ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኮሮና ቫይረስ ጥቃት የሞቱ ሐኪሞችን እና ካህናትን በጸሎት አስታወሱ።

ዛሬ መጋቢት 15/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ በኮሮና ቫይረስ ለተያዙ ሕሙማን የሕክምና ድጋፍን እና መንፈሳዊ ብርታትን በመስጠት ላይ እያሉ በቫይረሱ በመያዝ ሕይወታቸውን ያጡ የጤና ባለ ሞያዎችን እና ካህናትን ቅዱስነታቸው በጸሎታቸው አስታውሰው የሌላውን ሕይወት ለማዳን ሲባል የራስን ሕይወት ለሞት አሳልፎ መስጠት የመንፈሳዊ ጀግንነት ምሳሌ ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በቪዲዮ ምስል በቀጥታ ሲሰራጭ በነበረው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ  በኮሮና ቫይረስ ለተጠቁት ሕሙማን የህክምና አገልግሎትን በማበርከት ላይ እያሉ በቫይረሱ ተይዘው ሕይወታቸውን ያጡ የሕክምና ባለሞያዎችን እና ካህናትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጸሎት  አስታውሰዋል። በጣሊያን ውስጥ በኮሮና ቫይረስ የተያዙት ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ የጤና ባለሞያዎች መኖራቸው ሲነገር በቫይረሱ ተይዘው የሞቱት ካህናት ቁጥርም ወደ ሃምሳ ይጠጋል ተብሏል።

በጣሊያን ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው የሞቱ ሐኪሞች እና ካህናት መኖራቸውን ተረድቼአለሁ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዚህም የበቁት በቫይረሱ ለተያዙት ሰዎች የሕክምና እና መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ለማበርከት በተሰማሩበት ወቅት ነው ብለዋል። የሌሎችን ሕይወት ለማዳን ሲሉ ሕይወታቸውን በመሰዋት የመንፈሳዊ ጀግንነት ምሳሌ ሆነው ስለተገኙ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባል ብለው እነርሱም ሆነ ቤተሰቦቻቸው በጸሎት እናስታውሳቸው ብለዋል።

ለዕለቱ በተመደበው ዮሐ. 5: 1-16 ላይ በማስተነተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ የወንጌል ክፍል ላይ ቤተ ሳይዳ በተባለች አንዲት መጠመቂያ ስፍራ ለሠላሳ ስምንት ዓመት በሙሉ ሲታመም የኖረን ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ መፈወሱን አስታውሰው፣ ስንፍና ወደ ኃጢአት ሊመራ የሚችል መሆኑን ተናግረዋል። ዛሬ የተነበቡት ቅዱሳት መጽሐፍት ስለ ውሃ እንድናስተነትን ይጋብዙናል ያሉት ቅዱስነታቸው ውሃ የመዳንም፣ የጥፋትም ምልክት ሊሆን ይችላል ብለው ዛሬ የተነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ውሃ ለመዳን የሚያገለግል መሆኑን አስረድተዋል። ከትንቢተ ሕዝ. 47 ተወስዶ የተነበበው የመጀመሪያው ንባብ ውሃ ሕይወትን እንደሚሰጥ እንደዚሁም ከዮሐ. 5፡1-16 ተወስዶ የተነበበው ሁለተኛ ንባብ ሕሙማን ካደረባቸው ሕመም ለመፈወስ ብለው ውሃ ወዳለበት ሥፍራ የሚሄዱ መሆኑን አስታውሰዋል። ዛሬ በተነበበው የወንጌል ክፍል እንደተጠቀሰው ቤተ ሳይዳ በተባለች የመጠመቂያ ስፍራ ብዙ ሕሙማን አካለ ስንኩላን፣ ዐይነ ስውሮች፣ አንካሶችና ሽባዎች ለመፈውስ ይጠብቁ ነበር።

“አልፎ አልፎ የጌታ መልአክ ወርዶ ውሃውን በሚያናውጥበት ጊዜ፣ ቀድሞ ወደ መጠመቂያዪቱ የገባ ካደረበት ማንኛውም በሽታ ይፈወስ ነበር። በዚያም ለሠላሳ ስምንት ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር። ኢየሱስም ይህን ሰው ተኝቶ ባገኘው ጊዜ፣ ለብዙ ጊዜ በዚህ ሁኔታ እንደ ነበር ዐውቆ “ልትድን ትፈልጋለህን?” አለው። ሕመምተኛውም መልሶ፣ “ጌታዬ፣ ውሃው በሚናወጥበት ጊዜ ወደ መጠመቂያዪቱ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ ለመግባትም ስሞክር ሌላው ይቀድመኛል” አለው። ኢየሱስም፣ “ተነሥ! አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። ሰውየውም ወዲያው ተፈወሰ፤ መተኛውንም ተሸክሞ ሄደ”። (ዮሐ. 5: 4-16)   

ይህ የወንጌል ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ስላነጋገረው በሽተኛ እንድናስብ ይጋብዘናል ያሉት ቅዱስነታቸው  በእርግጥ ሰውየው የሕመም ምልክቶች ቢታዩበትም ትልቁ ሕመሙ የልብ እና የነፍስ፣ የሀዘን፣ የስንፍና እና የጭንቀት መሆኑን አስረድተዋል። በሕይወት ለመቆየት እና ለመፈወስም ይመኝ እንደነበር፣ ነገር ግን ካደረበት ሕመም ለመፈውስ ምንም ዓይነት የግል ጥረት ሳያደርግ በሰዎች እያሳበበ ለሰላሳ ስምንት ዓመታት መቆየቱን አስረድተዋል። የዚህ ሰው ኃጢአት ሌሎችን ጥፋተኛ ማድረግ እንደነበር ገልጸው፣ ስንፍና ሰይጣን የሚዘራው የኃጢአት ፍሬ መሆኑን አስረድተዋል።

ዛሬ የተነበበውን የወንጌል ክፍል (ዮሐ. 5: 1-16) ባለፈው እሑድ ከተነበበው (ዮሐ. 9: 1-41) ተውስዶ ከተነበበው የወንጌል ክፍል ጋር ያወዳደርይት ቅዱስነታቸው እሑድ በተነበበው የወንጌል ክፍል እንደተጠቀሰው ፈውስን ያገኘው ሰው ታላቅ ደስታ ተሰምቶት ቆራጥ ውሳኔን በማድረግ ከሙሴ የህግ መምህራን ጋር መከራከሩን አስታውሰው፣ ከዚህ በተለየ መልኩ ከዮሐ. 5: 1-16 ተወስዶ የተነበበው የወንጌል ክፍል፣ የበኩሉን ግዴታ ሳይወጣ በሌሎች ሰዎች በማሳበብ የኃጢአት ምንጭ በሆነው ስንፍና መያዙን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። በተመሳሳይ መልኩ በዘመናችን ክርስቲያኖች ዘንድ የሚታይ የስንፍና ምልክት እንዳለ ያስረዱት ቅዱስነታቸው ስንፍና ትክክለኛውን የክርስትና ሕይወት እንዳንኖር የሚያደርግ መርዝ ነው ብለዋል።

በዮሐ. 5 ላይ የተጸፈው ታሪክ ደግመን የምናነብ ከሆነ በኃጢአት ውስጥ እንድንወድቅ የሚያደርገን ትልቁ ፈተና የቱ እንደሆነ በሚገባ እናውቃለን ያሉት ቅዱስነታቸው ሌሎች ሰዎችን የኃጢአት ምክንያት ከማድረግ ይልቅ የራስን ድክመት በማመን ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘውን ምሕረት እና ፈውስ መለመን ያስፈልጋል ብለዋል። የሃይላችን እና የሕይወታችን ምሳሌ የሆነውን ውሃ ማሰብ ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ውሃን በሕይወት እንድንኖር ለጥምቀት ተጠቅሞታል ብለው ሰይጣን ግን የክርስትናን ሕይወት ለማደናቀፍ ስንፍናን ይጠቀማል ብለዋል።

ኃጢአት ምን ያህል አስቀያሚ እና ክፉ መሆኑን እንድንረዳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን ብለው በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከማጠቃለላቸው በፊት የሚከተለውን ጸሎት በሕብረት እንድናቀርብ ጠይቀዋል፥

“ኢየሱስ ሆይ! በቅዱሳት ምስጢራት ውስጥ አንተ እንደምትገኝ በእውነት አምናለሁ፤ ከሁሉ በላይ እወድሃለሁ፣ በሕይወቴ ውስጥ አንተ እንድትገኝ እመኛለሁ። በዚህ አስፈሪ ወቅት የአንተን ስጋ እና ደም መቀበል ባልችልም ከዚህ በፊት እንዳደረከው ሁሉ ዛሬም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በልቤ ውስጥ ግባ። ካንተ ላለመለየት ወስኜአለሁና በሙሉ ልቤ እቀበልሃለሁ”

በማለት የዕለቱን አስተንትኗቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
24 March 2020, 17:48
ሁሉንም ያንብቡ >