ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከቤት እንዳይወጡ የታዘዙ ቤተሰቦችን እና ሕጻናትን በጸሎት አስታወሱ።

ቅዳሜ መጋቢት 12/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ወስጥ በሚገኝ የቅድስት ማርታ ጸሎት በቀረቡት የመስውዕተ ቅዳሴ ጸሎት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኮሮና ቫይረስ መዛመትን ለመከላከል ሲባል በእነዚህ ቀናት ውስጥ ከቤት እንዳይወጡ የታዘዙ ቤተሰባችን እና ሕጻናትን በድጋሚ አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በዛሬው ስብከታቸው እነዚህን ቤተሰቦች ትህትናን በተላበሰ መንገድ በጸሎት እንድናስታውሳቸው አሳስበውናል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዛሬም ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በቀጥታ ይተላለፍ በነበረው የቪዲዮ ምስል ስርጭት በኩል ለቤተሰቦች ባስተላለፉት መልዕክት፣ የቤተሰብ አባላት፣ አረጋዊያን፣ አባት፣ እናት፣ ወጣቶች እና ሕጻናት እርስ በእርስ በመገናኘት በመካከላቸው ፍቅርን ለማሳደግ የሚያስችል ትክክለኛ መንገድን ለማውቅ ያግዛል ብለው በዚህ አስፈሪ ወቅት በቤተሰብ መካከል ሰላም እንዲሰፍን ጸሎታችንን እናቅርብ ብለዋል።

ለዕለቱ በተመደቡት የመጀመሪያ ንባብ፣ ከትንቢተ ሆሴዕ 6: 1-6 ላይ እና ከሉቃ. 18: 9-14 ተወስደው በተነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በማስተነተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጸሎትን አስመልክተው ባቀረቡት ስብከታቸው፣ ራሱን እንደ ጻድቅ በመቊጠር የሚመካ ፈሪሳዊ እና በርቀት ቆሞ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ማየት እንኳ ያልፈለገውን ቀረጥ ሰብሳቢን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ከፈሪሳዊው ይልቅ ቀረጥ ሰብሳቢው በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ጻድቅ ተቈጥሮ ወደ ቤቱ መመለሱን አስታውሰው ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላልና፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይላል” የሚለውን የወንጌል ክፍል በማስታወስ ጸሎታችን ራሳችንን ከማንም ጋር ሳናወዳድር፣ በትህትና የተሞላ መሆን አለበት ብለዋል።

በትናንትናው ዕለት ከትንቢተ ሆሴዕ 14:2-10 ላይ ተወስዶ የተነበበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እንደዚሁም ዛሬ ከትንቢተ ሆሴዕ 6:1-6 ተወስዶ የተነበበውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወደ እግዚአብሔር ቤት መመለስ፣ ድነትን ከእርሱ ብቻ ማግኘት እንደምንችል መናገሩን አስረድተዋል። በትንቢተ ሆሴዕ 6: 3 ላይ እግዚአብሔርን እንወቀው፤ የበለጠ እናውቀውም ዘንድ እንትጋ፤ እንደ ንጋት ብርሃን፣ በእርግጥ ይገለጣል፤ ምድርን እንደሚያረሰርስ የበልግ ዝናብ፣ እንደ ክረምትም ዝናብ ወደ እኛ ይመጣል” የሚለውን በመጥቀስ የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ተስፋ በማድረግ ወደ እርሱ መመለሱን አስታውሰው፣ ጸሎትም እግዚአብሔርን ማግኘት ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ በመሆኑ በጸሎት አማካይነት ወደ እርሱ እንመለስ ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ በኩል እንዴት መጸልይ እንዳለብን ያስተምረናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ህግ የሚያዘውን ሁሉ እፈጽማለሁ፣ አከብራለሁም፣ በሳምንት ሁለት ጊዜ እጾማለሁ፣ ስለሆነም ከእኔ የሚሻል የለም ያለው ፈሪሳዊ፣ እንደዚሁም በሉቃ. ምዕ. 15 ላይ ጠፍቶ በተገኘው ልጅ ምሳሌ ላይ ታላቅ ልጅ ከአባቱ ጋር የመኖር ትርጉም፣ የአባት ፍቅር ምን እንደሆነ ሳይገነዘብ በመቅረቱ መቆጣቱ ትዕቢተኝነት መሆኑን፣ በሌላ ወገን በርቀት ቆሞ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ማየት እንኳ ያልፈለገው ቀረጥ ሰብሳቢ፣ ደረቱን እየደቃ፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ’ በማለት ያቀረበው ጸሎቱ በእግዚአብሔር ዘንድ ተደማጭነትን ሊያገኝ መቻሉን አስረድተዋል።

በእነዚህ ምሳሌዎች በኩል እንዴት መጸለይ እንደሚጋባን፣ በምን መልኩ ወደ እርሱ መቅረብ እንደሚገባ እግዚአብሔር ያስተምረናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ እግዚአብሔር የምናቀርበው ጸሎት በትህትና የተሞላ፣ ማንነታችንን ደብቀን ሳይሆን ልባችንን ገልጠን የእርሱን ምሕረት ለመቀበል ወደ እርሱ መቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል። ወደ እግዚአብሔር የምንቀርበው በልበ የዋህነት ሳይሆን እንደ ፈሪሳዊው ራስን ከፍ በማድረግ እና በመጻደቅ ከሆነ ኃጢአታችን በልባችን ውስጥ ተደብቆ ይቀራል ብለዋል። ኃጢአታችንን በምንናዘዝበት ጊዜ ሚዛን ላይ በማስቀመጥ ወይም የፈጸምንበትን ምክንያት ሳናቀርብ በቀጥታ መናዘዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

ጸሎታችንን ወደ እግዚአብሔር በምናቀርብበት ጊዜ የእርሱን ፈቃድ በመለመን እንጂ ጥያቄአችን በግል ምኞት መሠረት ይፈጸምልናል በማለት እርግጠኞች ከሆንን ይህ ደግሞ ጸሎት መሆኑ ቀርቶ በመስተዋት ራሳችንን እንደማየት ይቆጠራል ብለዋል። በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ስንቀርብ የምንገኝበትን ሁኔታ በእውነት በሚገልጽ መንገድ፣ ከሁሉም በላይ ኃጢአተኛነትን በማመን እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመለመን መሆን እንዳለበት ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምረናል ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን የቅዱስ መጽሐፍት ንባባት አስተንትኗቸውን ከመፈጸማቸው በፊት ባቀረቡት የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ ጸሎት፥

“ኢየሱስ ሆይ! በቅዱሳት ምስጢራት ውስጥ አንተ እንደምትገኝ በእውነት አምናለሁ፤ ከሁሉ በላይ እወድሃለሁ፣ በሕይወቴ ውስጥ አንተ እንድትገኝ እመኛለሁ። በዚህ አስፈሪ ወቅት የአንተን ስጋ እና ደም መቀበል ባልችልም ከዚህ በፊት እንዳደረከው ሁሉ ዛሬም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በልቤ ውስጥ ግባ። ካንተ ላለመለየት ወስኜአለሁና በሙሉ ልቤ እቀበልሃለሁ”

በማለት የዕለቱን አስተንትኗቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
21 March 2020, 16:26
ሁሉንም ያንብቡ >