ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

“ስልጣን፣ ለማዘዝ ሳይሆን ትክክለኛ ሕይወትን በተግባር ለመመስከር ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጥር 5/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን የተገኙበትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከታቸው፣ ከእውነተኛ የእግዚአብሔር የትህትና እና የፍቅር መንገድ ርቀው የሚገኙ፣ ራሳቸውን ክርስቲያን ነን፣ አልፎ ተርፎም የቤተክርስቲያን መሪዎች ነን የሚሉ፣ ተግባራቸው ሲታይ ግን ክፋትን የሚፈጽሙ መኖራቸውን ገልጸዋል።     

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከማር. 1፡21-28 ተወስዶ በተነበበው በዛሬው የቅዱስ ወንጌል ንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምር የነበረው እንደባለስልጣን ነው” ብለው የእርሱን የማስተማር ስልጣን ወንጌላዊው ማርቆስ በምዕ. 1፡22 ላይ ሲገልጽ፣ ኢየሱስ፣ የሙሴ ሕግ መምህራን እንደሚያስተምሩት ዓይነት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ነበር፤ ስለዚህም የሰሙት ሁሉ በትምህርቱ ተደነቁ” በማለት ማስረዳቱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። የኢየሱስ ክርስቶስን የማስተማር ስልጣን መሠረት በማድረግ አስተንትኖአቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ውስጣዊ ሥልጣን እና በሙሴ የሕግ መምህራን መካከል ያለውን ልዩነት ሲያብራሩ፣ “የሙሴ የሕግ መምህራን ምንም እንኳን በሕግ ዕውቀት የተካኑ፣ በሕዝቦቻቸው ተደማጭነትን ቢያገኙም፣ ነገር ግን እምነት አልተጣለባቸውም” ብለዋል።          

የኢየሱስ የማስተማር ዘይቤ ክብር የሚሰጠው ነው፣

“የኢየሱስ ክርስቶስ የማስተማር ዘይቤው የቱ ነበር”? የኢየሱስ ክርስቶስ የማስተማር ዘይቤ የሚያንጽ፣ የሚቀሰቅስ፣ የሚፈውስ እና የሰዎችን ጥያቄ የሚያዳምጥ ነው። ይህን የመሰለ የማስተማር ስልት ከየትም ሳይሆን ከልብ የሚመነጭ እና በዓይንም የሚታይ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የማስተማር ሥልጣኑን መጠቀም የቻለው የሚያስተምረውን በዕለታዊ ሕይወቱ በተግባር ገልጾ ስላሳየ ነው። አንድ ሰው በእርግጥም የማስተማር ሥልጣን አለው የሚያሰኘው የሕይወት ምስክርነቱ ነው”።        

የሙሴ ሕግ መምህራን ያስተምራሉ፤ ነገር ግን በተግባር አያሳዩትም፣

“የሙሴ ሕግ መምህራን የሚያስተምሩትን እየኖሩበት በተግባር የሚያሳዩ ሆነው አልተገኙም” ያሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስም በሌላ ወገን  የሙሴ ሕግ መምህራን የሚያስተምሩትን ሕዝቡ በተግባር እያሳየ እንዲኖር፣ ነገር ግን የሚያድረጉትን እንዳያደርጉ ይመክራቸው ነበር ብለው፣ የሙሴ ሕግ መምህራን በሥራቸው የተወቀሱ መሆናቸው በወንጌላት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች መጠቀሱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

የሙሴ ሕግ መምህራን ሕይወት በትክክል ለመግለጽ ኢየሱስ የተጠቀመው ቃል “ግብዝነት” የሚል ነው። በማቴ. 23 ላይ የተገለጸውን ብንመለከት፣ ኢየሱስ ስለ ግብዝነት ሕይወት ብዙ ጊዜ እንደተናገረ እናያለን። ሐዋርያዊ አደራን በተሸከሙ ሰዎች ዘንድ ግብዝነት ሲንጸባረቅ እናያለን። እነዚህ ሰዎች የተጣለባቸው ሐዋርያዊ አደራ ይኑራቸው እንጂ በግብዝነታቸው ምክንያት የማገልገል ሥልጣናቸውን በአግባቡ የሚወጡ አይደሉም። ቢሆንም የእግዚአብሔር ሕዝብም የዋህ በመሆኑ ይታገሳቸዋል። የሚሳሳቱትን፣ የግብዝነት ሕይወት የሚኖሩ በቁጥር በርካታ ሐዋርያዊ አገልጋዮችን ይቅር ይላቸዋል”።    

የክርስቲያን ግብዝነት ውርደትን ያስከትላል፣

“ለሐዋርያዊ አገልጋዮቹ ይቅርታን የሚያደርግ የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ የፀጋን ኃይል መለየት ይችላል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዛሬው የመጀመሪያ ንባብ፣ ከ1ኛ ሳሙኤል ምዕ. 1 : 9-20 ላይ ተውስዶ በተነበበው በማስተንተን እንደተናገሩት፣ ካህኑ ኤሊ፣ የበረውን ሥልጣን በሙሉ በማጣት፣ የቀረው ነገር ቢኖር የመቀባት ጸጋ ብቻ እንደሆነ፣ በዚህ ጸጋ በመታገዝ፣ ልጅ ለመውለድ ከፍተኛ ምኞት የነበራት ሐናን በመባረክ ተዓምር መሥራቱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

“የእግዚአብሔር ሕዝብ በአንድን ሰው የመንፈሳዊ አገልግሎት ሥልጣን እና በጸጋ ቅባት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚገባ ለይቶ ያውቃል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ለንስሐ በሚቀርቡበት ጊዜ ለካህን የሚሰጡት አክብሮት ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ታላቅ ጥበብ፣ ለሚያገለግለው ሐዋርያዊ አባትም ይሁን ለክርስቲያን ወንድሞቹ እና እህቶቹ ይቅርታን ማድረግ ነው ብለዋል። ከእውነተኛ የእግዚአብሔር የትህትና እና የፍቅር መንገድ ርቀው የሚገኙ፣ ራሳቸውን ክርስቲያን ነን፣ አልፎ ተርፎም የቤተክርስቲያን መሪዎች ነን የሚሉ፣ ተግባራቸው ሲታይ በክፋት የተሞሉ መኖራቸው፣ ለውርደት የሚዳርግ የግብዝነት ሕይወት ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጥር 5/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ያደረጉትን የቅዱሳት መጻሕፍት አስተንትኖ ከማጠቃለላቸው አስቀድመው ባቀረቡት ጸሎት፣ የጥምቀትን ጸጋ የተቀበሉት በሙሉ የሐዋርያዊ አገልግሎት ሥልጣናቸውን፣ ራሳቸውን ከፍ ለማድረግ ሳይሆን አገልግሎታቸውን በእውነተኛ የሕይወት ምስክርነት፣ የሚያገለግሉትን ሕዝብ እግዚአብሔር ባዘጋጀላቸው መንገድ መምራት እንዲችሉ ጸጋን በመለመን የዕለቱን አስተንትኖአቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
14 January 2020, 16:30
ሁሉንም ያንብቡ >