ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣                ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ፖለቲከኞች አገራቸውን ለመጥቀም እንዲተባበሩ ጸልየዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ ሚያዝያ 12/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በፖለቲካው ዓለም ተሰማርተው ሕዝባቸውን የተጠሩትን፣ ወንዶችን እና ሴቶችን በጸሎታቸው አስታውሰው፣ በመንፈስ ቅዱስ እንደገና ስለመወለድ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ ሚያዝያ 11/2012 ዓ. ም. ተከብሮ የዋለውን የመለኮታዊ ምሕረት ክብረ በዓል ከቫቲካን ከተማ ውጭ፣ ሮም በሚገኝ በመንፈስ ቅዱስ ቁምስና አክብረው መመለሳቸው ታውቋል። ቅዱስነታችው በቫቲካን በሚገኘው ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤተ ያሳረጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመጀመሪያ በፊት እንዳስገነዘቡት በፖለቲካ ሕይወት ተሰማርተው ሕዝባቸውን ለማገልገል የቆሙ ወንዶችን እና ሴቶችን በጸሎት እናስታውሳቸው ብለው ፖለቲካ የቸርነት ሕይወት ከፍተኛ ደረጃ መሆኑን አስረተዋል። ቅዱስነታቸ ከዚህም ጋር በማዛመድ፣ ፖለቲከኞች ለሚመሯቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ቅድሚያን ከመስጠት ይልቅ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መላውን የሰው ልጅ እያሰቃየ በሚገኝበት ባሁኑ ወቅት የጋራ መድረክን ፈጥረው ለአገር ጥቅም እና ደህንነት ማሰብ እንዳለባቸው አደራ ብለዋል።

ኢየሱስና ኒቆዲሞስ፣

ከዮሐ. 3:1-8 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ፈሪሳዊው የአይሁድ መሪ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ሄዶ ሕዝቡ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ጥሩ ጋር ካልሆነ በቀር እነዚህን አንተ የምታደርጋቸውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል ማንም የለም፤ ስለዚህ አንተ ከእግዚአብሔር ጋር ዘንድ የመጣህ መምህር እንደሆንክ እናውቃለን” ማለቱን አስታውሰው፣ የኒቆዲሞስ ኑዛዜ እርሱ ራሱ ምን ማድረግ እንዳለበት በሚገባ ማወቅ አለመቻሉን ያመለክታል ብለዋል።

ዳግመኛ መወለድ፣

ኢየሱስም ለኒቆዲሞስ ሲመልስ “እውነት፣ እውነት እልሃለሁ፤ ሰው እንደገና ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ማለቱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ኒቆዲሞስም የኢየሱስን ንግግር በትክክል ካለመረዳቱ የተነሳ “ታዲያ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል?” ባለው ጊዜ ኢየሱስም “ዳግመኛ ከውሃ እና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድ አለበት በማለት ማስረዳቱን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

መንፈስ ቅዱስ፣

“መንፈስ ቅዱስ ከወዴት በኩል እንደሚመጣ ማወቅ አስቸጋሪ ነው“ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲያስረዳ “ነፋስ ወደ ፈለገው አቅጣጫ ይነፍሳል፣ ድምጹንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደሚመጣና ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፣ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው” ማለቱን አስታውሰዋል። ነፍሱ ለመንፈስ ቅዱስ ያስገዛ ሰው ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ የሚንቀሳቀሰው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እና ከእርሱ በሚያገኘው ነጻነት ይኖራል ብለዋል።

የመልካም ክርስቲያን ምልክቶች፣

ጥሩ ክርስቲያን ማለት የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት መጠበቅ ብቻ እንዳልሆነ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ብቻ የተገደብን ከሆነ ጥሩ ክርስቲያን አይደለንም ብለው፣ ጥሩ ክርስቲያን ማለት መንፈስ ቅዱስን ወደ ልቡ በመቀበል እርሱ ወደሚመራው አቅጣጫ የሚጓዝ ነው ብለዋል። እንደ ኒቆዲሞስ ምን ማድረግ እንዳለብን ካለማወቅ የተነሳ ግራ ልንጋባ እንችል ይሆናል። መንፈስ ቅዱስን ወደ ልባችን ውስጥ ለማስገባት በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ዝቅተኛ ሊሆን ይችል ይሆናል። ነገር ግን እንደገና ለመወለድ ከፈልግን፣ ወዴት እንደምንደርስ ባናውቅም መንፈስ ቅዱስ እገዛ በነጻነት ለመጓዝ ፍላጎት እንዳለን ማሳየት ያስፈልጋል በማለት ቅዱስነታቸው ምክራቸውን አካፍለዋል።

መንፈሳዊ ነጻነት እና ድፍረት የሚገኘው ከጸሎት ነው፣

ሐዋርያት ችግር ሲያጋጥማቸው እና ከችግራቸው የሚወጡበት መንገድ ሲዘጋባቸው በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቀርበው በመንፈስ ተሞልተው እንደሚወጡ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ጸሎት ለመንፈስ ቅዱስ መንገድን እንደሚከፍት እና በነጻነት ለመጓዝ የሚያስችል ኃይል ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

ከሐዋ. ሥራ 4:23-31 ተወስዶ የተነበበውን የመጀምሪያ ንባብ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ጴጥሮስ እና ዮሐንስ ወደ ካህናት አለቆች እና የአይሁድ ሽማግሌዎች ዘንድ ቀርበው ከተመለሱ በኋላ በክርስቲያን ማኅበረሰብ መካከል ፍርሃት እንደነገሠ ገልጸው፣ ነገር ግን በአንድነት ሆነው ጸሎታቸውን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ባቀረቡ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የእግዚአብሔርን ቃል በድፍረት ለመመስከር መብቃታቸውን አስታውሰዋል።

“በመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ መወለድ ማለት ይህ ነው” በማለት ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ በጥርጣሬ ውስጥ በመግባት ከዚህ በፊት ስናከናውን የቆየናቸውን መልካም ተግባራት፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት፣ ሐይማኖታዊ ልማዶችንም ከመፈጸም ወደ ኋላ ማለት እንደማይገባ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን ስብከት ከማጠቃለላቸው በፊት ባሳረጉት ጸሎት፣ ወዴት እንደሚወስደን እንኳ እርግጠኞች ባንሆንም መንፈስ ቅዱስ ለጉዟችን ድፍረት እንዲሰጠን ጠይቀው፣ ለመንፈስ ቅዱስ ራሳችንን ክፍት በማድረግ፣ ለእግዚአብሔር በምናቀርበው አገልግሎት የመንፈስ ቅዱስ እገዛ እንዲጨመርበት በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። 

20 April 2020, 14:51
ሁሉንም ያንብቡ >