ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ካህናት ቅዱስ ቁርባንን ለኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች እንዲያድሉ ጠየቁ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎታቸውን በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት የሚያሳርጉ መሆኑ ይታወቃል። ዛሬ መጋቢት 1/2012 ዓ. ም. ጠዋት ላይ ያቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በቀጥታ በቪዲዮ ምስል መሰራጨቱ ታውቋል። የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት እቤታቸው ሆነው ለሚከታተሉት ምዕመናን በቀጥታ ሲተላለፍ የዛሬው ሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ቀጣይነትም ያለው መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንዳስገነዘቡት በኮሮና ቫይረስ ለተያዙት ሕሙማን የህክምና አገልግሎትን በማቅረብ ላይ ለሚገኙት የጤና ባለሞያዎች በሙሉ ብርታትን ተመኝተው በበሽታው የተያዙትንም በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ በኮሮና ወረርሽኝ በመያዛቸው ምክንያት ከማሕበረሰብ ተነጥለው ሕክምናን በማግኘት ላይ ለሚገኙት ሕሙማን ካህናት ወደሚገኙበት ደርሰው የቅዱስ ወንጌልን መልካም ዜና እንዲያበስሩ ቅዱስ ቁርባንን እንዲያድሉ ጠይቀዋል።       

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በማሕበራዊ ድረ ገጽ በኩል በቀጥታ ሲተላለፍ በነበረው በዛሬው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁትን በሙሉ በጸሎታቸው ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሕክምና አገልግሎት ለማበርከት የተሰማሩ የጤና ባለሞያዎችን እና እንክብካቤ በማድረግ ላይ የሚገኙትን አስታውሰዋል።   

“ለካህናት እንጸልይ፣ ድፍረትን በማግኘት፣ በቫይረሱ ወደ ተያዙት ሰዎች ዘንድ ሄደው የእግዚአብሔርን የማዳን ኃይል እንዲመሰክሩ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ እና ደም ማደል እንዲችሉ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ጸሎታችንን እናቅርብ። የሕክምና አገልግሎትን ለሚያበረክቱት የጤና ባለሞያዎችን እና እንክብካቤን በማድረግ ላይ የሚገኙትን በጎ ፈቃደኞችን በጸሎታችን እናስታውስ”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያሳረጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ለተካፈሉት ካህናት፣ ደናግል እና ምዕመናን ያቀረቡት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ከማቴ. 23: 1-12 ተውስዶ በተነበበው የወንጌል ክፍል መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በዚህ አስተንትኗቸው በኩል እንዳስረዱት በዘመኑ የነበሩ የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን በሰዎች ዘንድ እራሳቸውን ከፍ በማድረግ፣ ጌቶች ተብለው እንዲጠሩ፣ በሌላ ወገን ሲታይ ግን ወደዚህ ደረጃ የሚያደርሳቸው ምንም ዓይነት የሥነ ምግባር ብቃት የሌላቸው ግብዞች መሆናቸውን አስረድተዋል።

“በትናንትናው ዕለት የተነበበው የእግዚአብሔር ቃል፣ ኃጢአታችንን አውቀን እንድንናዘዝ፣ የምናውቀውም በአዕምሮአችን ብቻ ሳይሆን በልባችንም ጭምር፣ በኃጢአታችንም በማፈር ሊሆን ይገባል። በኃጢያታችን አፍረን ወደ እግዚአብሔር ፊት ስንቀርብ ምን ያህል ማዘናችንን ይገልጻል። ዛሬ እግዚአብሔር፣ እኛ ኃጢአተኞች በሙሉ ወደ እርሱ ዘንድ እንድንቀርብ እና ከእርሱ ጋር እንድንነጋገር ይጠራናል። ምክንያቱም ኃጢአታችን ብቻችን ተነጥለን እንድንቀር እና እንድንደበቅ ያደርገናል፤ በውስጣችን ያለው እውነት እንዲሰወር ያደርጋል። አዳምን እና ሔዋንን ያጋጠማቸው ይህ ነው፤ አዳም እና ሔዋን ኃጢአትን ከሠሩ በኋላ ተደበቁ። የተደበቁትም በሠሩት ኃጢአት ስላፈሩ ነው፤ እራቁታቸውም ነበሩ። ኃጢአት የሠራ ሰው ስለሚያፍር መደበቅን ይመርጣል። ኃጢአትን በሠራን ቁጥር ሁሉ እግዚአብሔር ይጠራናል፤ ፍርሃትን አስወግደን በምንገኝበት ሁኔታ ላይ እንወያይ ይለናል። እግዚአብሔር ይህን ጥሪውን አያቋርጥም። በኃጢአት ብዛት ብትቆሽሹም እንደ በረዶ ነጭ ትሆናላችሁ ይለናል፤ ወደ እኔ ኑ! እኔ ሁሉን የመለወጥ ችሎታ አለኝ ይለናል። ስለዚህ ሳንፈራ ወደ እርሱ ቀርበን ችግራችንን እናወያየው።           

በኃጢአቱ በመጸጸአት ዘወትር በጸሎት የሚተጋውን አንድ ቅዱስ ሰው አስታወስኩኝ። እግዚአብሔር የሚጠይቀውን ሁሉ ያቀርብለት ነበር። ነገር ግን ያም ሆኖ እግዚአብሔር አልተደሰተበትም። አንድ ቀን ይህ ሰው ተቆጥቶ ስለነበር ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ቀርቦ፣ እኔ ምንም ሊገባኝ አልቻለም፤ የምትጠይቀኝን ሁሉ ሳላጓድል ዘወትር እስጥሃለሁ። ነገር ግን ደስተኛ አትመስልም። የሚግድልብኝ ነገር ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀው። እግዚአብሔርም ኃጢአቶችህን በሙሉ ምንም ወደ ኋላ ሳታስቀር ስጠኝ፤ የሚቀርብህም ይህ ነው አለው። ስለዚህ ኃጢአታችንን ፈርተን ሳንደብቅ ለእግዚአብሔር መናገር ያስፈልጋል፤ እርሱ በምሕረቱ አጥቦን እንደ በረዶ ያነጻናል።

እግዚአብሔር ይህን እንድናደርግ ይጋብዘናል። ነገር ግን ወደ ኋላ የሚያስቀረን አንድ ነገር አለ። ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ከመቅረብ ይልቅ ራሳችንን እንደ ጻድቅ አድርገን፣ ኃጢአት እንደሌለበት አድርገን እንመለከታለን። ኢየሱስ ክርስቶስ የኦሪት ሕግ መምህራንና ለፈሪሳውያን የሚነግራቸው ይህንን ነው። እነዚህ ሰዎች አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡት በሰዎች መወደስን፣ መከበርን፣ ይፈልጋሉ፤ በክብር ሥፍራ መቀመጠን ይመርጣሉ፤ መምህራን እና አዋቂዎች ተብለው መጠራትን ይፈልጋሉ። ውጫዊ ገጽታችን ውስጣዊ ማንነታችንን፣ የልባችንን እውነት ስለሚሸፍን ከንቱ ነው። ልባችንን የሚመርዝ፣ ልባችን ለእግዚአብሔር ጥሪ እንዲደነድንም ስለሚያደርግ ከዚህ በሽታ መፈወስ እጅግ አስቸጋሪ ነው።

ከንቱነት ከእግዚአብሔር ጥሪ ራሳችንን ሰውረን እንድንቀር ያደርገናል። ነገር ግን እግዚአብሔር በአባታዊ ፍቅሩ ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይጋብዘናል። ይህ የእግዚአብሔር ጥሪ ብርታትን እንዲሰጠን፣ ወደ እርሱ በምናቀርበው ጸሎት አማካይነት ኃጢአታችንን እና ድክመቶቻችንን ከእርሱ ጋር እንነጋገር። እርሱ እኛ ማን እንደሆንን ያውቃል። እኛም ኃጢአተኛነታችንን እናውቃለን ነገር ግን ከንቱ በመሆናችን ልንደብቀው እንሞክራለ። ወደ እርሱ በድፍረት ቀርበን ምሕረትን እንድንለምን እግዚአብሔር እገዛውን ይስጠን”።

    በማለት ዛሬ መጋቢት 1/2012 ዓ. ም. ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
10 March 2020, 15:59
ሁሉንም ያንብቡ >