ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ሰይጣን ቤተክርስቲያንን ሊያጠቃት ቢሞክርም መንፈስ ቅዱስ ይጠብቃታል"።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ግንቦት 1/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ የቅዱስ ቪንሴንት ማህበር አባል የነበረችውን ቅድስት ሉዊዛ ደ ማሪላክን እና በቅድስት ማርታ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ቤት ውስጥ በልዩ ልዩ አገልግሎቶች የተሰማሩትን ሌሎች የቅዱስ ቪንሴንት ማህበር ደናግልን በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅድሱነታቸው ከዚህም በተጨማሪ በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት ባሰሙት ስብከታቸው፣ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያንን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳድጋት መሆኑን ገልጸው፣ ብሌላ ወገን ይህን እድገት ማየት የማይፈልግ ክፉ መንፈስ በቅንዓት ተነሳስቶ እድገቷን ሊያደናቅፍ የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። ክፉ መንፈስ ቤተክርስቲያንን ለማደናቀፍ የሚጠቀምበት መንገድም ዓለማዊ ሥልጣን እና ገንዘብ መሆናቸውን አስረድተዋል። ክርስቲያን ግን በኢየሱስ ክርስቶስ እና በመንፈስ ቅዱስ የሚተማመን መሆኑን አስረድተዋል።        

የቫቲካን ዜና

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በምትከተል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የብርሃነ ትንሳኤ መታሰቢያ በዓል በተከበረ በአራተኛ ሳምንት በዋለው በዛሬው ዕለት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መጀመሪያ ላይ የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር አባል የነበረችውን ቅድስት ሉዊዛ ዴ ማሪላክን አስታውሰው፣ በቫቲካን ውስጥ፣ በቅድስት ማርታ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ እና በቫቲካን ውስጥ ያለውን የሕፃናት የሕፃናት ሕክምና መስጫ ማዕከልን የሚያስተዳድሩ የማኅበሩ ደናግልን አስታውሰዋል። የቅድስት ሉዊዛ መታሰቢያ ዓመታዊ ክብረበዓል እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በመጋቢት 15 የሚከበር ቢሆንም የጾም ወር በመሆኑ ወደ ዛሬው ቀን መዛወሩ ታውቋል። በቫቲካን ውስጥ፣ በቅድስት ማርታ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ እና በቫቲካን ውስጥ ያለውን የሕፃናት የሕፃናት ሕክምና መስጫ ማዕከልን የሚያስተዳድሩ ደናግል፣ ቅድስት ሉዊዛ ዴ ማሪላክ የመሠረተችው የቸርነት ሥራ ልጆች ማኅበር ፣ ከመላው የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ቅድስት ሉዊዛን የሚያስታውስ የቅብ ሥዕል ለመታሰቢያነት መቅረቡ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በስብከታቸው፣ ዛሬ በቅድስት ሉዊዛ መታሰቢያ ዕለት በቫቲካን ውስጥ በቅድስት ማርታ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ እና በሕጻናት ሕክምና መስጫ ማዕከል ውስጥ ለመቶ ዓመታት ያህል አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ ለሚገኙት ደናግል እንጸልይ ብለው እግዚአብሔርን ይባርካችሁ በማለት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ከሐዋ. 13:44-52 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ንባብ ላይ በማተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በአንጾኪያ የሚኖሩ አይሁዳዊያን ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው ምስክርነት ብዙዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ወደ እርሱ መምጣታቸን አይሁዳውያን ባዩ ጊዜ በቅንዓት ተሞልተው፣ በጳውሎስ እና በበርናባስ ላይ መከራን እንዳደረሱባቸው፣ በዚህም የተነሳ አካባቢዉን ለቀው እንዲሄዱ መገደዳቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። በዚህ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቤተክርስቲያን እንዳታድግ፣ እዳትስፋፋ ቅንዓት ያደረበት ክፉ መንፈስ እንቅፋቶችን በመዘርጋት የሚያደናቅፋት መሆኑን አስታውሰው፣ በሌላ ወገን ቤተክርስቲያን ከጊዜ ወደ ጊዜ እንድታድግ መንፈስ ቅዱስ ዘወትር ብርታትን እና ኃይልን የሚጨምርላት መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ በርካታ ትግሎች መካሄዳቸውን፣ የሕይወት መስዋዕትነቶች የተከፈሉ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ቤተክርስቲያን በየእግዚአብሔር ቃል ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገትን ስታሳይ ስቃይ እና መከራ መኖሩ የግድ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ሰይጣን በቅንዓት በመነሳሳት ቤተክርስቲያንን ሊያጠፋት ዘወትር ይሞክራል ብለዋል። ቢሆንም ቤተክርስቲያን ከእግዚአብሔር ዘንድ በምታገኘው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል መጽናናትን በማግኘት፣ የዓለም መከራን በማለፍ ወደ ፊት የምትጓዝ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተው። ክፉ መንፈስ ቤተክርስቲያንን ለማጥቃት ከሚጠቀምባቸው የቅንዓት መሣሪያዎች አንዱ የእግዚአብሔርን ስልጣን የሚቃወም ጊዜያዊው የዓለም ስልጣን ነው ብለዋል። ከስልጣን በስተጀርባ ገንዘብ አለ ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እውነቱ እና የእግዚአብሔር ታላቅ ሃይል እስከ ትንሳኤው ጠዋት ተደብቆ እንዲቆይ የተደረገው በገንዘብ ኃይል ነው ብለዋል። የክርስቲያን ተስፋው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና መንፈስ ቅዱስ እንጂ የዚህ ዓለም ስልጣን እና የገንዘብ ኃይል አለመሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብከታቸው አስረድተዋል።              

09 May 2020, 10:04
ሁሉንም ያንብቡ >