስጢረ ጥምቀት በተቀበልንበት ወቅት ብርሃን እንዳገኘን፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን እንደ ተሸጋገርን ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል። በእዚህ ምክንያት ምስጢረ ጥምቀት በመጀመሪያዎቹ ምዕተ-ዓመታት “ብርሃን” ተብሎ ይጠራ እንደ ነበረ የገለጹት ቅዱስነታቸው ምክንያቱም ብርሃን የሆነውን ኢየሱስ እንድንቀበል የምያደርገን ምስጢር በመሆኑ የተነሳ ነው ብለዋል።

“ከጨለማ ጋር በጣም ተለማምዶ መኖር አደገኛ ነው፣ በኃጢያታችን ውስጥ ገብተን መኖር በጨለማ እንደ መኖር ይቆጠራል፣ ኃጢአት ያጠፋናል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “እኛ የታመሙ ዓይኖች አሉን፣ በእዚህ ምክንያት ብርሃን መመልከት ይከብደናል፣ ይህንን በተመለከተ ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ በግልፅ ተናግሯል ‘ዓይንህ ታማሚ ከሆነ ሰውነትህ ሁሉ ይታመማል’” ብሎ መግለጹን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። "ዓይንህ ጨለማን ብቻ የሚመለከት ከሆነ፣ በውስጣቸው ስንት ጨለማ አለ?" በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “መለወጥ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገር ማለት ነው። ነገር ግን  የእምነት ዓይንን የሚያጎድፉና "የሚያሳውሩ ነገሮች ምንድናቸው? በማለት ጥያቄ ያነሱት ቅዱስነታቸው  “ምግባረ ብልሹነት ፣ ዓለማዊ መንፈስ ፣ እብሪተኝነት ” ናቸው ብለዋል።

እነዚህ ሦስት ነገሮች -አሉ  ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ “በጨለማ ውስጥ ሆነን እንድንኖር ያደርጉናል፣ ከእነዚ የጨለማ ሥራዎች ውስጥ መውጣት እንችል ዘንድ እንዲረዳን የጌታን ጸጋ መማጸን ይኖርብናል” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው የዕለቱን ስብከት አጠናቀዋል።

06 May 2020, 13:53
ሁሉንም ያንብቡ >