ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “አሁን ያለብንን ፍርሃት እንድናሸንፍ እግዚአብሔር ይርዳን”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ መጋቢት 17/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው ዛሬ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ በተላላፊው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት በፍርሃት ውስጥ የሚገኙ አረጋዊያንን፣ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የሕዝባዊ ተቋማት ሰራተኞችን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸ በማከልም የእግዚአብሔርን ስጦታዎች በሙሉ በከንቱ እንድናጣቸው የሚያደረጉን ነገሮችየትኞቹ እንደሆኑ ለይተን ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በቪዲዮ ምስል በቀጥታ በተሰራቸው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ተላላፊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መላው ዓለምን እያስፈራራ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የያዘንን ፍርሃት ማሸነፍ እንድንችል የእግዚአብሔርን እርዳታ ተማጽነዋል።

በእነዚህ ቀናት ውስጥ በሕዝቦች መካከል ከፍተኛ ስቃይ ይታያል፣ ብዙዎችም በፍርሃት ውስጥ ይገኛሉ ያሉት ቅዱስነታቸው ከእነዚህም መካከል የሚረዳቸውን አጥተው በቤታቸው ውስጥ ብቻቸውን የቀሩ፣ በሕክምና መስጫ ማዕከላት ውስጥ በሕመም ላይ የሚገኙ በርካታ አረጋዊያ መኖራቸውን አስታውሰው፣ ፍራሃታቸውም በዚህ አስጨናቂ ወቅት ሊያጋጥማቸው የሚችል አደጋ ስለሚገነዘቡ ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ሰዎች ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለው እቤት ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸው የእነዚህ ሰዎች ጭንቀትም ከወረርሽኙ በተጨማሪ ለቤተሰባቸው የሚሆን ቀለብ ከወዴት ማግኘት እንደሚችሉ በማሰብ ነው ብለዋል። በሕዝባዊ አገልግሎቶች ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎችም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሕይወታቸው የሰጉ መሆናቸውን አስረድተዋል። እያንዳንዳችን ከደረብን ፍርሃት የምንላቀቅበትን ኃይል ከእዚአብሔር ዘንድ ለማግኘት በጸሎት መበርታት ይኖርብናል ብለዋል።

ለዕለቱ በተመደበው የመጀመሪያ ንባብ፣ ኦሪት ዘጸዓት 32፡ 7-14 ላይ በማስተነተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተጠቀሰውን የወርቅ ጥጃ አምልኮን አስታውሰው የጣኦት አምልኮዎች በልባችን ይዘን የምንመራ ከሆነ የእግዚአብሔርን ስጦታዎች እናጣለን ብለዋል። የጣኦት አምልኮ የተሳሳተ የእምነት መንገድ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው በእውነትም እነዚህን የተሳሳቱ የአምልኮ መንገድ በልባችን ይዘን የምንከተል ከሆነ ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ዛሬ በተነበቡት ቅዱስት መጽሐፍት ላይ በማስተነተን የሚከተለውን ስብከተ ወንጌል አቅርበዋል፥

“ከኦሪት ዘጸዓት 32፡ 7-14 ላይ ተወስዶ በተነበበው የመጀመሪያ ንባብ ውስጥ የሰዎች ልብ መለወጥ የታየበትን ሁኔታ እናያለን። ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሕግጋትን ለመቀበል ወደ ሲና ተራራ ላይ ወጣ። እግዚአብሔር በድንጋይ ላይ የጻፋቸውን ሕጎች ለሙሴ ሰጠው። ነገር ግን ሙሴ በዘገየ ጊዜ ሕዝቡ ተቆጥቶ ወደ አሮን በመመለስ እንዲህ አለ። ሙሴ ለበርካታ ጊዜ ተሰውሮብናል፤ እኛም ያለ መሪ ብቻችን ቀርተናል፤ ወዴት እንዳለም አናውቅም አሉት። ስለዚህ ወደ ፊት እንድንጓዝ የሚረዳንን አምላክ እንፍጠር አሉ። በኋላ ላይ ካህን በመሆን ሕዝቡን ለማገልገል የበቃው አሮን፣ የሕዝቡን ስሞታ ካዳመጠ በኋላ ኣንዲህ አላቸው፥ ያላችሁት ትክክል ነው፣ ያላችሁትን ወርቅ እና ብር ስጡኝ አላቸው። እነርሱም ወርቃቸውን እና ብራቸውን አውጥተው ሰጡት። እርሱም በወርቃቸው የጥጃ ሐውልት ሰራ።

ምዕመናን ባቀረቡት የመዝሙር መልስም እግዚአብሔር ቅር መሰኘቱን ሰምተናል። በመዝሙረ ዳዊት 106 ላይ “በኮሬብ ጥጃ ሠሩ፤ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ፤ ክብራቸው የሆነውንም ሣር በሚበላ፣ በበሬ ምስል ለወጡ” ይላል። የመጀመሪያው የዛሬው ንባብ የሚጀምረው ከዚህ ነው። እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ከግብፅ ያወጣኻቸው ሕዝብህ ስተዋልና ውረድ አለው፤ ካዘዝኋቸው ፈቀቅ ለማለት ፈጣኖች ሆኑ፤ ለራሳቸውም በጥጃ ምስል የተቀረጸ ጣዖትን ሠሩ፤ ለእርሱም ሰገዱለት፤ ሠዉለትም፤ እንዲሁም፣ ‘እስራኤል ሆይ፤ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው’ ” አሉ። እግዲህ እውነተኛ ክህደት ይህ ነው። ሕያው እግዚአብሔርን ከማምለክ ይልቅ ጣኦትን ማምለክ ወደዱ። ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ እስኪመለስ በትዕግስት መጠበቅ አልቻሉም። እንግዳ ነገርን አዘጋጅተው መጠበቅን ፈለጉ። ይህን በተመለከተ አንዳንድ ነገሮችን መጠቆም እፈልጋለሁ።

ከሁሉም በላይ ሕዝቡ እግዚአብሔር አምላካቸውን ከማምለክ ይልቅ ጣኦትን ለማምልክ ምኞት እንዳደረባቸው እንመለከታለን። ወደ ጣኦት አምልኮ እንደገና መመለስን መረጡ፣ እግዚአብሔርን በትዕግስት መጠበቅ አልቻሉም። ይህን የመሰለ የተሳሳተ ምኞት በዛሬው ዘመን በእኛ መካከልም ሲንጸባረቅ እናያለን። እግዚአብሔርን በታማኝነት ኣና በነጻነት መከተል እንጀምራለን። ቀስ በቀስ ማማረርን እንጀምራለን። የችግር ዘመን ነው፣ የምንገኘውም በበርሃ ውስጥ ነው፣ ውሃ ያስፈልገናል፣ ምግብም ያስፈልገናል፣ በግብጽ ምድር ብዙ ጥሩ ነገሮችን ስንመገብ ቆይተናል፥ እዚህ ግን ምንም ነገር የለም። ጣኦትን ማምለክ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን እንድናይ ያደረገናል። ክፉ ነገሮችን እንዳናይ ዓይናችንን ይጋርደዋል። ዛሬ በተነበበው የኦሪት መጽሐፍ ላይ ታሪክ  እንዳየነው የሙሴ ሕዝብ በግብጽ ውስጥ የበሉትን ጮማ እና መልካም የሆኑ ነገሮች በሙሉ አስታውሰዋል። ነገር ግን በግብጽ ምድር በነበሩበት ጊዜ በባርነት ተይዘው መቆየታቸውን ዘንግተዋል።

በሌላ ወገንም ጣኦትን ማምለክ ሁሉን ነገር እንድናጣ ያደርጋል። አሮን የወርቅ ጥጃን ለመስራት ብሎ ወርቃቸውን እና ብራቸውን እንዲሰጡት በጠየቋቸው ጊዜ ያላቸውን ሁሉ አውጥተው ሰጡት። እነዚያ ወርቆች እና ብሮች ከእግዚአብሔር ያገኟቸው ስጦታዎች ነበሩ። ከእግዚአብሔር ባገኙት ስጦታዎች የጣኦት ማምለኪያን አዘጋጁ። ይህ በራሱ አስነዋሪ ድርጊት ነው። ይህ አስነዋሪ ተግባር ዛሬ በዓለማችንም ይከሰታል። ጣኦትን ማምለክ ስንጀምር ከእግዚአብሔር በሚያርቁን ነገሮች ላይ እንጣበቃለን። ከእግዚአብሔር የምንርቀውም ከእርሱ በተቀበልነውን ስጦታ የጣኦት ምልክቶችን ስለምንሰራበት ነው። እነዚህን ከእግዚ አብሔር የተቀበልናቸውን ስጦታዎች ለጣኦት አምልኮ የምናውላቸው በሚገባ እያወቅን፣ በሙሉ ፍላጎት እና ፍቅር ከልብ ተነሳስተን ነው። አንዳንዶቻችሁ በጣኦት አላመልክም፣ በቤቴ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል አለ። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል አለ ትሉ ይሆናል። ጣኦትን በልብ ውስጥ ብቻ ሊመለክ ይችላል። ይልቅስ ራስን መጠየቅ ያለብን ጥያቄ፥ በልቤ ውስጥ በስውር የማመልከው ጣኦት የቱ ነው? የሚል መሆን አለበት። በእውነት ከእግዚአብሔር የሚያርቀኝ ነገር ምንድር ነው? ብለን ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል። ራሔል ከአባቷ በሸሸችበት ጊዜ ብዙ ቁሳ ቁሶችን በልብሶቿ ውስጥ ደብቃ እንደወጣች ሁሉ እኛም ብዙ ጣኦቶችን በልብሶቻችን ልንሸፍን፣ በልባችን ውስጥ ልንደብቅ እንችላለን።

ዛሬ መጠየቅ የምፈልገው ጥያቄም ይህ ነው፥ ከእግዚአብሔር አምላክ ርቀን በስውር የምናመልከው ሌላ አምላክ የቱ ነው? ይህን የተለየ አምልኮ አስወግደን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በመቅረብ በፊቱ ብቻ ልንሰግድ ይገባል። ጣኦትን ማምለክ ወደ ተሳሳተ እምነት ውስጥ ሊከት ይችላል። ወደ ዓለማዊነት ሊመራ ይችላል። ለቅዱሳት ምስጢራት ያለንን ክብር በዓለማዊነት ደስታ ሊቀይረው ይችላል። በጋብቻ ዕለት የሚደረገውን በዓል እናስታውስ። ምስጢረ ተክሊል፣ ሁለቱ ተጋቢዎች በእግዚአብሔር ፊት ቆመው አንዱ ሌላውን በእውነት እንደሚወዱ፣ ሁል ጊዜ አንዱ ለሌላው ታምኝ ሆነው ለመኖር ቃል በመግባት የእግዚአብሔርን ጸጋ የሚቀበሉበት ምስጢር ነው ወይስ ኣንዲሁ ለታይታ የሚደረግ ዓለማዊ ሥነ ሥርዓት ነው?

ዛሬ ላቀርብ የምፈልገው ጥያቄ፥ ጣኦታችን ምንድር ነው። በልባችን ውስጥ ሰውረን ያስቀመጥነው ጣኦት የቱ ነው? እግዚአብሔር በሕይወታችን መጨረሻ ላይ እያንዳንዳችንን “እራሳችሁን ከእኔ አርቃችኋል፣ ከመንገዴም ወጣችኋል፣ ለሌላ አምላክ ሰግዳችኋል” ይለናል። ስለዚህ እውነተኛ አምላካችንን ለይተን የምናውቅበትን ጸጋ እንዲሰጠን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቅ ካሉ በኋላ ለዛሬ ያቀረቡትን ስብከተ ወንጌል ከማጠቃለላቸው በፊት የሚከተለውን ጸሎት በሕብረት እንድናቀርብ ጠይቀዋል፥

“ኢየሱስ ሆይ! በቅዱሳት ምስጢራት ውስጥ አንተ እንደምትገኝ በእውነት አምናለሁ፤ ከሁሉ በላይ እወድሃለሁ፣ በሕይወቴ ውስጥ አንተ እንድትገኝ እመኛለሁ። በዚህ አስፈሪ ወቅት የአንተን ስጋ እና ደም መቀበል ባልችልም ከዚህ በፊት እንዳደረከው ሁሉ ዛሬም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በልቤ ውስጥ ግባ። ካንተ ላለመለየት ወስኜአለሁና በሙሉ ልቤ እቀበልሃለሁ”

በማለት የዕለቱን አስተንትኗቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 March 2020, 16:19
ሁሉንም ያንብቡ >