ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣                ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ፖለቲከኞች እና ሳይንትስቶች ከገንዘብ ይልቅ ለሕዝብ ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቀረቡ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ ሚያዝያ 5/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል በሚደረግ ጥረት መካከል የመንግሥት መሪዎች እና የሳይንስ ጠበብት ለገንዘብ ሳይሆን ለሕዝባቸው ደህንነት እና እድገት ቅድሚያን በመስጠት ወረርሽኙ ያስከተላቸው በርካታ ቀውሶች የሚወገዱበትን መንገድ እንዲያገኙ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ቅዱስነታችው በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መጀመሪያ ላይ ባቀረቡት ሃሳብ፣ የመንግሥታት መሪዎች እና የሳይንሱ ማሕበረሰብ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ካስከተለው ቀውስ ለመውጣት ጥረት በተጀመረበት ባሁኑ ወቅት የሕዝባቸውን ጥቅም እና ዕድገት በማስቀደም ትክክለኛውን የመፍትሄ መንገድ እንዲያገኙ እንጸልይላቸው ብለዋል።   

ከማቴ. 28:8-15 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱን የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸዋን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፣ በዚህ የወንጌል ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሳኤው በኋላ ለተገለጠላችው አንዳንድ ሴቶች “አትፍሩ! ወደ ገሊላ ሄዱ እና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው፤ የሚያዩኝም በዚያ ነው” በማለት ማሳሰቡን አስታውሰዋል። በዚህን ጊዜ የካህናት አለቆች እና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ከተማከሩ በኋላ ለወታደሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥቶአቸው “እኛ ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት ብላችሁ ለሕዝቡ ንገሩ” ማለታቸውን አስታውሰው፣ የዕለቱ ወንጌል ሁለት ምርጫዎችን እንደሚያስቀምጥ እነርሱም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ ተስፋ እና የመካነ መቃብር ናፍቆት መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዛሬ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል የሰው ልጅ በየዕለቱ ሊያደርጋቸው የሚመኛቸውን ምርጫዎች እንደሚናገር የገለጹት ቅዱስነታቸው ምርጫዎቹም ደስታ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ ተስፋ እና የመካነ መቃብር ናፍቆት ናቸው ብለዋል። የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤን ቀድመው በመሄድ ያውጁት ሴቶች ናቸው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ በሴቶች በኩል እንደሚጀምር፣ ሴቶችም ያወቁትን፣ ያዩትን እና በእጆቻቸው የዳሰሱትን ያለ ጥርጥር መመስከራቸውን አስረድተው መቃብሩ ባዶ መሆኑንም በዓይናቸው ተመልክተዋል ብለዋል። ሴቶቹ በነገሯቸው መልካም ዜና ላይ ጥርጣሬ ያደረባቸው ደቀ መዛሙርት ቶሎ ብለው ለማመን ቢቸገሩም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ትንሳኤ እስከ ዛሬ ጸንቶ እንዲኖር እና ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ በመከከላችን መገኘቱን እውን ያደረጉት ሴቶች መሆናቸውን አስረድተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ባዶ የቀረው መቃብር ማመን የማይፈልጉ ሰዎች እውነቱን እንዲዘነጉ በማድረግ ሃያሉን እግዚአብሔር ከማገልገል ይልቅ ለገንዘብ እንዲገዙ ያደርጋቸውል ብለዋል።             

ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ. 6:24 ላይ አንድ ሰው የሁለት ጌታ አገልጋይ ሊሆን አይችልም፤ አንዱን ይጠላል ሌላውን ይወዳል፤ አንዱን ያከብራል ሌላውን ይንቃል ፤ እንዲሁም የገንዘብ ተገዥ የሆነ ሰው የእግዚአብሔር አገልጋይ መሆን ከቶ አይችልም ተብሎ የተጻፈውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካህናት አለቆች እና የሙሴ ሕግ መምህራን አቋማቸውን ለመግለጽ የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ እውነት ከመመስከር ይልቅ ገንዘብ ለመክፈል በመስማማት ዝምታን እንደመረጡ እና ይህም ግልጽ ሙስና መሆኑን አስረድተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ መሆኑን የማትመሰክር ከሆነ ሙስና የሚገኝበትን መቃብር ስለምታስብ ነው። ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆን እስካሁን አለተገነዘቡም ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም በሚገባ ስላልሰበክን የእኛ ጥፋት ነው ብለው ይህ የሚሆነው የሰይጣንን የሙስና መንገድ በመከትል ዝምታን በሚመርጡበት ጊዜ ነው ብለዋል።    

ወደ ፊት ይህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከዓለማች ሲወገድ ተመሳሳይ ምርጫ ይጠብቀናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምርጫችንም ሕይወት እና የሕዝባችን ትንሳኤ፣  ይህ ካልሆን ደግሞ ራሳችንን ለገንዘብ በማስገዛት  የገንዘብ ባርነት ፣ ረሃብ፣ ጦርነት፣ የጦር መሣሪያዎች ምርት፣ ሕጻናት ያለ ትምህርት ወደ ሚያድጉበት መቃብር እንወርዳለን ብለዋል።

በግል እና በማኅበራዊ ሕይወታችን የገንዘብ ባሪያዎች በመሆን ወደ መቃብር ከመውደቅ ይልቅ የሕዝባችንን ዕድገት በማሰብ የእርሱን መልካም ዜናን የምናበስርበትን ኃይል እንዲሰጠን ወደ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታችንን እናቅርብ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያሳረጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመፈጸማቸው በፊት ባቀረቡት የቅዱስ ቁርባ ቡራኬ ጸሎት፥ “ኢየሱስ ሆይ! በቅዱስ ቁርባን ውስጥ በእውነት እንደምትገኝ አምናለሁ። ከሁሉም በላይ አብልጬ እወድሃለሁ፤ በነፍሴ ውስጥ እንድትገኝ እመኛለሁ። አሁን በምገኝበት ሁኔታ በቅዱሳት ምስጢራት አማካይነት ስጋህን እና ደምህን መቀበል ባልችልም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በልቤ ውስጥ ግባ። ከዚህ በፊት ወደ እኔ ስትመጣ እንዳደረግሁት ሁሉ በደስታ እቀበልሃለሁ፤ ዘወትር ካንተ ጋር መሆን ስለምፈልግ ካንተ እንዳልለይ አድርገኝ፤ አሜን” የሚለውን ጸሎት ከደገሙ በኋላ ቅዱስነታቸው  በወቅቱ ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ አጠናቀዋል።      

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ ካጠናቀቁ በኋላ ከፋሲካ በዓል አንስቶ እስከ ጴርቅሊጦስ በዓል ድረስ “የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን አበሰራት፣ እርሷም በመንፈስ ቅዱስ ጸነሰች”  በማለት ከፋሲካ ወቅት ውጪ በሚደገመው የብሥራተ ገብርኤል ጸሎት ተክቶ የሚደገመው “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ" የተሰኘው ጸሎት በመዝሙ መልክ መዘመሩ ተገልቱጹዋል። የእዚህ መዝሙር ሙል ይዘት የሚከተለው ነው።

የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ – ሃሌ ሉያ

እሱን ለመሸከም በቅተሻልና – ሃሌ ሉያ –

እንደተናገረው ከሙታን ተለይቶ ተነሣ – ሃሌ ሉያ

እግዚአብሔርን ለምኝልን – ሃሌ ሉያ

ድንግል ማርያም ሆይ በጣም ደስ ይበልሽ – ሃሌ ሉያ –

ጌታ በእውነት ስለተነሣ – ሃሌ ሉያ፡፡

13 April 2020, 14:25
ሁሉንም ያንብቡ >