ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣                ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአካል ጉዳተኞችን የሚንከባከቡ የጤና ባለሞያዎች በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ሚያዝያ 10/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ጊዜ ለአካል ጉዳተኞች የሕክምና ድጋፍን በማድረግ ላይ የሚገኙ የጤና ባለሞያዎችን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በስብከታቸው፣ ክርስቲያን ከመንፈስ ቅዱስ የሚያገኘውን ነጻነት በመጠቀም እውነትን በድፍረት መናገር የሚችል መሆኑን አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ቅዱስነታችው በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መጀመሪያ ላይ በተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ከመዝሙር ዳዊት በምዕ. 104 ላይ፣ እግዚአብሔር በግብጽ ምድር ሲሰቃይ የኖረ ሕዝቡን ነጻ በማውጣት በደስታ ተሞልተው ለምስጋና እንዲበቁ ማድረጉን አስታውሰዋል። በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ለሚሰቃዩት የአካል ጉዳተኞች የሕክምና ዕርዳታን ማቅረ ፈታኝ እና አስቸጋሪ መሆኑን የተረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለእነዚህ ሰዎች የሕክምና እርዳታን በማድረግ ላይ የሚገኙ የጤና ባለሞታዎችን በሙሉ በጸሎታቸው እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሐዋ. ሥራ ምዕ. 4: 13-21 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ንባብ ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከት፣ ሐዋርያት፣ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ዮሐንስ የኢየሱስን ስም በመጥራት ለማንም እንዳይናገሩ ከሸንጎ አባላት በኩል ብርቱ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም “ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ተገቢ ነውን? እስቲ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። እኛስ ያየነውን እና የሰማነውን ከመናገር አንቆጠብም” በማለት በግልጽ መናገራቸውን አስታውሰዋል። ግልጽነት የወንጌል አብሳሪዎች መለያ ምልክት ነው ያሉት ቅዱስነታቸ ድፍረት ክርስቲያኖችን በነጻነት እንዲናገሩ ያደርጋቸዋል ብለዋል። የሸንጎ አባላት ልብ የተዘጋ በመሆኑ ግልጽ አልነበሩም ያሉት ቅዱስነታቸው ልባቸው የተዘጋ በመሆኑ መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ውስጥ ሊገባ አልቻለም ብለዋል። ከሸንጎ አባላት ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ሐዋርያው ጴጥሮስ ፍርሃት ቢሰማውም ከመንፈስ ቅዱስ ድፍረት ማግኘቱን ቅዱስነታቸው ገልጸው ክርስቲያን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሕብረት ስላለው እውነትን በድፍረት መናገር የሚችል መሆኑን አስረድተዋል።     

ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ዕብራዊያን በላከው መልዕክቱ በምዕ. 10:35 ላይ “እንግዲህ ታላቅ ሽልማት የምታገኙበትን መተማመኛችሁን አትጥጣሉት” ያለውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የወንጌል ተልዕኮም ከዚህ ይጀምራል ብለው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ድፍረትን በመስጠት ወንጌልን በታማኝነት እንድናበስር ያደርጋል ብለዋል።   

ከማር. 16: 9-15 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤን ለማመን ልባቸውን ያደነደኑ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ እንደነቀፋቸው እና ቀጥሎም ለእያንዳንዱ ፍጥረት ወንጌልን በድፍረት እንዲያስተምሩ በማዘዝ ወደ ዓለም ሁሉ የላካቸው መሆኑን አስታውሰው እግዚአብሔር ወንጌልን በድፍረት ማብሰር የምንችልበትን ጸጋ ይስጠን በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያሳረጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመፈጸማቸው በፊት ባቀረቡት የቅዱስ ቁርባ ቡራኬ ጸሎት፥ ኢየሱስ ሆይ ፣ በእግሮችህ ስር በመምበርከክ ወደ ቅድስናህ መግባት እችል ዘንድ የልቤን ንስሐ ወደ አንተ አቀርባለሁ። የፍቅር ምስጢር የሆነው ቅዱስ ቁርባንህ ዘወትር አከብርሃለሁ። አሁን በምገኝበት ጎስቋላ ሥፍራ ሆኜ በልቤ ውስጥ ልቀበልህ እፈልጋለሁ። ከቅዱስት ምስጢራት ጋር በማደርገው አንድነት የሚገኘውን ደስታ በመጠባበቅ በመንፈስ ልቀበልህ እፈልጋለሁ። እኔ ወደ አንተ ከመምጣት ይልቅ አንተ ወደ እኔ ና፤ ፍቅርህ ሁለንተናዬን በመግዛት እስከ ሞት ድረስ መላ ሕይወቴን ያብራኝ። ዘወትር ባንተ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እወድሃለሁ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለት ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ ካጠናቀቁ በኋላ ከፋሲካ በዓል አንስቶ እስከ ጴራቅሊጦስ በዓል ድረስ የሚደገመው “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ" የተሰኘ ጸሎት በመዝሙር ቀርቧል፥

የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ – ሃሌ ሉያ

እሱን ለመሸከም በቅተሻልና – ሃሌ ሉያ –

እንደተናገረው ከሙታን ተለይቶ ተነሣ – ሃሌ ሉያ

እግዚአብሔርን ለምኝልን – ሃሌ ሉያ

ድንግል ማርያም ሆይ በጣም ደስ ይበልሽ – ሃሌ ሉያ –

ጌታ በእውነት ስለተነሣ – ሃሌ ሉያ፡፡

18 April 2020, 17:39
ሁሉንም ያንብቡ >